ቅሬታ ያስከተለው የአአ ከተማ የአሰልጣኝ ሹመት እና የክለቡ ምላሽ…

አዲስ አበባ ከተማ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በገዛ ፍቃዳቸው ከስራ መልቀቃቸውን ተከትሎ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ አስራት አባተን ሾሟል፡፡ የስዩም ከበደ ረዳት የነበሩት በፀሎት ልኡልሰገድ ደግሞ በአስራት አባተ ረዳት ሆነው እንዲቀጥሉ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ሆኖም አሰልጣኝ በጸሎት የረዳት አሰልጣኝነት ሚናቸው እንዲቀጥሉ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ የቅሬታ ደብዳቤ ለክለቡ በማስገባት አሳውቀዋል፡፡ ያለፉት ሁለት ተከታታይ ልምምዶች ላይም ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

አሰልጣኝ በፀሎት ለክለቡ ባስገቡት ደብዳቤ የክለቡ ወሳኔ አሳማኝ ያልሆነ መሆኑ ቅሬታ እኖፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

” ክለቡ እኔ በምክትልነት እንድቀጥል እና አስራትን በዋና አሰልጣኝነት ለመሾም የደረሰበትን ውሳኔ አከብራለሁ፡፡ ነገር ግን ውሳኔው ያለኝን የስራ ልምድ ፣ የትምህርት ዝግጁነት ፣ ለቡድኑ ያለኝን ቅርበት እና ለቡድኑ እያበረከትኩት ያለውን አስተዋጽኦ ያላገናዘበ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዋና አሰልጣኝነት የተሾሙት በሴቶች እግርኳስ ላይ ብቻ ከመስራታቸው በተጨማሪ በትምህርት ዝግጅትም ፣ ቀጥተኛ ተያያዥነት ባለው የስራ ልምድም ሆነ ከክለቡ ጋር ባለኝ ቀረቤታ ፣ የተቃራኒ ቡድንን ጠንካራ እና ደካማ ጎን እንዲሁም የሚከተሉትን ስትራቴጂዎች የማወቅ እና የተሻለ ስራ የመስራት ፣ ኃላፊነቱንም የመረከብ እድሉ የኔ ሆኖ ሳለ ክለቡም ከእኔ ጋር ምክክር ሳያደርግበት የተላለፈው ውሳኔ በእኔም ሆነ በተጫዋቾቹ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን የሞራል እና የነልቡና ጉዳት ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ቅሬታ ፈጥሮብኛል፡፡ ”

“የተወሰነው ውሳኔ ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች ማዕከል ባደረገ መልኩ እንዲታይልኝ ስል በትህትና እየጠየክሁ ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ከክለቡ ጋር በስምምነት ለመለያየት የምገደድ መሆኑን እገልጻለሁ፡፡ ” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በበኩላቸው በፀሎት ቅሬታ የመግለፅ መብት እንዳለው ገልጸው ያቀረበበት መንገድ ግን አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

” ቅሬታ ማቅረቡ መብቱ ነው። የተሰማውን ነገር መግለፅ ይችላል፡፡ ሆኖም በየትኛውም የስራ ዘርፍ ቢሆን በሰለጠነ መንገድ ቅሬታን በማቅረብ ስራውን በሚገባ መስራት እንጂ ስራን ትቶ በመሄድ አይደለም፡፡ ሁለት ቀን በስራው ላይ አልተገኘም ፤ ይህ ደግሞ ስህተት ነው። ለማንኛውም አስተዳደሩ በቅርቡ ላቀረበው ቅሬታ ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል። ” ብለዋል፡፡

አቶ ገዛኸኝ አክለውም የአሰልጣኝ በጸሎት በስራ ገበታቸው አለመገኘት በቡድኑ ላይ ተፅዕኖ እንደማይፈጥር ገልጸው ክለቡ በጉዳዩ ዙርያ ያለውን ሁኔታ ወደፊት እንደሚያሳውቅ ጠቁመዋል፡፡

” የምክትል አሰልጣኝ አለመኖር ተፅዕኖ አይፈጥርም፡  ቡድኑ በትክክለኛው መንገድ እየሄደ ነው። ወሳኞቹ ተጨዋቾቹ ናቸው ፤ እነሱም በሰለጠነ መንገድ ተሰብስበው ስራቸውን እንደሚሰሩና ከአሰልጣኙ ጎን እንደሚቆሙ ገልፀዋል፡፡ ከእኛም ጋር በጥሩ ሁኔታ ተነጋግረን መግባባት ላይ ደርሰዋል። ስለዚህ ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድረው ነገር የለም ። ዋናው አሰልጣኝ ፣ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ እና የቡድን መሪው በጋራ በመሆን ወደ ጅማ በማቅናት ከጅማ አባቡና ጋር ያለውን ጨዋታ የሚመሩት ይሆናል፡፡ በክለቡ ቀጣይ ጉዞ ምን መሆን እንዳለበትም ወደፊት የምናሳውቅ ይሆናል”

ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት የተረከቡት አስራት አባተ በበኩላቸው ከሴት ቡድን ወደ ወንዶች ቡድን መሸጋገር አዲስ አሰራር እንዳልሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

” እንደውም ከወንድ ወደ ሴት ቡድን አሰልጣኝነት መሸጋገር ከባድ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ሴቶች ቡድን ላይ ሰርተው ወደ ወንዶች በመሸጋገር ውጤታማ የሆኑ አሰልጣኞችን እንደ ጳውሎስ ጌታቸው ፣ መሰረት ማኒ እና ያሬድ ቶሌራ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ”

አሰልጣኝ አስራት አክለውም ቡድኑን በሚገባ እንደሚያውቁት እና ለስራ እንደማይቸገሩ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

” በክትትል ደረጃ ሁሉንም የሀገራችን ቡድኖች በአካል ተገኝቼ እከታተላለሁ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ክለቤ ነው፡፡ የዋናውን እና የታዳጊዎቹን ጨዋታ ከአዲስ አበባ ውጪ እየወጣሁ ስከታተልም ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ችግር አይገጥመኝም፡፡ የመጀመርያ ልምምድ ሳሰራ እንደተመለከታችሁት የመጀመርያዬ አይመስልም”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *