ሞሮካዊው የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) ዋና ፀሃፊ ሂሻም ኤል-አምራኒ ከስራ ገበታቸው በራሳቸው ፍቃድ መልቀቃቸውን ዛሬ ለእሀጉሪቱ የእግርኳስ አስተዳዳሪ አካል እና ለአባል ፌድሬሽኖች በላኩት ደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡
የኤል-አምራኒን የስራ መልቀቂ ደብዳቤ ዛሬ በይፋ ስራቸውን የጀመሩት አዲሱ የካፍ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ ተቀብለውታል፡፡
የ37 ዓመቱ ኤል-አምራኒ ለስድስት ዓመታት በዋና ፀሃፊነት ያገለገሉ ሲሆን የቀድሞውን ግብፃዊ የካፍ ዋና ፀሃፊ መስጠፋ ፋሚን የተኩት በ2010 ነበር፡፡ በቀድሞ የካፍ ፕሬዝደንት ኢሳ ሃያቱ ከፍተኛ አመኔታ የነበራቸው ኤል-አምራኒ ከስራ መልቀቃቸው የአፍሪካ እግርኳስ በቅርበት ለሚከታተሉ አግራሞትን አልፈጠረም፡፡ ከሳምንት በፊት አዲስ አበባ ላይ በከፍተኛ ድምፅ ብልጫ ተሸንፈው ከአመራርነታቸው የተሰናበቱት ኢሳ ሃየቱን ሲደግፉ የነበሩ ቁልፍ የካፍ ሰዎች በአዲሱ አመራር ውስጥ ቦታ የሌላቸው መስሏል፡፡
በስንብት ደብዳቢያቸው ኤል-አምራኒ የቀድሞውን ፕሬዝደንት ሃያቱን፣ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና የስራ ባልደረቦቻቸውን በካፍ ለነበራቸው ቆይታ አምስግነዋል፡፡ ለመጪው ፕሬዝደንት አህመድ እና አዲሱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትም መልካም የስራ ዘመን ተመኝተዋል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ በኤል-አምራኒ ምትክ ምክትል ዋና ፀሃፊ የነበሩት ግብፃዊው ኢሳም አህመድን በግዜያዊነት መሾማቸውን ዛሬ አስታውቀዋል፡፡ አህመድ ከአዲሶቹ የስራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባላት ከሆኑት ኮንስታንት ኦማሪ እና ክዌሲ ናያታቺ ጋር በመሆኑ ለካፍ ሰራተኞች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጋቸውን ኮንፌድሬሽኑ ጨምሮ አስታውቋል፡፡