ወላይታ ድቻ አራት ተጫዋቾችን ከቡድኑ ቀንሷል

በዝውውር መስኮቱ ሁለት ተጫዋች በውሰት ያገኘው ወላይታ ድቻ በውድድር ዘመኑ በቂ ግልጋሎት አላበረከቱልኝም ያላቸው አራት ተጫዋቾች ከቡድኑ ማሰናበቱን አስታውቋል፡፡

መሳይ አንጪሶ በወላይታ ድቻ ከተሰናበቱ ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡ አማካዩ በቡድኑ ውስጥ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች አንዱ የነበረ ሲሆን ዘንድሮም በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ችሎ ነበር፡፡

ዮርዳኖስ ዮሃንስ ሌላው የስንብት እጣ የደረሰው ተጫዋች ነው፡፡ አማካዩ አምና በዝዋይ በተካሄደው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ለመተሀራ ስኳር ባሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የአሰልጣኝ መሳይን ቀልብ ስቦ ክለቡን ቢቀላቀልም በድቻ የመጫወት እድል ሳያገኝ ቆይቶ በመጨረሻ ከክለቡ ጋር ተለያይቷል፡፡

በ2007 በሀድያ ሆሳዕና ድንቅ እንቅስቃሴ አድርጎ ወደ ድቻ ያመራው ቴዎድሮስ መንገሻ ክለቡን ከተሰናበቱ ተጫዋቾች መካከል ይገኝበታል፡፡ አጥቂው በወላይታ ድቻ የ1 አመት ከ6 ወር ቆይታው ወጠ ጥአቋም ማሳየት ተስኖት ቆይቷል፡፡

እንደ ዮርዳኖስ ሁሉ በብሄራዊ ሊጉ ድንቅ አቋም አሳይቶ ከአራዳ ክፍለ ከተማ ክለቡን የተቀላቀለው የግራ መስመር ተከላካዩ ዳዊት መኮንን ለቡድኑ አንድም ጨዋታ ሳያደርግ ተሰናብቷል፡፡

ወላይታ ድቻ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት አሳምነው አንጀሎን ከድሬዳዋ ከተማ ፣ ፍራኦል መንግስቱን ከኢትዮጵያ ቡና በውሰት ውል ማስፈረሙ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *