በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት ሁለት ቡድኖችን ባገናኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2-1 በሆነ ውጤት ድል ማድረግ ችሏል። የቡድኖቹ አሰልጣኞችም ስለጨዋታው የነበራቸውን አስተያየት እንደሚከተለው ገልፀዋል ።
አሰልጣኝ አስራት አባተ – አዲስ አበባ ከተማ
ስለጨዋታው አጠቃላይ እንቅስቃሴ
” በዛሬው ጨዋታ እንዳያችሁት ሁለታችንም ወራጅ ቀጠና ውስጥ ስለምንገኝ እና ያለንም ነጥብ አነስተኛ በመሆኑ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ይዘን ነው የገባነው። ጥሩ ፉክክርም የታየበት ጨዋታ ነበር። እንዳጋጣሚ ተሳክቶልናል ፤ ከዕረፍት በፊት በርካታ እድሎችን ፈጥረን 2-1 ማሸነፍ ችለናል ። ”
ስለ ጨዋታ አቀራረባቸው
” ንግድ ባንኮች ባልጠበቅናቸው መልኩ ነው ጨዋታውን የጀመሩት። ከዚህ በፊት በአንድ አጥቂ ነበር የሚጠቀሙት፡፡ ዛሬ ደግሞ ሁለት አጥቂዎችን ተጠቅመዋል። ይህ ደግሞ ለኛ በሁለተኛ ዕቅዳችን ጥሩ የሚባል የማጥቃት ስትራቴጂ ፈጥሮልናል። በተጨማሪም ከጎሉ በኋላ ሶስት አጥቂዎችን ለመጠቀም ሞክረዋል። እኛ ደግሞ ተጨማሪ የመከላከል ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾችን በመጨመር ውጤታማ እንዳይሆኑ ለማድረግ ሞክረናል ። ”
ስላለመውረድ ፉክክሩ
” የመውረድ ስጋቱ በኛ እና በባንክ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ክለቦች ላይ ያንዣበበ ነው። በተለይ በዚህ በሁለተኛው ዙር ማሸነፍ በጣም ጥቅም አለው። አቻ መውጣት ወደኋላ ያስቀራል። ስለዚህ ሁሉንም ቡድኖች ለማሸነፍ እንጫወታለን። ከወራጅ ቀጠናውም እንወጣለን የሚል እምነት አለን። በባህሪያቸው የታነፁ ወጣት ልጆች አሉን ፤ ቡድኑንም ያድኑታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህም ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን ። ”
አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ስለጨዋታው አጠቃላይ እንቅስቃሴ
” ጨዋታው በውጤት ደረጃ ለኛ መልካም የሚባል አልነበረም። ሆኖም አሸንፈን ለመውጣት ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን በማጥቃት ላይ ተመስርተን ለመጫወት ሞክረናል። ሆኖም ጎል ማስቆጠር አልቻልንም ፤ በቀላሉም ጎሎች ተቆጥረውብናል። ስለዚህም ከጨዋታው ምንም መልካም ነገር ማግኘት አልቻልንም ። ”
ቡድናቸው ስለነበረው አቋም
” አሁንም ቡድናችን በቀላሉ ግቦችን ማስተናገዱ ትልቁ ደካማ ጎኑ ነው። ጎሎቹም የሚቆጠሩበት መንገድ በጣም በቀላሉ ነው። አዲስ አበባዎች በመልሶ ማጥቃት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም መቆጣጠር አልቻልንም። በጨዋታው ሙሉ ደቂቃ ነጥብ ይዘን ለመውጣት ጥረት ማድረጋችን ደግሞ ጠንካራው ጎናችን ነበር። ”
ስለ ፒተር ንዋድኬ ተጠባባቂ መሆን
” ፒተር አመቱን ሙሉ ሲያደርግ በነበረው እንቅስቃሴ ቡድኑን እየጠቀመው አይደለም። በዚህ ሳምንትም በጉዳት ሳቢያ ሙሉ ልምምዶችን ማድረግ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የነበረን አማራጭ አዲስ ያመጣናቸውን ቢኒያም አሰፋን እና ሻኪሩን አጣምረን መጀመር ነበር። ከዚያ በኋላ ፒተርን ቀይረን ስናስገባ የተሻለ ሀይል ፈጥሮልን ነበር። ግን ዞሮ ዞሮ ያው የምንፈልገውን ነገር በማንም ሰው ማግኘት አልቻልንም። ያም ቢሆን ብዙ ጨዋታዎች አሉ እስከመጨረሻው ድረስ የምንችለውን እናደርጋለን ። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይወርዳል ብዬ አላስብም ። “