በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የአንደኛ ዙር ጨዋታዎች ኤስፔራንስ፣ ዋይዳድ ካዛብላንካ፣ አል አሃሊ እና ዩኤስኤም አልጀር ድል ሲቀናቸው ያንግ አፍሪካንስ በሜዳው ነጥብ ተጋርቷል፡፡
ዳሬ ሰላም ላይ የዛምቢያ ቻምፒዮኑን ዛናኮን ያስተናገደው ያንግ አፍሪካንስ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠረበት ግብ 1-1 ተለያይቷል፡፡ ሳይመን ሙሱቫ ሃያሉን የታንዛኒያ ክለብ ያንጋን መሪ ያረገች ግብ በመጀመሪያው አጋማሽ አስቆጥሯል፡፡ ካዋሜ አትራምስ በመጨረሻው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ዛናኮን ለመልሱ ጨዋታ የበላይነት እንዲወስድ አስችላለች፡፡ የአትራምስ ግብ ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል ያንጋዎች ጁቡቲያዊው ረዳት ዳኛ ላይ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ ያንጋ ወደ ምድብ ለመግባት የሚያደረግው ጥረት አሁን ላይ የከበደ ይመስላል፡፡
ባለሪከርድ አፍሪካ ቻምፒዮኑ አል አሃሊ የደቡብ አፍሪካውን ቤድቬስት ዊትስን 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፏል፡፡ የአል አሃሊን የድል ግብ ተከላካዩ አህመድ ሄጋዚ በሁለተኛው አጋማሽ አስቆጥሯል፡፡ ዊትስ በግብፅ ካስመዘገበው መልካም የሚባል ውጤት ምክንያት በመልሱ የካይሮው ሃያል ሊፈተን ይችላል፡፡
የቱኑዚያው ኤስፔራንስ የጊኒውን ሆሮያን 3-1 ቱኒዝ ላይ አሸፏል፡፡ ፈርጃኒ ሳሲ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ሲያደርግ በተከላካዮች ስህተት የተገኘችውን ኳስ ተጠቅሞ ሜንዶ እንግዶቹን አቻ አድርጓል፡፡ ሳሲ ሁለተኛ ግብ ሲስቆጥር ፋክረዲን ቤን የሱፍ ሶስተኛውን ግብ አክሎ ከ2013 ወዲህ በቻምፒየንስ ሊግ ስኬትን ማስመዝገብ ለከበደው ኤስፔራንስ ማሸነፍ ትልቁን ሚናን ተወጥተዋል፡፡ ሆሮያዎች በተደጋጋሚ በሁለተኛው አጋማሽ ሲያደርጓቸው የነበሩት አደገኛ ሙከራዎች አልተሳኩም እንጂ ተጨማሪ ግብ የማግኘት እድል ነበራቸው፡፡
የ2015 የቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚ የአልጄሪያው ዩኤስኤም አልጀር የቡርኪናፋሶን ሪያል ክለብ ካዲዮጎን 2-0 አሸንፏል፡፡ እንግዶቹ በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላካሉም ይሁን በማጥቃቱ ጠንክረው መቅረባቸው የአልጀርሱን ክለብ አጣብቂኝ ውስጥ ከተው ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ከባለሜዳዎቹ ይልቅ አስደንጋጭ ሙከራዎቹን ማድረግ የቻሉት ካዲዮጎዎች ነበሩ፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉት ዩኤስኤም አልጀሮች በተቀያሪው አሚር ሳዮድ እና ኦሳማ ዴርፋሎ ግቦች ታግዘው 2-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ሳዮድ እና አብዱልቃድር ሜዛይን ለባለሜዳዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ ቁልፍ ሚናን ተወጥተዋል፡፡ ካዲዮጎዎች በአልጀርስ ካሳዩት መልካም እንቅስቃሴ አንፃር ኦጋዱጉ በሚኖረው የመልስ ጨዋታ የአልጄሪያው ክለብ ፈተና ይጠብቀዋል፡፡
የ2016 ቻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ዋይዳድ ካዛብላንካ የጋቦኑን ሞናናን በሜዳው 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፏል፡፡
ጨዋታዎቹ ዛሬም በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች በሚደረጉ 10 ጨዋታዎች ይቀጥላሉ፡፡ የኢትዮጵያው ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ከሰዓት የኮንጎ ሪፐብሊክን ኤሲ ሊዮፓርድሰን ይገጥማል፡፡
ዓርብ ውጤት
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) 2-1 ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ (ዩጋንዳ)
ቅዳሜ ውጤቶች
ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) 1-1 ዛናኮ (ዛምቢያ)
ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ (ቱኒዚያ) 3-1 ሆሮያ (ጊኒ)
አል አሃሊ (ግብፅ) 1-0 ቤድቬስት ዊትስ (ደቡብ አፍሪካ)
ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ) 1-0 ሞናና (ጋቦን)
ዩኤስኤም አልጀር (አልጄሪያ) 2-0 ሪያል ክለብ ዱ ካዲዮጎ (ቡርኪናፋሶ)
እሁድ
14፡30 – አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ) ከ ፋት ዩኒየን ስፖርት (ሞሮኮ)
15፡00 – ክለብ ፌሬቫያሮ ደ ቤይራ (ሞዛምቢክ) ከ ባራክ ያንግ ኮንትሮለር (ላይቤሪያ)
15፡30 – ኤሲ ሊዮፓርድስ ደ ዶሊሲ (ኮንጎ ሪፐብሊክ) ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ኢትዮጵያ)
15፡30 – ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) ከ ካፕስ ዩናይትድ (ዚምባቡዌ)
15፡30 – ኮተን ስፖርት (ካሜሮን) ከ ሲኤንኤፒኤስ ስፖርት (ማዳጋስካር)
16፡00 – ሪቨርስ ዩናይትድ (ናይጄሪያ) ከ ኤል ሜሪክ (ሱዳን)
16፡00 – ጋምቢያ ፖርትስ ኦቶሪቲ (ጋምቢያ) ከ ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)
18፡00 – ዛማሌክ (ግብፅ) ከ ኢንጉ ሬንጀርስ ኢንተርናሽናል (ናይጄሪያ)
18፡00 – ኤቷል ደ ሳህል (ቱኒዚያ) ከ ኤኤስ ደ ታንዳ (ኮትዲቯር)
20፡00 – አል ሂላል (ሱዳን) ከ ኤኤስ ፖር ሉዊ 2000 (ሞሪሺየስ)