ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዋሊድ አታ ወደ ሳውዲ አረቢያው ናጅራን ስፖርት ክለብ ዝውውሩን አጠናቅቋል፡፡ የመሃል ተከላካዮ ከህዳር ወር አንስቶ ክለብ የሌለው ስለነበር በነፃ ዝውውር ነው የሳውዲውን አንደኛ ዲቪዚዮን ክለብ የተቀላቀለው፡፡
በደቡባዊ ምዕራብ ሳውዲ አረቢያ የምትገኘው ናጅራን በሳውዲ እና የመን ድንበር ላይ የምትገኘ ከተማ ነች፡፡ በየመን ባለው የአለመረጋጋት ምክንያት ክለቡ አሁን ላይ አባ በምትባል የሳውዲ ከተማ ጨዋታዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ከቻይና ክለቦች የተጫወትልን ጥያቄ ያልተቀበለው ዋሊድ ወደ ትውልድ ሃገሩ ከመዘዋወሩ በፊት በስዊድን የተጫወትልን ጥያቄዎች ቀርበውለት እንደነበር ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ “የተጫወትልን ጥያቄዎች ከስዊድን ክለቦች ነበሩ፡፡ ቢሆንም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የባህር ሰላጤ ሃገራት እግርኳስን የመጫወት አላማ ከበፊትም ነበረኝ፡፡ የተሻለ ደሞዝም ስለቀረበልኝ ወደ ሳውዲ ላመራ ችያለው፡፡ ከገንዘቡ ባሻገር አዲስ የሆነ የእግርኳስ ባህል እና የተለየ ነገር ለመሞከር ማሰቤ ወደ ናጅራን እንድመጣ አስችሎኛል፡፡”
ዋሊድ ክለቡን ቢቀላቀልም እስካሁን ጨዋታ ማድረግ አልቻለም፡፡ ከኦስተርሰንድስ ጋር በህዳር ወር ከተለያየ በኃላ ከጨዋታ መራቁ ፊትነሱን ለማግኘት ግዜያት እንደፈጀበት ይናገራል፡፡ “ናጅራንን የተቀላቀልኩት በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ነው፡፡ በስዊድን ደግሞ ግዜው የእረፍተ ነው ሊጉ ስለሚጠናቀቅ፡፡ የተሻለ አቋም ላይ ለመድረስ ጠንክሬ ልምምዴን እየሰራው እገኛለው፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ በሚኖረን ጨዋታ ላይም የመሰለፍ እድል የሚገጥመኝ ይመስለኛል፡፡”
ናጅራን በ2015/16 ለአስር ዓመታት ከቆየበት የሳውዲ ፕሪምየር ሊግ ወርዷል፡፡ ክለቡ ከአንደኛ ዲቪዚዮን ክለቦች በተሻለ ጥራት ያላቸውን ተጫዋቾችን ቢሰበስብም ዳግም ወደ ሃገሪቱ ታላቅ ሊግ የሚያደርገው ጉዞ በፈተና የታጀበ ሆኗል፡፡ ከመሪው በስምነት ነጥብ የራቀ ከመሆኑ ባሻገር በወጥነት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ሲሳነው ነበር፡፡ “ናጅራን በአንደኛ ዲቪዚዮን ክለቦች ትልቁ ነው፡፡ በወረቀት ላይ ጥሩ ቡድን ነው በውጤት ደረጃ ግን ተገላቢጦሽ ነው፡፡ 2 ክለቦች በቀጥታ ወደ ዋናው ሊጉ ያድጋሉ፡፡ ሶስተኛው ክለብ ደግሞ በማጣሪያ ነው የሚገባው፡፡ ከመሪው ጋር በሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታ አለን፡፡ የነጥብ ልዩነቱን አጥብቦ የውድድር ዘመኑን ለማሳመር ጨዋታው ለእኛ ሲበዛ ወሳኝ ነው፡፡” ይላል የ30 ዓመቱ የቀድሞ የቢኬ ሃከን እና ኤአይኬ ተከላካይ፡፡
በፈረንጆቹ 1986 በሪያድ ከኢትዮጵያዊ እናት እና ኤርትራዊ አባት የተወለደው ዋሊድ ወደ ተወለደባት የመካከለኛው ምስራቅ ሃገር እግርኳስን መጫወት መቻሉ አስደስቶታል፡፡ “ቤተሰቦች በጅዳ እና ሪያድ አሉኝ፡፡ ወደ እዚህ መጥቼ መጫወት መቻሌ እና ቤተሰቦቼን ማግኘቴ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የተለየ ስሜትም ፈጥሮብኛል፡፡”
በቀጣይ የዋሊድ እቅድ ወደ ተሻለ ክለብ ማምራት እንደሆነ ይናገራል፡፡ “በናጅራን በሚኖረኝ ቆይታ የተሻለ ተጫውቼ ወደ ሳውዲ አረቢያ ዋና ሊግ ክለቦች ወይም ካታር ክለቦች ማምራት ነው ፍላጎቴ፡፡ አሁን ላይ ክለብን ወደ ዋናው ሊግ የማሳደግ ፍልሚያ ላይ የበኩሌን መውጣት እፈልጋለው፡፡”
ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መጫወት ምርጫው ካደረገ በኃላ ዋሊድ በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ በዋሊያዎቹ መለያ ተመልክተነዋል፡፡ ስለኢትዮጵያ የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ምድብም መስራት ከተቻለ ወደ ካሜሮን ማምራት እንደሚቻል አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ “አሁን ላይ የምድብ ድልድሉ ጠንካራ ነው፡፡ የማለፍ እድል አለ በእግርኳስ የማይቻል ነገር የለም፡፡ ባለፈው የጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ በጥቃቅን ነገሮች ማለፍ አልቻልንም፡፡ ይህ በጣም ያስከፋል፡፡ አሁን ላይ ያለው ምድብ ጠንካራ ከሆኑ ሃገራት ጋር በመሆኑ ጠንካራ ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡ በሜዳችን በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብን መሰብሰብ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እኔም ወደ ብሄራዊ ቡድን ከተመልሼ ቡድኑን መርዳት እፈልጋለው፡፡” ሲል ሃሳቡን አጠናቅቋል፡፡