በ16ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ የማይገባቸው ተጫዋቾች ለቡና እና ሀዋሳ ተሰልፈው ተጫውተዋል በሚል አአ ከተማ እና ደደቢት ለፌዴሬሽኑ ያስገቡት ክስ ውድቅ ተደርጓል፡፡
አዲስ አበባ ከተማዎች ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ መሀመድ ሲይላ የመኖርያ ፍቃድ እና ስራ ፍቃድ ሳያሟላ ነው የተጫወተው በሚል የተጨዋች ተገቢነት ክስ ለፌዴሬሽኑ ማቅረቡ ይታወሳል። የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ክሱን ተቀብሎ የውጭ ተጨዋቾች የዝውውርን ደንብ ከመረመረ በኋላ ተጨዋቹ ከማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የመኖርያ ፍቃድ እና የስራ ፍቃድ የተሟላ መረጃ አቅርቦ ቲሴራ የወጣለት በመሆኑ ለመጫወት ተገቢ መሆኑን አስታውቋል። በዚህም አዲስ አበባ ከተማ ያቀረበው የተገቢነት ክስ ውድቅ ሆኗል፡፡
ሌላው ክስ አቅርቦ የነበረው ደደቢትም ውድቅ ተደርጎበታል፡፡ ቡድኑ ከኢትዮዽያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ በውሰት ለሀዋሳ ከተማ የተሰጠ ተጨዋች ሆኖ ሳለ እንዲሁም ሀዋሳም የተጫዋቹ ይገባኛል ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ ሳያገኝ ከእኛ ጋር መጫወት አልነበረበትም በሚል ነበር ደደቢት ክስ ያቀረበው፡፡
በተጨዋቾች የውሰት ደንብ ላይ በተቀመጠው መሰረት አንድ ተጨዋች በውሰት ውል ላይ ሁለቱ ተወያይ ወገኖች ለኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴፌሽን አቅርበው በፌዴሬሽኑ ሲያፀድቀው ብቻ ነው ውሰቱ ተግባራዊ የሚሆነው፡፡ ስለዚህም በፌዴሬሽኑ እውቅና የተከናወነ የውሰት ውል ስለሌለ በሀዋሳ በኩል የቀረበው የውሰት ይገባኛልም ሆነ ደደቢት ያቀረበው የተጨዋች ተገቢነት ክስ ውድቅ መሆኑን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡