በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳታፊ መሆን የቻለው ድሬዳዋ ከተማ የኢትዮጵያ ቡናው ዮሴፍ ዳሙዬ እና ቶማስ እሸቱን በውሰት ውል ማስፈረም ችሏል፡፡
በ2008 ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቅሎ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ድንቅ አቋም ያሳየው ዮሴፍ ከዛ ወዲህ የተጠበቀውን ያህል የመሰለፍ እድል ሳያገኝ ቀርቶ ወደ ድሬዳዋ ከተማ አምርቷል፡፡ በድሬዳዋ ከተማ እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ በሚያደርገው ቆይታም የተሻለ የመሰለፍ እድል ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ድሬዳዋ ከተማ ከዮሴፍ በተጨማሪ ቶማስ እሸቱን ከኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ የውሰት ውል አስፈርሟል፡፡ የቀድሞው የናሽናል ሴሜንት ተከላካይ በቡና ጥቂት የመሰለፍ እድል አግኝቶ ወደ ትውልድ ከተማው ተመልሷል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በዚህ የዝወውር መስኮት ሶስት ተጫዋቾችን በውሰት ለሌሎች ክለቦች ሰጥቷል፡፡ ከዮሴፍ እና ቶማስ በተጨማሪ ፍራኦል መንግስቱ ወደ ወላይታ ድቻ ማምራቱ የሚታወስ ነው፡፡