ኢትዮጵያዊው አጥቂ ፍቅሩ ተፈራ ለደቡብ አፍሪካው የአብሳ ፕሪምየርሺፕ ተወዳዳሪ ለሆነው ሃይላንድስ ፓርክ ፈርሟል፡፡
ከባንግላዴሹ ሼክ ሩሴል ክለብ በ2016 ከተለያየ በኃላ ያለፉትን ወራት ክለብ ያልነበረው ፍቅሩ በስተመጨረሻም ለሃይላንድስ ፓርክ የአጭር ግዜ ውል መፈረሙን ሲቲዝን ድህገ ገፅ ዘግቧል፡፡ ፍቅሩ ለህንዱ የአንደኛ ዲቪዚዮን ክለብ መሃመዳን ጋር ያልተሳካ ድርድር ያደረገ ሲሆን ሃይላንድስ ፓርክ ከፕሪምየርሺፑ ላለመውረድ የሚያደርገውን ጥረት ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንደድህረ ገፁ ዘገባ ከሆነ ፍቅሩ የስድስት ወራት ውል ፈርሟል፡፡ የመጀመረያ ጨዋታውን ከፍሪ ስቴት ስታርስ ጋር በሳምንቱ መጨረሻ በኔድባንክ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፍቅሩ ክለቡ ላለውረድ በሚያደርገው ትግል የፊት መስመሩን እንደሚያጠነክርላቸው የክለቡ አሰልጣኝ ጎርደን ኢግሱንድ ገልፀዋል፡፡
ዴይሊ ሰን ኤግሱንድ ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ፍቅሩ ያለበት የአካል ብቃት ደረጃ ለወራት ክለብ አልባ የነበረ ቢሆንም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ “ፍቅሩ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ንቁ እና ብርቱም ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ 11 ግቦች ካስቆጠረበት የህንድ ሊግ ነው ወደ ደቡብ አፍሪካ የተመለሰው፡፡”
የቀድሞ የባፋና ባፋና እና ሱፐርስፖርት ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤግሱንድ ሲቀጥሉ “(ፍቅሩ) ኳስ በጥሩ መልኩ ይይዛል ኮሊንስ ምቤዙማን እንደዛው፡፡ ነገር ግን ኮሊንስ ለጨዋታዎች ብቁ ለመሆን ሁለት ሳምንታት ያስፈልጉታል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ግዜ የለንም፡፡ ጥሩ ተጫዋቾች አሉን ፍቅሩ ደግሞ ይበልጥ ጥንካሬን በፊት መስመሩ ላይ ይጨምርልናል፡፡”
ዛምቢያዊው አጥቂ ምቤዙማ ለሶስት ወራት በጉዳት ከሜዳ ርቆ ከባሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ወደ ልምምድ ተመልሷል፡፡ ለጨዋታ ብቁ ሆኖ አለመገኘቱ ግን ሃይላንድ ፓርክስን ወደ ፍቅሩ ፊቱን እንዲያዞር አድርጎታል፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወደ ሊጉ ያደገው ሃይላንድ ፓርክስ በመጣበት አመት እንዳይወርድ ይሰጋል፡፡ በሊግ ሰንጠረዡ በ17 ነጥብ 15ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ላለመውረድም ከአያክስ ኬፕታውን፣ ብሎምፍንቴን ሴልቲክ፣ ፍሪ ስቴት ስታርስ እና አዲስ አዳጊው ባሮካ ጋር እየተፋለመ ይገኛል፡፡
ፍቅሩ በደቡብ አፍሪካ ብቻ ለኦርላንዶ ፓይሬትስ፣ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ፣ ፍሪ ስቴት ስታርስ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶሪያ፣ ሜላኖ ዩናይትድ እና ቤድቬስት ዊትስ መጫወት ችሏል፡፡