የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ሲካሄዱ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ተከታትለው የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ዙርያ ያሉ ጉዳዮችን እንዲህ አሰናድታዋለች፡፡
ቦታ – አዲስ አበባ ስታድየም
ቀን – ቅዳሜ የካቲት 25 ቀን 2009
ሰአት – 10፡00
ስርጭት – ቀጥታ የጽሁፍ ስርጭት በሶከር ኢትዮጵያ
ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ተፎካካሪ ሆነው በመሆኑ ለጨዋታው ልዩ ትኩረት እንድንሰጥ ያደርገናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ32 ነጥቦች ሲመራ ደደቢት በ28 ነጥቦች ይከተለዋል፡፡ ስለዚህም ከጨዋታው የሚገኘው ድል አንደኛውን ቡድን ይበልጥ ወደ ዋንጫው ሲያቀርበው ሌላኛውን ደግሞ የሊጉን ፉክክር ነፍስ እንዲዘራበት ይረዳዋል፡፡
የጨዋታ አቀራረብ
ምንም እንኳን በብዛት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ 4-3-3 እንዲሁም ደደቢት በ 4-4-2 የተጨዋቾች አደራደር ሲጠቀሙ ቢታዩም የሁለቱም ቡድኖች የጨዋታ አቀራረብ እንዲሁም ጠንካራ እና ደካማ ጎን ተቀራራቢ ነው። በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ደደቢት ዋነኛ የማጥቃት አማራጮቻቸው ሁለቱ መስመሮች መሆናቸው ጨዋታውን ለማሸነፍ በሁለቱ ክንፎች በኩል የሚደረገው ፉክክር የሚጠበቅ ነው የሚሆነው። የሁለቱም ቡድኖች ደካማ ጎን ተደርጎ በሚወሰደው በሜዳው ቁመት በሚደረግ እንቅስቃሴም የቡድኖቹ የአጥቂ አማካዮች የሚያደርጉት ፉክክር ለመስመሮቹ ጥቃቶች የሚኖራቸው አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነው። በዚህ ረገድ ደደቢት ዋነኛ የመሀል ክፍል ተሰላፊዎቹን በጉዳት እና በቅጣት ማጣቱ ነገሮችን ሊያከብድበት እንደሚችል መናገር ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪም የሁለቱ የሊጉ መሪዎች የመከላከል ጥንካሬ ሊነሳ የሚገባው ነው። የተረጋጋ የመሀል ተከላካዮች ጥምረት እና እምብዛም በማጥቃት ላይ የማይሳተፉ የመስመር ተከላካዮች ባለቤት የሆኑት ሁለቱ ቡድኖች በቀላሉ ግብ የሚቆጠሩባቸው አይደሉም። ይህም በመሆኑ ጌታነህ ከበደ እና ሳላሀዲን ሰይድ በሁለቱ ግቦች አፋፍ ላይ ከተጋጣሚያቸው የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ሌላው የጨዋታው ወሳኝ ነጥብ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በጥቅሉ ሁለቱም ቡድኖች ማጥቃት ላይ እና ግቦችን ማስቆጠር ላይ ያመዘነ የጨዋታ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም ደደቢት ከሌሎች ትልልቅ ቡድኖች ጋር በተጫወተባቸው አጋጣሚዎች ብልጫ ሲወሰድበት ወደኋላ ሲያፈገፍግ መስተዋሉ በዚህኛው ጨዋታ ተመሳሳይ አቀራረብ ሊያሳይ እንደሚችል የሚያስጠረጥር ነው የሚሆነው ።
የቅርብ ጊዜ አቋም
ቅዱስ ጊዮርጊስ | አሸ-አሸ-አቻ-አሸ-አሸ
የመጀመሪያውን ዙር ሁለት ጊዜ ብቻ ሽንፈት በማስተናገድ የጨረሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለተኛውንም ዙር በርከት ያሉ ግቦችን በማስቆጠር በድል ነበር የጀመረው ። ግቦችን በብዛት ከማስቆጠር ችግሩ ተላቆም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ማስቆጠሩ በነገው ጨዋታ አጥቂዎቹ በግብ ፊት የሚኖራቸውን በራስ መተማመን ከፍ እንዲል የሚያግዘው ይሆናል ።
ደደቢት | አቻ- አቻ-አሸ-አቻ-ተሸ
በ28 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደደቢት በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ያስመዘገበው ውጤት ከሊጉ መሪዎች አንዱ ከመሆኑ አንፃር ሲታይ ደካማ የሚባል ነው ። ሆኖም በአራቱ ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ መውጣቱ በርካታ ግብ ከሚያስቆጥር ቡድን ጋር እንደመጫወቱም መጠን በመልካም ጎኑ ሊነሳ የሚገባው ነው።
ግንኙነቶች
ደደቢት ወደ ሊጉ በመጣበት የ2002 የውድድር ዘመን በተገናኙበት ወቅት 0-0 በሆነ ውጤት በመለያየት የእርስ በእርስ ግኑኝነታቸውን የጀመሩት ሁለቱ ቡድኖች በቅርብ ጊዜያት ያደረጓቸው ጨዋታዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት የታየባቸው ነበሩ። ደደቢት ዋንጫውን ባነሳበት የ2005 የውድድር አመት ሁለተኛ ዙር በጊዮርጊስ ላይ ያስመዘገበው የ 3-1 ውጤት በሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ለመጨረሻ ጊዜ ያሳካው ድል ሆኖ ተመዝግቧል። በመጀመሪያው ዙር የዘንድሮ ግንኙነትም በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር ።
ጉዳት እና ቅጣት
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አሉላ ግርማ ፣ ራምኬል ሎክ እና ምንያህል ተሾመ አሁንም ከረጅም ጊዜ ጉዳታቸው ያላገገሙ በመሆኑ በቡድኑ ውስጥ አይካተቱም። ከዚህ በተጨማሪ አማካዩ ናትናኤል ዘለቀ በአርባምንጩ ጨዋታ አምስተኛ ቢጫ በመመልከቱ እንዲሁም ሌላው አማካይ አብዱልከሪም ኒኪማም በኤሌክትሪኩ ጨዋታ ባየው የቀይ ካርድ ምክንያት የአራተኛ ጨዋታ ቅጣቱ ላይ በመሆኑ በዚህ ጨዋታ ላይ አንመለከታቸውም። የፈረሰኞቹ የፊት አጥቂ ሳላሀዲን ሰይድ እና የመሀል ተከላካዩ ደጉ ደበበ ከጉዳታቸው በማገገም ወደልምምድ በመመለሳቸው ለዛሬው ጨዋታ እንደሚደርሱ ይታመናል።
የደደቢት ዋነኛ ጠንካራ ጎን የነበረውን የአማካይ ክፍል ጥምረት በዚህ ጨዋታ የማንመለከተው ነው ሚሆነው። አስራት መገርሳ የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ከደረሰበት ጉዳት ባለማገገሙ ይህ ጨዋታ የሚያመልጠው ሲሆን ሌላው አጣማሪው ካድር ኩሊባሊ ደግሞ አምስተኛ ቢጫ በመመልከቱ ከእለቱ ጨዋታ ውጪ ሆኗል።
ምን ተባለ?
ቅዱስ ጊዮርጊስ – ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ
ከቀድሞው አሰልጣኙ አስራት ሀይሌ ጋር ስለመገናኘቱ
” አሰልጣኝ አስራት ከዚህ በፊት መድንን ይዞ በተቃራኒ ቡድን አሰልጣኝነት ተገንኝተን ነበር አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የምንገናኘው ማለት ነው። እንደ አሰልጣኝ በእግር ኳስ ህይወቴ ትልቅ ቦታ ካለው አሰልጣኝ አስራት ሀይሌ ጎን መቆሜ ያስገርመኛል። ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ነገር የሰራው እና በእኔ የተጫዋችነት እና ያሰልጣኝነት ጉዞ ውስጥም ትልቅ ተፅዕኖ ካለው አስልጣኝ ጋር መገናኘቴ የሚያደስትም ጭምር ነው። በዚህም ለእርሱ ያለኝን ክብር ከፍ ያለ ነው። በእኔ የእግር ኳስ ህይወት ውስጥ ያለውን ተፅእኖም መቼም ቢሆን የምረሳው አይደለም፡፡
ስለጨዋታው
” ከኢንተርናሽናል ጨዋታ መልስ አርባምንጭን ባለፈው ሳምንት ገጥመናል። ይሄኛው ጨዋታ ሁለተኛችን ነው የሚሆነው። ደደቢት ትልቅ ቡድን ነው ፤ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችም አሉት። ትልቅ ልምድ ያለው አሰልጣኝ ባለቤትም በመሆኑ ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ። ነገር ግን በየሳምንቱ ለጨዋታዎች በምንዘጋጅበት መንገድ ነው ምንዘጋጀው። ባለፉት ጨዋታዎች የነበሩንን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በመለየት ለዚህኛው ጨዋታ እየተዘጋጀን ነው። ሁሉም ጨዋታ ለኛ አንድ አይነት ነው ። ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ ወደ ሻምፕዮንነት የሚመራን ነው ብለን ስለምናስብ እንደሁል ጊዜው በትኩረት እየተዘጋጀን ነው። ”
ደደቢት – አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ
የቀድሞው ክለቡን ስለመግጠሙ
” ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጨዋችነት ዘመኔ የተጫወትኩበት ክለብ ነው። በአሰልጣኝነትም ከታች ጀምሬ እስከ ፕሪምየር ሊግ ድረስ ያሰለጠንኩት ክለብ ነው። በሁለቱም አጋጣሚዎች በሀገር ውስጥ እንዲሁም በአፍሪካ ውድድሮች ብዙ ውጤታማ ጊዜዎችን አሳልፊያለው። በተጨማሪም በኔ ስር ተጫውተው ያለፉት ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታም አሁን ላይ ክለቡን እያሰለጠኑ ይገኛሉ። ቅዱስ ጊዮርጊስን በተቃራኒት ስገጥም የመጀመሪያ አይደለም ። ከዚህ በፊት የተለያዩ ክለቦችን ይዤ ጊዮርጊስን ገጥሚያለው። ያሸነፍኩበትም የተሸነፍኩበትም አጋጣሚ አለ ። ምንም እንኳን የቀደመ ታሪኬ ከጊዮርጊስ ጋር የተያያዘ ቢሆንም እንደባለሙያ አሁን ደደቢት ውጤታማ የሚሆንበትን መንገድ ነው የማስበው። ”
ስለጨዋታው
” ቡድናችን ከሞላ ጎደል እየተስተካከለ ነው። ከመሪው ብዙም ሳንርቅ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ነን። ሁሌም እንደምለው እግር ኳስ መላ ምት ነው። ጥሩ ተጫዉተን ጥሩ ውጤት ይዘን እንደምንወጣ አምናለው። በመጀመሪያው ዙር ጊዮርጊስ በቀላሉ አሸንፏል። በጊዜው አሰልጣኝ የነበርኩ ባይሆንም ጨዋታውን ግን ተከታትዬዋለው ። ያንን ጨዋታ በመንተራስም የሰራነው ስራ አለ። በፊት ከነበረው ቡድንም የአጨዋወት ለውጥ ማድረጋችን ይታወሳል። አሁን ላይ ወደ ውጤታማነት እየተመለስን ነው ማለት ይቻላል። ሌላው ጉዳይ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ላይ አጥቅተን አለመጫወታችን ነው። ይህም አስራት መገርሳ በማሟሟቅቅ ላይ ሳለ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት የተፈጠረ ነው። ተጨዋቾቻችን በአጋጣሚው ትንሽ ድንጋጤ ውስጥ የገቡበት አጋጣሚ ነበር የጨዋታው ዕቅዳችንም በአስራት ላይ የተመሰረተ የነበረ በመሆኑ ጎድቶናል። በዚህም ምክንያት ሳምሶንን ወደ ኋላ መልሰን ዳዊትን በሁለተኛ አጥቂነት ተጠቅመን በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሞክረን ነበር። ሆኖም ዳዊት የአማካይነት ባህሪ ስለሌለው የመሀል ሜዳ ብልጫ ተዎስዶብን ነበር ። ቢሆንም ግን አደጋ አልተፈጠረብንም ይጎል ዕድሎችንም መፍጠር ችለን ነበር ። በመሆኑም ከነዚህ ችግሮች በመነሳት ከጊዮርጊስ ጋር በሚኖረን ጨዋታ መልካም እንቅስቃሴ ለማድረግ አስበናል፡፡ ”
ጨዋታውን ማን ይመራዋል?
ሳምንት ጎንደር ላይ ፋሲል ከተማ በሲዳማ ቡና 3-1 በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ በመሀል ዳኝነት ያጫወተው ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ የዛሬውን ጨዋታ እንደሚመራው ታውቋል ።
ግምታዊ አሰላለፍ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)
ሮበርት ኦዶንካራ
ፍሬዘር ካሳ – ሳላዲን በርጊቾ – አስቻለው ታመነ – አበባው ቡታቆ
ያስር ሙገርዋ – ምንተስኖት አዳነ – አዳነ ግርማ
በሃይሉ አሰፋ – ሳላዲን ሰኢድ – አቡበከር ሳኒ
ደደቢት (4-4-2)
ክሌመንት አዞንቶ
ስዩም ተስፋዬ – አይናለም ኃይለ – አክሊሉ አየነው – ብርሃኑ ቦጋለ
ሽመክት ጉግሳ – አቤል እንዳለ– ስምሶን ጥላሁን – ኤፍሬም አሻሞ
ጌታነህ ከበደ – ዳዊት ፍቃዱ