ቅዱስ ጊዮርጊስ የኮንጎ ሪፐብሊኩን ኤሲ ሊዮፓርድስ ደ ዶሊሲን አዲስ አበባ ላይ በማሸነፍ ወደ ምድብ ለመጀመሪያ ግዜ ማለፉን አረጋግጧል፡፡ በሳላዲን ሰዒድ ሁለት ግቦች ታግዘው ፈረሰኞቹ የኒያሪ አውሬዎቹን በአጠቃላይ ውጤት 3-0 መርታት ችለዋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት ሆላንዳዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ ማርት ኖይ ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ መደምደም እንደነበረባቸው ተናግረዋል፡፡ “እውነት ለመናገር ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ መጨረስ ይገባን ነበር፡፡ የሳላዲን፣ ፕሪንስ እና አዳና ግርማ ሙከራወች ወደ ግብነት ቢለወጡ ኖር ጨዋታው ተጠናቅቆ ነበር፡፡ ቡዙ የግብ ማግባት ሙከራዎች ፈጥረናል፡፡ ይህ ደግሞ ለእኛ ጥሩ ነገር ነው ምክንያቱም ጥሩ እንቅስቃሴ እንደነበረን ያስረዳል፡፡”
አሰልጣኝ ኖይ ተጋጣሚያቸው በመጀመሪያ አጋማሽ ጫና ፈጥሮ ቢጫወትም የሳላዲን ግብ ጨዋታውን እንደለወጠው ገልፀዋል፡፡ “ይህ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ነው በዚህ ላይ የገጠምነው ጥሩ የሆነ ተቃራኒ ቡድን ነው፡፡ ገና ከጨዋታው ጅማሬ አንስቶ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ የኛ ልጆች ትንሽ ተጨንቀው ነበር ጨዋታውን የጀመሩት፡፡ ተደራጅተን ነበር የተጫወትነው፡፡ የሳላ ግብ ሲመጣ የግብ ጠባቂው ስህተት ስህተት ታክሎበት ለእኛ እፎይታ ነበር፡፡ ለእኛ ዶሊሲ ላይ 1-0 ማሸነፍ መቻላችን በጣም ጥሩ ውጤት ነበር፡፡”
አሰልጣኙ ወደ ከድሉ በኃላ ወደ ሃገራቸው አምርተው ዳግም ቡድናቸውን ዓርብ በሚኖረው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ እንሚመሩ ተናግረዋል፡፡ “ተመልሼ ወደ ሃገሬ ሆላንድ እሄዳለው፡፡ ከባላቤቴ ጋር የህክምና ቀጠሮ አለኝ፡፡ የጡት ካንሰር ህመም ተጠቅታለች፡፡ ሐሙስ ተመልሼ ቡድኔን መምራት እቀጥላለው፡፡ አሁን ላይ በድሉ ደስተኛ ብሆንም ከባለቤቴ ጎን መሆን ስላለብኝ ወደ ሃገሬ አመራለው፡፡” ሲሉ ሃሳባቸው አጠናቅቀዋል፡፡