ታሪክ ተሰራ ! 

ፈረሰኞቹ የዘመናት ህልማቸውን እውን አድርገዋል

በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ወደ ዶሊሴ አቅንቶ ምንተስኖት አዳነ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፎ የተመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው የመልስ ጨዋታ በሰልሀዲን ሰኢድ ሁለት ግቦች ኤሲ ሊዮፓርድስን በድምር ውጤት 3-0 በማሸነፍ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ለመጀመሪያ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ወደ ምድብ ድልድል መግባት የቻለ ቡድን በመሆን አይረሴ ታሪክን ማስቀመጥ ችሏል፡፡

ፈረሰኞቹ ባሳለፍነው እሁድ ግቧን ያስቆጠረውና ከሜዳ በቀይ ካርድ የተሰናበተውን ምንተስኖት አዳነን በአዳነ ግርማ ከተኩት ውጪ ባሳለፍነው እሁድ የተጠቀሙበትን ተመሳሳይ የመጀመርያ 11 ተጫዋቾች ይዘው ነበር ጨዋታውን የጀመሩት፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ከተከላካይ በቀጥታ ወደፊት በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች በቶሎ ወደፊት ለመድረስ ጥረት ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች በተለይም የመሀል ተከላካዮ ሰልሀዲን በርጌቾ በተደጋጋሚ ከትኩረት ማነስ በመነጨ ስህተቶች ቢሰራም የቡድኑ አጋሮቹ ስህተቶቹ አደጋ እንዳይፈጥሩ አድርገዋቸዋል፡፡ በአንጻሩ ኤሲ ሊዮፓርድሶች የምእራብ አፍሪካ ቡድኖች በሚታወቁበት የመስመር አጨዋወት ወደ ግራ መስመር ባደላ መልኩ በግራ መስመር ተከላካያቸው በኩል በተደጋጋሚ ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡

በ15ኛው ደቂቃ ላይ የኤሲ ሊዮፓርድሱ ግብጠባቂ ሉቱኑ በረጅሙ ሊለጋ የነበረውን ኳስ ሰልሀዲን ሰኢድ ተደርቦ በማስቆጠር የፈረሰኞቹን እድል ያሰፋችውን የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ በተደጋጋሚ ሊዮፓርድሶች በጨዋታው ጠንካራ የማጥቃት መሰንዘሪያ በነበረው የግራ መስመራቸው በኩል የቅዱስ ጊዮርጊሱን የቀኝ መስመር ተከላካይ የሆነውን ፍሬዘር ካሳ በተደጋጋሚ ቡድኑ ኳስ በሚያጣበት ጊዜ በሚኖረው የ4-5-1 ቅርፅ መሠረት ከሱ ፊት ከሚገኘው በሀይሉ አሰፋ በቂ የሆነ እገዛ ባለማግኘቱ በተደጋጋሚ 1ለ1 ከተቃራኒ ቡድን የመስመር ተጫዋቾች ጋር እየተገናኘ በቀላሉ ኳሶች ወደ መሀል ማሻማት ችለው ነበር፡፡ ነገርግን ኳሶቹ እምብዛም አደጋ መፍጠር አልቻሉም፡፡ 

በተቃራኒው ሊዮፓርድሶች ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚያደርጉት ሽግግር እጅግ የዘገመ በመሆኑ መነሻነት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ እጅግ በርካታ እድሎችን ቢያገኙም መጠቀም አልቻሉም፡፡ ከነዚህም መካከል በ19ኛው ደቂቃ ላይ ሰልሀዲን ሰኢድ ከቀኝ መስመር አብዱልከሪም ኒኪማ ያሻማለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ ቋሚ የመለሰበት እንዲሁም በ45ኛው ደቂቃ ሰልሀዲን ሰኢድ ከአቡዱልከሪም ኒኪማ የተቀበለውን ኳስ እራሱ ማስቆጠር ሲችል ለበሀይሉ አሰፋ አቀብሎት ያመከኗት ኳስ ተጠቃሽ ነበሩ፡፡ ከነዚህም በተጨማሪ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው አጋማሽ ከተጋጣሚያቸው ተሽለው ቢገኙም ያገኟቸውን በርካታ የግብ እድሎችን ግን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሜዳ ላይ ከነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ይልቅ ከሜዳ ውጪ የነበረው የፈረሰኞቹ ደጋፊዎች ድባብ እጅግ የሚያስደምም ነበር፡፡

በዚህ አጋማሽ አበባው ቡጣቆ ከግራ መስመር አቅጣጫ ያሻማውን ኳስ አዳነ ግርማ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ ከወጣበት ኳስ ውጪ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ይህ ነው የሚባል የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም፡፡ በአመዛኙም ውጤቱን ለማስጠበቅ በሚመስል በብዙ አጋጣሚዎች ወደ ኃላ አፈገግፍገው ሲጫወቱ ተስተውሏል፡፡ በአንጻሩ ለማለፍ ከሁለት በላይ ግቦች ያስፈልጋቸው የነበሩት ኤሲ ሊዮፓርዶች ከመጀመሪያው በተሻለ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ ቢችሉም ግቦችን ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ጨዋታው ሊገባደድ ሲል በጭማሪ ሰአት የማእዘን ምት ለመሻማት የኤሲ ሊዮፓርድስ ተጫዋቾች ሙሉ በሙሉ ግብ ጠባቂውን ጨምሮ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል መሄዳቸውን ተከትሎ በቀላሉ ተገጭቶ የተመለሰውን የማእዘን ምት ኳስ ሰልሀዲን ሰኢድ ከራሱ የግብ ክልል አንስቶ እየገፋ በመሄድ የፈሰኞቹን ድል ያረጋጠችውን ጎል አስቆጥሮ የቡድኑን ደጋፊዎች ወደ ወሰን የሌለው የደስታ ስሜት ውስጥ መክተት ችሏል፡፡

የጨዋታውን መጠናቀቅ ያበሰረችውን ፌሽካ በእለቱ ጨዋታውን የመሩት ሱማሊያዊው አልቢትር ካሰሙ በኃላ በስታዲየሙ የነበረው የደስታን ስሜት ቃላቶች ከሚገልፁት በላይ ልዩ የነበረ ሲሆን የክለቡ የበላይ ጠባቂ የሆኑት አቶ አብነት ገብረመስቀልን ጨምሮ የቡድኑ አመራሮች እና ተጫዋቾች በከፍተኛ ሆኔታ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ደስታቸውን ሲገልፁ ተስተውሏል፡፡ በዚህ ውጤት መሠረትም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ የምድብ ድልድል ውስጥ የገባ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ክለብ በመሆን ታሪክ መስራት ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *