የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች ሲቀጥሉ ወደ አርባምንጭ ያቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከተማን 4 – 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
በርካታ ቁጥር ያለው ተመልካች በታደመበት የዛሬው ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት የአርባምንጭ ከተማ ደጋፊዎች የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ምንተስኖት አበራን ኮከብ ተጨዋች አድርገው የሸለሙ ሲሆን በተጨማሪም በቀድሞ አርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅና ለአርባምንጭ ከነማ ተጫውተው ላሳለፉት ታሪኩ ተስፋዬ እና ስለሺ ሽብሩ ለከተማዋ ክለቦች የሰጡትን አገልግሎት በማስታወስ የክብር ሽልማት ሰጥተዋል።
ብዙም ሳቢና የተደራጀ አጨዋወት ባልታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ አርባምንጮች ወደ ጎል በመቅረብና በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢወስዱም ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ጠንካራ የግብ ሙከራ ልናይ አልቻልንም። በመጀመርያው አጋማሽ ላይ ምንም እንኳን በሁለቱም ቡድኖች መካከል ጥሩ የአልሸነፍ ባይነት ፉክክር የነበረ ቢሆንም በተደጋጋሚ በሚሰሩ ጥፋቶች ጨዋታው እየተቆራረጠ ፍሰት ያለው እግርኳስ እንዳይኖር ሆኗል። የመጀመርያው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተቀይሮ በመግባት በዕለቱ ፈረሰኞቹ ካስቆጠሯቸው ጎሎች ውስጥ በሶስቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆኖ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው አስራ አንድ ቁጥር ለባሹ ፕሪንስ ሴቨሪን በ41 ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ጥሩ አቋቋም ላይ ይገኝ የነበረው በኃይሉ አሰፋ ወደ ግብነት በመቀየር ፈረሰኞቹ መሪ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ አድርጓል።
ከእረፍት መልስ ከመጀመርያው አጋማሽ ፍፁም በተሻለ ሁኔታ ጠንካራ እና ማራኪ ጨዋታ የተመለከትን ሲሆን ባለ ሜዳዎቹ አርባምንጮች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ ፍለጋ ነቅለው በመውጣት ጫና መፍጠር ችለዋል። እንግዶቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንፃሩ ፍጥነት ባለው መልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ተንቀሳቅሰዋል። በጨዋታው 48ኛ ደቂቃም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመልሶ ማጥቃት የፈጠሩትን ግልፅ የግብ አጋጣሚ ምንተስኖት አዳነ አምክኗል።
አዳነ ግርማ በ65ኛው እና 75ኛው ደቂቃ ላይ ልምድ እና ችሎታውን ያስመሰከረባቸውን ግሩም ጎሎች በማስቆጠር ፈረሰኞቹን 3 – 0 እንዲመሩ አስችሎ አርባምንጮች አቻ ለመሆን ያደርጉ የነበረውን ጥረት ተስፋ አስቆራጭ እንዲሆን አድርጓል። አዳነ ግርማ ላስቆጠራቸው ሁለቱም ግቦች የፕሪንስ ሴቨሪን ሚና ትለቅ ነበር። በግብ ልዩነቱ መስፋት የተከፋው ተመልካችም ጨዋታው ለመጠናቀቅ ብዙ እየቀረው ስቴዲሙን በመልቀቅ ሲወጣ ተስተውሏል።
ከአዳነ ግርማ ግቦች በኋላ ፈረሰኞቹ ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን በ87ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ቦጋለ በክርን በመማታቱ ምክንያት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ በመወገዱ የቁጥር ብልጫውንም ለቀሪ ደቂቃዎች ይዘዋል።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው ታደለ መንገሻ በግምት ከ20 ሜትር ርቀት ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ከመረብ አገናኝቶ ከማስተዛዘኛነት ያለፈ ፋይዳ ያልነበረው ግብ ለአርባምንጭ ከተማ አስቆጥሯል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስ በመልሶ ማጥቃት የፈጠረውን ዕድል ብሩኖ ኮኔ የማሳረጊያ ግብ አድርጎታል። ግቧ በጥር የዝውውር መስኮት ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው አይቮሪያዊ አጥቂ በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ ያስቆጠራት የመጀመርያ ግብም ሆና ተመዝግባለች። ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ፈረሰኞቹ በ32 ነጥብ መሪነታቸውን አስጠብው ሲቀጥሉ ተሸናፊው አርባምንጭ ከተማ በ22 ነጥብ በነበረበት 7ኛ ደረጃ ለመቀጠል ተገዷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በስታዲየሙ ከፍተኛ የሆነ ሁከትና ግርግር ተፈጥሯል። የአርባምንጭ ስታዲየም ኳስ አቀባይ የሆነ አንድ ወጣት ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ሳላህዲን ባርጌቾ ጋር የፈጠሩት ውዝግብ ለነገሩ መነሻ የሆነ ሲሆን በስታዲየሙ የተገኘው ደጋፊ ድንጋይ ወደ ሜዳው ሲወረውር ነገሩን በቀላሉ መቆጣጠር ሲቻል የፀጥታ ሀይሎች የአስለቃሽ ጭስ እና ተኩስ በመጠቀም ከመጠን ያለፈ ምላሽ በመስጠታቸው ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ግርግር ተፈጥሮ ጉዳት አስከትሏል። እስከ 12:15 ድረስ ተጨዋቾቹም ሆኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባት ቆይተው ችግሩ ከተፈታ በኋላ ሁሉም በሰላም ወደመጡበት አምርተዋል።