በ18ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የደቡብ ደርቢ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ሀዋሳ ከተማን አስተናግዶ ያለምንም ግብ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡
ተመጣጣኝ ፍክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ኳስ ይዘው ለመጫወት ቢምክሩም ዠሜዳው ለእንቅስቃሴ ምቹ አለመሆን እክል ሲፈጥር ተመልክተናል፡፡ ጨዋታው እንደተጀመረ አስጨናቂ ሉቃስ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ገብረሚካኤል ያዕቆብ ወደ ግብ ሞክሮ ወደ ውጭ የወጣችበት የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር፡፡ በ8ኛው ደቂቃ የሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ ከግብ ክልል ውጭ ኳስ ነክቷል በሚል የአርባምንጭ ከተማ ደጋፊዎች ዳኛው ላይ ተቃውሞ ያሰሙበትም በጨዋታው መጀመርያ ከታዩ ክስተቶች መካከል ነበር፡፡
ታፈሰ ሰለሞን ያሻገረውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ዳግም ለመድሀኔ ታደሰ አሾልኮ አቀብሎት ሳይጠቀምበት የቀረው ፤ የአርባምንጩ አምበል አማኑኤል ጎበና ያሻገረውን ገ/ሚካኤል ያዕቆብ ከወንድሜነህ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ወንድሜነህ ዘሪሁን ሳይደርስበት የቀረው በሁለቱ ቡድኖች የታዩ ሌሎች ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡
በ29ኛው ደቂቃ ጃኮ አራፋት በሀዋሳ በኩል በጉዳት መውጣቱ የሀዋሳ ከተማ የማጥቃት እንቅስቃሴ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ የሀዋሳ ታፈሰ ሰለምን ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የሞከረውን ኳስ አንድነት አዳነ ያወጣበት ፤ መድሀኔ ታደሰ ዳግም ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ጃክሰን ፊጣ ያወጣበት ሀዋሳ በመጀመሪያው አጋማሽ መሪ ሊሆንባቸው የሚችላቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ አርባምንጭ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥሮ ተጫውቷል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ያጡትን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በሁለተኛው አጋማሽ መመለስ ችለዋል፡፡ በአመለ ሚሊኪያስ ተቀይሮ የገባው ፀጋዬ አበራ በ58 ተኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂው ሶሆሆ ጋር ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ አርባምንጭ 3 ነጥብ የሚያገኝበት አጋጣሚም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አማኑኤል ጎበና በረጅሙ ያሻገረውን ፀጋዬ አበራ በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታም ተደጋጋሚ ሙከራወችን ሲያመክን የነበረው የሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ሱሆሆ ሜንሳ የያዘበትም የሚጠቀስ ሙከራ ነበር፡፡
ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ለመሄድ ችሏል፡፡ አስጨናቂ ሉቃስ ከቅጣት ምት በቀጥታ መቶ የተመለሰውን ታፈሰ ሰለሞን ወደ ግብ ቢመታም የአርባምንጭ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል፡፡
በጉዳት አርባምንጭን ሳያገለግል የቆየው እንዳለ ከበደ ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ ተንቀሳቅሷል፡፡ እንዳለ ከወንድሜነህ ጋር ተቀባብሎ ያሻገረውንም ገብረሚካኤል ያዕቆብ ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡
ይሁንና ጨዋታው አልፍ አልፍ ከሚታየው የኳስ እንቅስቃሴ ውጭ ሳቢ ያልሆነ ጨዋታ ሆኖ ያለ ግብ በአቻ ውጤተት ተፈጽሟል፡፡ በአንፃሩ የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች ለስታዲየሙ ድምቀት ነበሩ፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ፓውሎስ ፀጋዬን የአርባምንጭ ደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውም አሰምተዋል፡፡
አስተያየቶች
ጳውሎስ ጸጋዬ
በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ ነበርን፡፡ ነገር ግን በውጤቱ ደስተኛ አደለውም፡፡ በቀጣይ አሻሽለን እንቀርባለን፡፡ ከሜዳችን ውጭ ያለንን ጥሩ ውጤት በሜዳችን መድገም አልቻልንም፡፡ ከጊዮርጊስ ሽንፈት በኃላ በፍጥነት ከዚህ ውጤት ማገገም ችለናል፡፡ ሆኖም ከወልዲያ ስንመጣ በመኪና ስለመጣን ድካም ተጫዋቾቼ ላይ ታይቷል፡፡ በሁለተኛው ዙር ባሳደግናቸው 3 ተጫዋቾች እስከ አራተኛ ደረጃ ውስጥ ገብተን እናጠናቅቃለን፡፡
ውበቱ አባተ
” ከባድ ጨዋታ ነው፡፡ በተለይ ፀሀዩ እና አየሩ አስቸጋሪ ነበር ፤ ሙቀቱም እንደዛው፡፡ እኛ ከዕረፍት በፊት ጥሩ ነበርን፡፡ ማግባትም ይኖርብን ነበር፡፡ ነገር ግን የትም ሜዳ ተጫወት ነጥብ ያስፈልገናል፡፡ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ግብ አልተቆጠረብንም ፤ ይህም ጠንካራ ጎናችን ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ የአየር ፀባይ አቻ መውጣታችን አያስከፋም በልጆቼ እንቅስቃሴም ደስተኛ ነኝ፡፡