በሴቶች ጥሎ ማለፍ ባንክ ፣ ደደቢት ፣ ሀዋሳ እና ጥረት ወደ ሩብ ፍጻሜ አልፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ 2ኛ ዙር ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጠናቋል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ጥረት ኮርፖሬት እና ደደቢትም ወደ ሩብ ፍጻሜ ያለፉበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

09:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመው ጥረት ኮርፖሬት 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል፡፡ ወርቅነሽ መልሜላ ጥረትን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ስታስቆጥር ሙሉወርቅ በሪሁን በፍጹም ቅጣት ምት አቻ ማድረግ ችላ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ የጥረት የጨዋታ ብልጫ የታየ ሲሆን ግቦች ለማስቆጠር ሲቸገሩም አልታዩም፡፡ ተከላካይዋ አሳቤ ሙሶ ፣ ፍቅርተ አስማማው እና ሊድያ ጌትነት አከታትለው ባስቆጠሯቸው ግቦችም 4-1 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀል ችለዋል፡፡

አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ በ10:00 ሀዋሳ ከተማ መከላከያን 2-1 አሸንፏል፡፡ በሁሉም ረገድ ብልጫ የነበራቸው ሀዋሳዎች በስንታየሁ ማቲዮስ ጎል ቀዳሚ ሲሆኑ ብሩክታዊት አየለ መከላከያን አቻ አድርጋ እረፍት ወጥተዋል፡፡ ከእረፍት መልስ ጠንካራ ፉክክር በታየበት ጨዋታ በዘንድሮ አመት የሀዋሳ ከነማ ውጤታማ ጉዞ  ምርጥ አቋሟን በማሳየት ላይ የምትገኘው ትርሲት መገርሳ ሀዋሳ ወደ ቀጣዩ ዝር ያለፈበት ወሳኝ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

11:30 ላይ አርባምንጭ ከተማን የገጠመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ አማካይዋ ህይወት ደንጊሶ የግቧ ባለቤት ነች፡፡ ንግድ ባንክ በጨዋታው ከአርባምንጭ ከባድ ፈተና ደርሶበት ተስተውሏል፡፡

ዛሬ ደደቢት ከ ሲዳማ ቡና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ሲዳማ ባለመገኘቱ ምክንያት ደደቢት በፎርፌ ወደ ተከታዩ ዙር ማለፍ ችሏል፡፡

የ2ኛ ዙር ውጤቶች

አርብ የካቲት 17 ቀን 2009

ድሬዳዋ ከተማ 0-3 ኢ.ወ.ስ. አካዳሚ (ፎርፌ)

ቦሌ 0-1 ንፋስ ስልክ ላፍቶ

አዳማ ከተማ 3-1 ቅድስት ማርያም

ልደታ 1-5 ጌዲኦ ዲላ

ማክሰኞ የካቲት 21 ቀን 2009

ጥረት 4-1 ኢትዮጵያ ቡና

ደደቢት 3-0 ሲዳማ ቡና (ፎርፌ)

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 አርባምንጭ ከተማ

መከላከያ 1-2 ሀዋሳ ከተማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *