የሊጉ 20ኛ ሳምንት የአዲስ አበባ ስታድየም ሁለተኛ ጨዋታ የዋንጫ ተፎካካሪ የሆነው ደደቢት እና ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ የሚገኘውን ጅማ አባ ቡናን አገናኝቶ በመልካም እንቅስቃሴ በመታጀብ በ1-1 አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ምንም እንኳን በመጀመሪያው አሰላለፍ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የ 4-2-3-1 ቅርፅ ጨዋታውን የጀመሩ ቢሆንም የማጥቃት አጨዋወታቸው መነሻ ነጥቦች ግን የተለያዩ ነበሩ። የቅርፅ እና የተጨዋቾች ሚና ለውጥ ያደረገው አባ ቡና የፊት አጥቂ ቦታውን ለመሀመድ ናስር በመስጠት አሜ መሀመድን በቀኝ መስመር አማካይነት ያስጀመረ ሲሆን በመጀመሪያዎች ደቂቃዎችም አብዛኛው የማጥቃት እንቅስቃሴው በዚሁ የቀኝ መስመር እና በዋነኝነት በሜዳው ቁመት መሀል ለመሀል በአጥቂ አማካዩ ዳዊት ተፈራ መሪነት የሚደረግ ነበር። በደደቢቶች በኩል ደግሞ እንደተለመደው ከሁለቱ መስመሮች በሚነሱ እንቅስቃሴዎች ብቸኛውን አጥቂያቸውን ጌታነህ ከበደን ለማግኘት ሲሞክሩ ከተከላካይ አማካዬቹ ፊት የተሰለፈው ወጣቱ አቤል እንዳለም ለቡድኑ ጥቃት ሌላ አማራጭ ሲፈጥር ተስተውሏል።
በመጀመሪዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎች ደደቢቶች በፈጣን እንቅስቃሴ ለማጥቃት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በተለይም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ደስታ ደሙ የማጥቃት ተሳትፎ የቡድኑን ጥቃት በማስጀመር በኩል የጎላ አስተዋፅኦ ነበረው ። ይህንን የደደቢት ጥቃት ተከትሎ በራሳቸው ሜዳ ላይ በብዛት ቀርተው የነበሩት የጅማ አባ ቡና ተጨዋቾች ደደቢት በመጀመሪያ ደቂቃዎች የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥር ማድረግ ችለው ቆይተዋል። ሆኖም በሂደት ጅማዎች ከኳስ ውጪ ወደፊት ገፍተው መጫወት መጀመራቸው የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራዎች ለማድረግ አስችሏቸዋል። በዚህም ዳዊት ተፈራ በ7ኛው ደቂቃ አሜ መሀመድ ከቀኝ መስመር ይዞ በመግባት ወደኋላ የመለሰለትን እንዲሁም በ10ኛው ደቂቃ ከኄኖክ ኢሳያስ ተሻግራ በክሌመንት ስትመለስ ካገኛት ኳስ በመነሳት ሁለት የመጀመሪያ ሙከራዎችን ለቡድኑ ማድረግ ችሏል ።
በ12 ኛው ደቂቃ በሰለሞን ሀብቴ ከግራ መስመር የተነሳ የረጅም ርቀት ጠንካራ ምት የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ ደደቢቶችም በ14 እና 21ኛው ደቂቃዎች ላይም በጌታነህ ከበደ እና በአቤል እንዳለ አማካይነት የጅማ አባ ቡና የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ዘልቀው ቢገቡም የመጀመሪያው በቢያድግልኝ ኤልያስ ሁለተኛው በሲሳይ ባንጫ ጥረት ግብ ከመሆን ድነዋል። ሲሳይም የአቤልን ኳስ ለማውጣት ያረገው ጥረት ለጉዳት ዳርጎት ከሁለት ወራት ጉዳት በኋላ ወደጨዋታ በተመለሰው ጀማል ጣሰው ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።
ከአጀማመሩ አንፃር የተቀዛቀዘው ጨዋታም በዚህ መልኩ ቀጥሎ 27ኛው ደቂቃ ላይ አባ ቡናዎች በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ይፈጥሩ ከነበሩት ጫና በመንነሳት የቀሙትን ኳስ ዳዊት ተፈራ ሲያሻግርለት የፊት አጥቂው መሀመድ ናስር በደደቢት ተከላካዮች መሀል በመሮጥ እና የክሌመንትን አቋቋም ባመመልከት ለጅማ አባ ቡና የመጀመሪያውን ጎል ማስቆጠር ችሏል። ይህችም ጎል ለአጥቂው በውድድር አመቱም በጅማ አባ ቡና መለያም የመጀመሪያው ሆና የተመዘገበች ናት ። ከጎሏ መቆጠር በኋላ የነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ጅማዎች እንዳጀማመራቸው ወደኋላ ያፈገፈጉበት እና ደደቢቶች የአቻ ጎል ፍለጋ ወደፊት ገፍተው የተጫወቱበት ሆኖ አልፏል። በዚህም ረገድ አባ ቡናዎች ግብ ሳይቆጠርባቸው በተከታታይ ጨዋታዎች ሲያደርጉ እንደነበረው በጠንካራ የተከላካይ መስመራቸው በመታገዝ ግልፅ የግብ ሙከራ ሳይስተናገድባቸው ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ እንደተጠበቀው ሁሉ ደደቢት ሙሉ ለሙሉ በማጥቃት ላይ ተመስርቶ በመጫወት ጎል የማግኛ ቀዳዳዎችን ለመፍጠር ሲሞክር ተስተውሏል ። ባደረጋቸው የተጨዋቾች ቅያሪ እና የቦታ ሽግሽግ በሁለቱም የመስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ለውጦችን አድርጎ በአንጋፋዎቹ ስዩም ከበደ እና ብርሀኑ ቦጋለ መመራት የጀመረው ደደቢት የመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ሚና ከመጀመሪያው አጋማሽ ጋር ሲነፃፀር ቀንሶ ታይቷል። የ65ኛ ደቂቃውን የሮበን ኦባማን ቅያሪም ጨምሮ ደደቢት የመስመር እና የመሀል አማካዮቹን ለፊት አጥቂው ቀርበው እንዲጫወቱ በማድረግ እና ከኋላ ረጃጅም ኳሶችን በመላክ የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ሲያደርግም ተስተውሏል ። ሆኖም ይህ አጨዋወት ኳስ በሚጨናገፍበት ወቅት ቡድኑ ወደመከላከል በሚያደርገው ሽግግር ወቅት በሁለት እየተከፈለ እና የመስመር አማካዮቹን የመከላከል ተሳትፎ እያጣ በተደጋጋሚ ለመልሶ መጠቃት ሲያጋልጠው እንድንመለከት አድርጎናል። በማጥቃቱም ረገድ ጌታነህ ከበደ ከቆሙ ኳሶች ከመሞከራቸው እና 53ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ሞክሮ በግቡ አናት ወደ ውጪ ከወጣበት ኳስ በቀር በበቂ ሁኔታ የተጋጣሚውን የመከላከል መስመር ሰብሮ ገብቷል ማለት አይቻልም።
በመሀመድ ናስር ጎል ቀዳሚ መሆን ችለው የነበሩት የምዕራብ የኢትዮጵያዎቹ አባ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ወደኋላ በማፈግፈግ እና የተጋጣሚያቸውን ጥቃት በቢያድግልኝ ኤልያስ መሪነት በጠንካራው የመከላከል አደራጀታቸው በማቋረጥ የሚገኙ ኳሶችን በረጅሙ ወደፊት በመላክ ወደመሀል ሜዳው ከተጠጋው የደደቢት የተከላከይ መስመር ጀርባ ያለውን ሰፊ ክፍተት ለመጠቀም አልመው ነበር። ክሪዚስቶም ንታንቢ በዳዊት ተፈራ ተቀይሮ መግባትም ይህን ሀሳብ ይበልጥ የሚያጎላው ነበር ። ሆኖም ከቅያሪው 3 ደቂቃዎች በኋላ መሀመድ ናስር በካድር ኩሊባሊ ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ መውጣቱ የአሰልጣኝ ገ/መድህን ሀይሌ ቡድን ከፈጣን መልሶ ማጥቃቱ ሊያገኝ ይችል የነበራቸውን እድሎች ያመነመነበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። ከቀይ ካርዱም በኋላ ጅማዎች ፊት ላይ አሜ መሀመድን በመጠቀም የተጨዋቹን ፍጥነት ያማከለ ጥረት ሲያደርጉ ታይቷል ። ወጣቱ አጥቂም በ56ኛ እና 70ኛ ደቂቃዎች ላይ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችልም ቡድኑ ግን በፈጣን የማጥቃት ሽግግር በተጋጣሚው ሜዳ ላይ ተጨዋቾችን በአነስተኛ ቁጥር በማሳተፍ ያደረጋቸው የጥቃት ሙከራዎች ባልተሳኩ ቅብብሎች ምክንያት ፍሬ ማፍራት አልቻለም።
ጨዋታው በዚህ መልኩ ቀጥሎም 88ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ የተነሳው የደደቢቶች ጥቃት ወደ ቀኝ መስመር አምርቶ ኤፍሬም አሻሞ ከዚሁ ቀን መስመር ላይ የላካት ኳስ በሳጥን ውስጥ ከጅማዎች ተከላካይ መስመር ፊት ለአፍታ ለብቻው ይገኝ ወደነበረው ጌታነህ ከበደ አምርታ አጥቂው በሚያስደምመው የተለመደ አጨራረሱ የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ግቧም ለጌታነህ በሊጉ 16ኛ ፣ ለደደቢት በጨዋታው አንድ ነጥብ ማሳኪያ እንዲሁም ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ በጅማ አባ ቡና መረብ ላይ ያረፈች የመጀመሪያ ግብ ሆና ተመዝግባለች። በጨዋታው ከፍተኛ ውዝግብ ሲነሳባቸው የቆዩት ፌደራል ዳኛ ማናዬ ወ/ፃዲቅም በሁለተኛው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ክሪዚስቶም ንታንቢ ከመሀል ሜዳ በቀጥታ ሲመታ ክሌመንት ኳሷን ቢይዛትም ተጨዋቹ ኳሷን ያዳነው ከግብ መስመር ካለፈች በኋላ ነው በሚል በጅማዎች በኩል ቅሬታ ቀርቦባቸዋል። የአልቢትሩ አብዛኛው ውሳኔዎች ያልተዋጠላቸው የአባቡና ተጨዋቾችም ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ተቃውሟቸው ቀጥሎ ታይቷል። ከዳኛው ፊሽካ መሰማት በኋላም የሁለቱ ቡድን ተጨዋቾች እና የቡድን መሪዎች ለድብድብ ሲጋበዙም መታዘብ ችለናል ። በጥቅሉ የጨዋታው የአቻ ውጤት ደደቢትን በ35 ነጥብ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እኩል ቢያደርገውም መሪነቱን መረከብ ሚችልበትን ዕድል ግን አሳጥቶታል። የድሬደዋ ከተማን ማሸነፍ ተከትሎም ጅማ አባ ቡና ምንም እንኳን አንድ ነጥብ ቢያሳካም ወደ ወራጅ ቀጠናው ተመልሷል።