ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ የነበረው የደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል፡፡
ገና ጨዋታው በተጀመረ በመጀመሪያው ደቂቃ በ38ኛው ሰኮንድ ኤልያስ የጎል ሙከራ አድርጎ የግራው ቋሚ በመለሰበት መንገድ ሙቀቱ ይበልጡኑ የጋለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና አብላጫ የማጥቃት እንቅስቃሴ እና በደደቢት የጥንቃቄ እንዲሁም ጥብቅ መከላከል አጨዋወት ላይ አተኩሮ ያለግብ ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በ 4 – 3 – 3 የተጨዋቾች የሜዳ ላይ መነሻ የአደራደር ቅርፅ ጨዋታውን የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ጊዜዎች ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን ለማድረግ የሚያስችሉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ተግብረዋል ። በተለይም በሜዳው ቁመት ያለውን የግራ መስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ ሂደትን መተግበሪያ በማድረግ በአብዱልከሪም ፣ ኤልያስ እና አስቻለው ጥምረት በደደቢቶች በኩል የሚገኙት ደስታ እና ሽመክት ላይ የበላይነት መውሰድ ችለዋል፡፡ በ9ኛው ደቂቃ ላይም አህመድ ከግራ መስመር በጥሩ እይታ በረጅሙ ለሳኑሚ ያሻማው የአየር ላይ ኳስ አጥቂው በጭንቅላቱ ገጭቶ በግቡ አናተ ትወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ ይህ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ቀጥሎ በ26ኛው እና 28ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው እና ሳኑሚ ጥሩ የሚባሉ የጎል ሙከራዎችን አድርገው የመጀመርያውን ክሌመንት ሲያድነው ሁለተኛውን ደግሞ በአግዳሚው በኩል ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡
በአንጻሩ ደደቢቶች የመጀመርያውን አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የቡናን የማጥቃት አጨዋወት በመመከት እና አደገኛ የሚባሉ የጎል ሙከራዎችን በመቀነስ ላይ ባተኮረ አጨዋወት ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል፡፡ በ4-1-3-2 (በዳዊት ወደኋላ መሳብ ምክንያዥ ይበልጠኑ 4-1-3-1-1 ፣ 4-1-4-1 ) ይመስል የነበረው የቡድኑ ቅርጽ የቡድኑን ወሳኝ አጥቂ ጌታነህ ከበደን ከአማካዮቹ እንዲነጠል አስገድዶታል፡፡ በዚህም ምክንያት አጥቂውም ሆነ አጠቃላይ ቡድኑ ተጠቃሽ የጎል ሙከራ ሳያደርጉ የጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡
የሁለቱ ቡድኖች የአጨዋወት ሒደት በሁለተኛው አጋማሽም ተመሳሳይ የነበረ ሲሆን እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በዚህም ቡናዎች በግብ ሙከራ የበላይ ነበሩ፡፡ በ58ኛው እና 59ኛው ደቂቃ ላይም በተከታታይ ሳኑሚ እና አስቻለው ከሳጥን ውጪ ከተመሳሳይ ርቀት የሞከሯቸው ኳሶች የግብ ጠባቂው ክሌመንት ሲሳይ ሆነዋል፡፡
በደደቢት በኩል አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በ53ኛው ደቂቃ አቤል እንዳለን በኤፍሬም አሻሞ በመተካትና የመሀለኛውን ክፍል እንዲመራ በማድረግ ለጌታነህ እና አማካዮች አገናኝ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዳዊት ፍቃዱ ከመስመር እየተነሳ እንዲያጠቃ ቢያደርጉም የታሰበውን ያህል የማጥቃት እንቅስቃሴው ስኬታማ ሳይሆን እንዲሁም የግብ ሙከራ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ ሆኖም በመከላከሉ ጠንካራ መሆናቸው ከጨዋታው 1 ነጥብ ይዘው እንዲወጡ አግዟቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ወንድይፍራው ጌታሁን የደደቢት ቅብብሎች ወደ አደጋ ክልል ሳይደርሱ በመቁረጡ ረገድ የተሳካ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል፡፡ ጌታነህ ከበደን ጥብቅ በሆነ የሰው በሰው ቁጥጥር ስልት የ1ለ1 ግንኙነቶችን ሲያሸንፍ ተስተውሏል፡፡
በአጠቃላይ ጨዋታው የተጠበቀውን ያህል እንቅስቃሴ እና የመሸናነፍ ፉክክር ያላስተናገደ ሆኖ ተጠናቋል፡፡ ሁለቱ ክለቦች በሊጉ ባላቸው የእርስ በእርስ ግንኙነት ታሪክም ጎል ሳይቆጠርበት እና ሳይሸናነፉ የተጠናቀቀ የመጀመርያ ጨዋታ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡