የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዛሬ በተለያዩ ከተሞች ቀጥሎ ሲውል ወልድያ እና ደደቢት ድል አስመዝግበዋል፡፡ የደቡብ ደርቢ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ ጅማ አባ ቡናም በሜዳው ነጥብ ተጋርቷል፡፡
ሀዋሳ ከተማ 1-3 ደደቢት
ደደቢት በጌታነህ ከበደ ግሩም ብቃት ታግዞ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ የሀዋሳ ከተማ የበላይነት በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ በ18ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጌታነህ ከበደ ወደ ግብነት በመለወጥ ደደቢትን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
በ38ኛው ደቂቃ መሳይ ጳውሎስ በሀዋሳ የግብ ክልል ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ጌታነህ መትቶ በሶሆሆ ሜንሳህ ቢከሽፍበትም ከ4 ደቂቃዎች በኋላ ከመስመር ገፍቶ ወደ ውስጥ በመግባት ግብ አስቆጥሮ የደደቢትን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡
በ68ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሀብቴ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ በጭንቅላቱ ገጭቶ የደደቢትን መሪነት ወደ ሶስት ሲያሰፋ በ80ኛው ደቂቃ አይናለም ኃይለ በታፈሰ ሰለሞን ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ፍሬው ሰለሞን በአግባቡ ተጠቅሞ ጨዋታው በደደቢት 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሮሪ ሆቴል ያዘጋጀው የጨዋታ ኮከብ ሽልማት የተካሄደ ሲሆን ጌተታነህ ከበደ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በመመረጥ የ6 ሺህ ብር እና ለ6 ወራት ነጻ የሆቴል አግልግሎት የሚያገኝበትን ሽልማት ተረክቧል፡፡
ወልድያ 1-0 መከላከያ
ያለ አምበሉ ዮሃንስ ኃይሉ ወደ ሜዳ የገባው ወልድያ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ባማረ የደጋፊ ድባብ እና በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ በርካታ የግብ ሙከራዎችንም ማስተናገድ ችሏል፡፡
ጨዋታው እንደተጀመረ ምንይሉ ወንድሙ ከመስመር ይዞ በመግባት ሞክሮ ቢሌንጌ ያዳነበት የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር፡፡ በ5 ደቂቃ በያሬድ ብርሃኑ ፣ በ7ኛው ደቂቃ በሳሙኤል ታዬ ፣ በ15ኛው ደቂቃ በማራኪ ወርቁ ፣ በ20ኛው ደቂቃ ደግሞ አንዱአለም ንጉሴ የሞከሯቸው ኳሶች በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ከተሞከሩ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በ23 ደቂቃ በረዥሙ ወደ ጎል የተላከውን አንዷለም ንጉሴ በአቤል ላይ ቺፕ በማድረግ አሳልፎ ወልድያን 3 ነጥብ ያስጨበጠች ግብ አስቆጥሯል።
በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች ውጤቱን ለመቀልበስ ኳስ ተቆጣጥረው የተጫወቱ ሲሆን ወልድያዎችም በመልሶ ማጥቃት ያለቀላቸው የግብ እድሎች መፍጠር ችለዋል። በ47 ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ የሞከረውን አስደንጋጭ የግንባር ኳስ ቢሌንጌ በግሩም ሁኔታ አውጥቶ ወልድያን መታደግ ችሏል።
በሁለቱም በኩል በርካታ የግብ ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን ወልድያዎች በመልሶ ማጥቃት በጨዋታው መገባደጃ ተቀይሮ በገባው ጫላ ድሪባ አማካኝነት ሁለት ያለቀላቸው ኳሶች ቢያገኙም አምክኗቸዋል። በተለይ በ94ኛው ደቂቃ ከአቤል ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ የምታስቆጭ እና መሪነቱን ሊያሰፋበት የሚችልበት ነበር።
በጨዋታው 2ኛ አጋማሽ የመከላከያ ኮቺንግ ስታፍ ከኳስ አቀባዩች ጋር ኳስ ዘግይቶብናል በሚል እሰጥ እገባ ውስጥ ገብተው ነበር። በዚህ የተነሳም ከደጋፊዎች ጋር በተወሰነ መልኩ አለመግባባቶች ተስተውለዋል።
በሌሎች ጨዋታዎች ሶዶ ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ በጨዋታው ጥቂት ሙከራዎች ብቻ የተስተናገዱ ቢሆንም በስፍራው ከፍተኛ ተመልካች መገኘቱንና ደማቅ ድባብ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጅማ ላይ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ጅማ አባ ቡና በተመሳሳይ ጨዋታውን ያለ ግብ አጠናቆ ከወራጅ ቀጠናው ይበልጥ መራቅ የሚችልበትን አጋጣሚ ሳይጠቀም ቀርቷል፡፡