ፋሲል ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና | ቀጥታ የፅሁፍ ስርጭት

 FT   ፋሲል ከተማ   1-4   ኢትዮጵያ ቡና  

67′ ኤዶም ሆሮሶውቪ (P) || 36′ ኤልያስ ማሞ፣ 50′ ሳሙኤል ሳኑሚ፣ 61′ አስቻለው ግርማ፣ 89′ ጋቶች ፓኖም


ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


90′ ተጨማሪ ሰዐት – 2 ደቂቃ


89′ ጎልልል!!!!

ኢትዮጵያ ቡና በጋቶች ፓኖም አማካኝነት አራተኛውን ግብ አግኝቷል።

hr

85′ የተጨዋች ለውጥ – ኢትዮጵያ ቡና 

ያቡን ዊልያም ገብቶ ሳሙኤል ሳኑሚ ወጥቷል።

hr

82′ የተጨዋች ለውጥ ቡና 

ኤልያስ ማሞ ወጥቶ መስዑድ መሀመድ ገብቷል።


81′ ጨዋታው ተቋርጦ ከተጀመረ በኋላ በተጨዋቾቹ ላይ የሚታየው የመጫወት ፍላጎት የተቀዛቀዘ ሆኗል።


80′ የተጨዋች ለውጥ – ኢትዮጵያ ቡና 

አስቻለው ግርማ ወጥቶ አማኑኤል ዮሐንስ ገብቷል። 


78′ ኤልያስ ማሞ የዮሐንስን ሽኩርን መውጣት አይቶ ከርቀት የመታው ኳስ ለጥቂት ወደውጪ ወጥቷል። 


74′ ቢጫ – ፋሲል ከተማ 

ፍቅረሚካኤል አለሙ እያሱ ታምሩ ላይ በሰራው ያልተገባ አጨዋወት የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል።


72′ የተጨዋች ለውጥ – ፋሲል ከተማ 

ፍቅረሚካኤል አለሙ ገብቶ ሄኖክ ገምቴሳ ወጥቷል።


67′ ጎልልልል!!!!

ኤዶም ሆሮሶውቪ ፍፁም ቅጣት ምቱን ወደግብ ቀይሮታል።


66′ ፍፁም ቅጣት ምት ለፋሲል ከተማ ተሰጥቷል።


65′ ጨዋታው በሚገርም የደጋፊ ድባብ ቢጀመርም በአሁን ሰአት አብዛኛው ተመልካች ሜዳውን ትቶ ወጥቷል።


ጨዋታው ከ36 ደቂቃ መቋረጥ በኋላ ከቆመበት 62ኛው ደቂቃ  አንስቶ ተጀምሯል።


ስቴዲዮሙ ውስጥ ከፍተኛ ረብሻ ተነስቷል፤ ጨዋታውም እስካሁን አልቀጠለም።


62′ ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ የእለቱ ዳኛ ጨዋታው በድጋሚ አቋርጠውታል።


61′ ጎልልልል !!!!

አስቻለው ግርማ የኢትዮጵያ ቡናን 3ኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል።


60′ ፋሲሎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ወደ ጎል ለመቅረብ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።


56′ በስቴዲዮሙ በካታንጋ አቅጣጫ በኩል በተፈጠረ ግርግር ዳኛው ጨዋታውን አቋርጠው አሁን በድጋሚ አስጀምረዋል።


53′ በስቴዲዮሙ የሚገኙ የኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች ቡዳናቸው እያስመዘገበ ባለው ውጤት ደስታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።


50′ ጎልልልል !!!!

ሳሙኤል ሳኑሚ ኢትዮጵያ ቡና ልዩነቱን ያሰፋበትን ግብ አስቆጥሯል።


ተጀመረ !

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጀምሯል።



እረፍት !

የመጀመሪያው አጋማሽ በኢትዮዽያ ቡና 1 – 0 መሪነት ተጠናቋል።


44′ ቢጫ – ኢትዮጵያ ቡና 

ወንድይፍራው ጌታሁን የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል።


43′ የተጨዋች ለውጥ – ፋሲል ከተማ 

ያሬድ ባየህ ወጥቶ ታደለ ባይሳ ገብቷል።


41′ ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ ፋሲሎች ተጭነው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ ቡናዎች አፈግፍገው በመከላከል ላይ ይገኛሉ።


36′ ጎልልልል !!!!

ኢትዮዽያ ቡና በኤልያስ ማሞ አማካኝነት መሪ የሆነበትን ግሩም ግብ አስቆጥሯል።


34′ አስቻለው ግርማ  ከርቀት የመታውን ቅጣት ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ጎን ወጣበት።


30′ አፄዎቹ በአብዱራህማን ሙባረክ ቡናዎች በአስቻለው ግርማ አማካኝነት እየፈጠሩት ያለው የማጥቃት እንቅስቃሴ በተከላካዮች ብስለት በተሞላበት መንገድ እየመከነባቸው ይገኛል።


22′ ጨዋታው ግለቱን ጠብቆ በደጋፊዎች ህብረ ዝማሬ ታጅቦ በሁለቱም በኩል በሚደረግ የማጥቃት አጨዋወት ቀጥሎ ይገኛል።


16′ ቁጥሩ በርካታ ለሆነው በአፄ ፋሲል ስቴዲየም ለታደመው ተመልካች የሚመጥን ቁጭ ብድግ የሚያደርግ ግሩም ጨዋታ እየተመለከትን እንገኛለን።


14′ አስቻለው ግርማ የሞከረውን ኳስ የግቡ አግዳሚ መለሰበት፤ እረፍት የሌለው የሚገርም ጨዋታ።


11′ በአንድ ደቂቃ ልዮነት አብዱራህማን ሙባረክና ኤርሚያስ ሀይሉ ግልፅ የጎል እድል አመከኑ።


9′ ቢጫ!  ፋሲል ከተማ 

ዮሐንስ ሽኩር የዳኛን ውሳኔ በመቃወም የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል።


7′ ኤልያስ ማሞ በግምት 30 ሜትር ርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት መትቶ ዮሐንስ ሽኩር አዳነበት።

 ጨዋታው  ባማረ የኳስ ፍሰት በማራኪ እንቅስቃሴ  በሁለቱም በኩል ተጋግሎ ቀጥሏል።


3′ ፋሲሎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት የፈጠሩትን የጎል እድል ኤፍሬም አለሙ በሚገርም ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።


ተጀመረ !  

ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡናው ሳሙኤል ሳኑሚ አማካኝነት ተጀምሯል።


08:55 – ሁለቱ ቡድኖች በእለቱ ኮሚሽነር እየተመሩ በሚገርም የደጋፊዎች ድባብ ታጅበው ወደ ሜዳ እየገቡ ይገኛሉ።


የፋሲል ከተማ አሰላለፍ

93 ዮሀንስ ሽኩር

13 ሰኢድ ሁሴን – 3 ሱሌይማን አህመድ – 16 ያሬድ ባየህ – 21 አምሳሉ ጥላሁን

26 ኄኖክ ገምቴሳ – 17 ይስሀቅ መኩርያ – 25 ኤፍሬም አለሙ

99 ኤርሚያስ ኃይሉ – 9 ኤዶም ኮድዞ – 18 አብዱራህማን ሙባረክ


ተጠባባቂዎች

31 ቴዎድሮስ ጌትነት

7 ፍጹም ከበደ

5 ታደለ ባይሳ

4 ፍቅረሚካኤል አለሙ

27 ሰለሞን ገብረመድህን

20 ናትናኤል ጋንጂላ

10 ሙሉቀን ታሪኩ


የኢትዮጵያ ቡና አሰላለፍ

99 ሀሪሰን ሄሱ

15 አብዱልከሪም መሀመድ – 5 ወንድይፍራው ጌታሁን – 16 ኤፍሬም ወንድወሰን – 13 አህመድ ረሺድ

25 ጋቶች ፓኖም – 19 አክሊሉ ዋለልኝ – 9 ኤልያስ ማሞ

24 አስቻለው ግርማ – 11 ሳሙኤል ሳኑሚ – 14 እያሱ ታምሩ


ተጠባባቂዎች

32 ዮሃንስ በዛብህ

3 መስኡድ መሀመድ

28 ያቡን ዊልያም

21 አስናቀ ሞገስ

18 ሳለአምላክ ተገኝ

4 ኢኮ ፊቨር


08:45 – ሁለቱም ቡድኖች ልምምዳቸውን በተገቢ ሁኔታ አጠናቀው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


08:35 – ሁለቱም ቡድኖች ወደ ሜዳ በመግባት የቅድመ ጨዋታ ሰውነት ማሟሟቂያ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ።


የእለቱን ጨዋታ ፌደራል አልቢትር ጌቱ ተፈራ በዋና ዳኛነት የሚመራው ይሆናል።


08:30 – የአፄ ፋሲል ስቴዲዮም በፋሲል ከተማ ደጋፊዎች  ከአፍ እስከ ገደቡ ሞልቷ፤ ያለው ድባብ እጅግ የሚገርም ነው። በአንፃሩ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች ለስቴዲዮሙ ሌላ ተጨማሪ ድምቀት ሆነዋል።


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር አመቱ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት የጀመሩ ሲሆን አብዛኞቹ ጨዋታዎችም ዛሬ የሚደረጉ ይሆናል ። ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል ጎንደር ላይ ፋሲል ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረትብ ስቧል። ሶከር ኢትዮጵያም ጨዋታውን በቀጥታ የፅሁፍ ስርጭት ጨዋታውን ወደ እናንተ ታደርሳለች፡፡ ጨዋታው እስኪጀምር ድረስ ስለጨዋታው ያሰናዳነውን እያነበባችሁ እንድትጠባበቁ እንጋብዛለን፡፡


ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ – በዮናታን ሙሉጌታ

የመጀመሪያው ዙር ሲጠናቀቅ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ የጨረሰው ፋሲል ከተማ በወቅቱ በ24 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ከነበረው ኢትዮጵያ ቡና በሁለት ነጥቦች ከፍ ብሎ ነበር ያጠናቀቀው ። ሆኖም ግን በሁለተኛው ዙር በሲዳማ ቡና እና በወላይታ ድቻ የደረሰበት ያልታሰበ ተከታታይ ሽንፈት ቡድኑን ወደ ስድተኛ ደረጃ እንዲወርድ አስገድዶታል። ከደደቢት ጋር አቻ የተለያየው እና መከላከያን ያሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ አራት ነጥቦችን አግኝቶ በ28 ነጥቦች በተራው የዛሬውን ተጋጣሚውን በሁለት ነጥቦች በልጦ በሊጉ አራተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል። ይህ የነጥብ መቀራረብ እና በደረጃ ሰንጠረዡ ቦታ የመለዋወጥ ሂደትም ጨዋታውን ተጠባቂ ያደርገዋል ። በውጤቱም ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ አናት መሪ ወደሆኑት ሶስት ክለቦች ለመድረስ ወሳኝ ፍልሚያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከውጤት እና ደረጃ መቀራረቡ በላይ የጨዋታውን ተጠባቂነት የሚያጎላው ግን የሁለቱ ክለቦች የደጋፊ ሀብታምነት ነው። የፕሪምየር ሊጉ ያለፉት አመታት ዝቅተኛ የደጋፊዎች ቁጥር ዘንድሮ ተሻሽሎ ሲታይ የፋሲል ከተማ ሊጉን መቀላቀል እንደ ዋና ነጥብ የሚነሳ ነው የሚሆነው ። ከሜዳውጪ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ተዟዙረው በመደገፍ ለጨዋታዎች ድምቀት የሆኑት የአፄዎቹ ደጋፊዎች በሜዳቸው ላይ ቡድኑ ተጋጣሚዎቹን በሚያስተናግዳቸው ጨዋታዎች ስቴድየሙን ብቻ ሳይሆን ከተማዋንም እግር ኳሳዊ ውበት ሲያላብሷት ይታያል። ከዚህ በተጨማሪ ለተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች የሚያደርጉት አቀባበል እና በጨዋታ ወቅት ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ከመሀላቸው በተወጣጡ በጎ ፍቃደኞች በኩል የሚያደርጉት እንቅስቃሴም ይበል የሚያሰኝ ነው ። ዛሬ ደግሞ ጎንደር ላይ በሀገሪቱ በርካታ ደጋፊዎች ካሏቸው ክለቦች መሀከል አንዱ የሆነውን ኢትዮጵያ ቡናን ማስተናገዳቸው ጨዋታው በተለየ ድባብ እንደሚካሄድ እርግጠኛ የሚያደርግ ነው። ሳምንት ቡድኑ መከላከያን በረታበት ጨዋታ በከፍተኛ ቅደስታ ከ አዲስ አበባ ስታድየም የወጡት የቡናማዎቹ ደጋፊዎች ዛሬም ወደጎንደር በማቅናት የተለመደ ሞቅ ያለ ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የጨዋታ አቀራረብ

ሁለቱም ክለቦች ቡድኖቻቸውን በተመሳሳይ የ 4-3-3 ቅርፅ ወደሜዳ ይዘው ሲገቡ ይስተዋላል። በፋሲል ከተማ በኩል ይህ ቅርፅ ኳስን ተቆጣጥሮ እና የመሀል ሜዳ የበላይነትን አግኝቶ ጨዋታዎችን ለማድረግ ሲፈልግ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹን ቁጥር በመጨመር ወደ 4-1-4-1 የተጨዋቾች አደራደር ሲያደላ ይስተዋላል። በዚህም ጨዋታ ላይ በመሀል ማዳ ላይ የሚኖረው ፉክክር የሚያጓጓ ነው ። የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍል በተመሳሳይ የአማካይ መስመር ተጨዋቾች ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ማድረጉ ወደ ጥሩ ውህደት የወሰደው ይመስላል። የጋቶች ፓኖምን የተከላካይ አማካይነት ሚና የተረከበው  አክሊሉ ዋለልኝ ወጥ አቋም ጥሩ መግባባት ከሚታየበት የኤልያስ ማሞ እና ጋቶች ፓኖም ጥምረት ጋር ተዳምሮ ለቡናማዎቹ ጥንካሬን አላብሷቸዋል ። በመከላከያው ጨዋታ የታየው ይቡና የመሀል ክፍል የበላይነት ዛሬ ጎንደር ላይ ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጪ በተጋጣሚ ተጨዋታዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ከሚያሳድሩት ፋሲሎች ጋር መገናኘቱ ጊዜ እና ክፍተትን ለሚፈልገው አጨዋወቱ ከባድ ተቃርኖ እንደሚፈጥርበት ማሰብ ይቻላል። ከመስመር አጥቂዎቹ እገዛን የሚያገኘው በሔኖክ ገምተሳ የሚመራው የፋሲሎች የመሀል ክፍል በፍጥነት ወደተጋጣሚው ሜዳ በመግባት የመጨረሻ ኳሶችን ለአጥቂዎች በማድረስ እንዲሁም ወደመከላከል በሚደረግ ሽግግር የተሻለ ሽፋን ለተከላካዮቹ ከመስጠት ባለፈ ተጋጣሚዎችን ጫና ውስጥ በመክተት ኳስ የማቀበያ ክፍተቶችን እንዳገኙ በማድረግ ጥንካሬው ይነሳል። ይህ ጨዋታ ኳስን ከኋላ ጀምሮ በመመስረት ከሚጫወት እንዲሁም  የመልሶ ማጥቃት እድሎች ሲኖሩ የፈጣን የመስመር አጥቂዎቹን ብቃት በመጠቀም ወደፊት ከሚሄድ ቡድን ጋር በመሆኑ የፋሲሎች የመከላከል ሽግግር ስኬታማነት ለሚኖራቸው ውጤት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቡና  የሁለቱ የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ሚና የፋሲል ከተማ ጠንካራ ጎን ከሆኑት የመስመር አጥቂዎች ጋር የሚኖረው ትንቅንቅ በወሳኝነት ይነሳል ። በሽግግሮች ወቅት በሜዳው ሁለት ክንፎች የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ማን ቀድሞ ይጠቀምባቸዋል የሚለውም ጥያቄ መልስ ጨዋታውን በእጅጉ የመወሰን አቅም ይኖረዋል።

የቅርብ ጊዜ አቋም

ፋሲል ከተማ  | ተሸ – አሸ –  አሸ – ተሸ – ተሸ

አፄዎቹ ሁለተኛው ዙር እንደመጀመሪው ዙር መጨረሻ የሆነላቸው አይመስልም። የደረሰባቸው ሁለት ተከታታይ ሽንፈትም ከዋንጫው ፉክክር በመጠኑ እንዲርቁ አድርጓቸዋል። የመጀመሪያው ዙር ሲገባደድ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳያስተናግድ ያሸነፈው ፋሲል አሁን ግን በሁለቱ ጨዋታዎች አምስት ግቦች ከመረቡ ላይ አርፈውበታል።

ኢትዮጵያ ቡና  | አሸ – አሸ –  አቻ –  አቻ – አሸ

ኢትዮጵያ ቡና በ9ኛው ሳምንት በወልድያ ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ እስካሁን ድረስ ሌላ ሽንፈት አልገጠመውም ። ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ በኋላም ቢሆን በሁለት ጨዋታዎች 4 ነጥቦችን አስመዝግቧል ። ቡድኑ መከላከያን 4 ለ 0 የረታበት የመጨረሻ ጨዋታም ዘንድሮ ቡድኑ በሰፊ የግብ ልዩነት የያሸነፈበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል።

ግንኙነቶች

ፋሲል ከተማ በቋሚነት በፕሪምየር ሊጉ መሳተፍ የጀመረው ዘንድሮ በመሆኑ ሁለቱ ቡድኖች በቅርብ አመታት ውስጥ እርስ በእርስ የመገናኘት አጋጣሚ አልነበራቸውም። ሆኖም በ 2000 ዓ.ም በክለቦች እና በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ መሀከል በተፈጠረው ክፍፍል ወቅት ፋሲል ከተማ ከወቅቱ የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ጋር በመቀላቀል መወዳደሩ የሚታወስ ነው። በዚያ  ወቅት አዲስ አበባ ላይ የተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት በ 1-1 አቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። በዘንድሮ ውድድር ሶስተኛ ሳምንት ላይ ሲገናኙም ፋሲል ከተማ በኤርሚያስ ኃይሉ የ49ኛ ደቂቃ ጎል ኢትዮጵያ ቡናን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መርታቱ ይታወሳል።

ጉዳት እና ቅጣት

ሁለቱም ክለቦች ከጉዳት ነፃ ሆነው ጨዋታውን የሚያደርጉ ሲሆን ፋሲል ከተማዎች ከደደቢት በውሰት ያገኙት አጥቂው አቤል ያለው አምስተኛ የቢጫ ካርድ በመመልከቱ ሳቢያ ዛሬ ለክለቡ አገልግሎት የሚሰጥ አይሆንም።  በተቃራኒው ኢትዮጵያ ቡና ከቅጣት መልስ የመሀል ተከላካዩን ኤፍሬም ወንደሰንን የሚጠቀም ይሆናል።

ምን ተባለ?

አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ

” በሁለቱም የሲዳማ ቡና እና የወላይታ ድቻ  ጨዋታ ላይ ብንሸነፍም መልካም ጎኖች ነበሩን ። የጎል እድል በሚገባ ፈጥረን ተጫውተናል ። ሆኖም ያገኘናቸውን የጎል እድሎች የመጠቀም ችግር ነበረብን ። ጥሩ ጎናችንን አጠናክረን ያሉብን ክፍተቶች አርመን እንቀርባለን ።

” ከኢትዮዽያ ቡና ጋር በሚኖረን ጨዋታ በማሸነፍ በቡድኑ ውስጥ መነሳሳትን እንፈጥራለን ። ካስታወሳቹ በመጀመርያው ዙር ላይ ከሜዳችን ውጭ በሲዳማ ቡና ተሸንፈን ኢትዮዽያ ቡናን ካማሸነፍ በኋላ ነበር በልጆቼ ላይ ተነሳሽነት የተፈጠረው ። አሁንም ከሁለት ጨዋታ ሽንፈት በኋላ በዛሬው ጨዋታ በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት መንፈስ የማንመለስበት ነገር የለም ። ”

አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ

“እያንዳንዱ ጨዋታ ለእኛ አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ለዋንጫ ለምናደርገው ፉክክር የራሱ አስተዋፆ አለው። ለሁሉም ጨዋታ የምንሰጠው ትኩረት አንድ በመሆኑ ከፈሲል ጋር  ለሚኖረው ጨዋታ የተለየ ዝግጅት አላደረግንም ያም ቢሆን ጎንደር የመጣነው ለማሸነፍ ብቻ ነው። በጥንቃቄ ተጫውተን ጥሩ ውጤት አስመዝግበን እንመለሳለን። ቡድኔ ውስጥ በየጨዋታው  የተነሳሽነት እና የማሸነፍ ፍላጎት ከፍተኛ ነው ይህ በጣም ጥሩ ነገር ነው። በመጀመርያው ዙር በፈሲል መሸነፋችን ይታወቃል ። ሆኖም ያሚፈጥርብን ተፅኖ የለም ይበልጥ ውጤቱን ቀልብሰን እንድናሸንፍ መነሳሳትን ይፈጥርብናል እንጂ።”

ጨዋታውን  ማን ይመራዋል ?

ፌደራል ዳኛ ጌቱ ተፈራ ይህን ተጠባቂ ጨዋታ በመሀል ዳኛነት ይመራዋል ። ሆኖም አልቢትሩ በሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ የዳኘው ጨዋታ በመጀመሪያው ዙር አራተኛ ሳምንት ላይ ፋሲል ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደበትን ጨዋታ መሆኑ እና ከዛ በኋላ ሌላ ጨዋታ አለማድረጉ ሁኔታውን አነጋጋሪ አድርጎታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *