በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ዛሬም በ5 ጨዋታዎች ቀጥሎ ውሏል፡፡ መከላከያ ፣ ንግድ ባንክ ፣ ጌዲኦ ዲላ እና ቦሌ ድል ሲቀናቸው ሲዳማ ቡና ነጥብ ጥሏል፡፡
ምድብ ሀ (በዳዊት ጸሀዬ)
ጠዋት 03:00 ላይ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ቦሌ ክ/ከተማ በተገናኙበት ጨዋታ ቦሌዎች 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል፡፡
ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ነበር የተጠናቀቀ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ቦሌዎች በምንትዋብ ዮሀንስ ግብ መምራት ችለው ነበር፡፡ ይመችሽ ዘውዴ በግል ጥረቷ ባስቆጠረቻት ግብ አካዳሚ አቻ መሆን ሲችል በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለችው ምንትዋብ ዮሀንስ ለራሷና ለቡድኗ ሁለተኛ የሆነውን ወሳኝ ግብ አስቆጥራ ቡድኗ 2-1 እንዲያሸንፍ አስችላለች፡፡
በእለቱ ሁለተኛ መርሃግብር በነበረውና 5፡00 በተጀመረው የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ በምድብ ሀ ከመሪው ደደቢት ተከታትለው በ2ኛና 3ኛ ላይ የተቀመጡት መከላከያና አዳማ ከተማን አገናኝቶ መከላከያ ከሙሉ የጨዋታ የበላይነት ጋር 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሄለን እሸቱ ማራኪ የሆነ የቅጣት ምት ግብ አስቆጥራ ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡
አዳማዎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወደ ግብ ክልላቸው አፈግገው ሲከላከሉ በአንጻሩ መከላከያዎች ከሳቢ የእግርኳስ ፍሰት ጋር በተደጋጋሚ የአዳማን የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች መፈተሽ ችለዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ አጥቅተው የተጫወቱት መከላከያዎች ከሰሞኑ ምርጥ ብቃትዋ ላይ የምትገውና ከቅጣት መልስ የተሰለፈችው የምስራች ላቀው የቡድኗን መሪነት ያሳደገች ግብ አስቆጥራለች፡፡ መከላከያዎች የግብ ልዮነቱን ሊያሰፉበት የሚችሉትን የፍፁም ቅጣት ምት እመቤት አዲሱ ብትመታም የግቡ ቋሚ ሊመልስባት ችሏል፡፡
በጨዋታው መገባደጃ ላይ የአዳማ ከተማዋ ተስፈኛ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ሴናፍ ዋቁማ በቀይ ከሜዳ ወጥታለች፡፡
በዚህ ምድብ ዛሬ ሊደረግ የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና ጥረት ኮርፖሬት ጨዋታ በድሬዳዋ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ለነገ ጠዋት ተዘዋውሯል፡፡
[table id=232 /]
[league_table 18073]
ምድብ ለ (ቴዎድሮስ ታከለ)
አመሻሽ 11:30 በተደረገው ጨዋታ የምድቡ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምድቡ ግርጌ ላይ የሚገኘው አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ላይ ከግማሽ ደርዘን በላይ ግብ አስቆጥሮ 7-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡
የአንድ ቡድን ፍፁም የሆነ የበላይነት በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አቃቂ ቃሊቲዎች ንግድ ባንክን መቋቋም ተስኗቸው ተስተውሏል፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሳለፍነው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ በሜዳው ከደረሰበት ያልተጠበቀ የ1-0 ሽንፈት በኃላ ባስመዘገበው የዛሬው ድል ነጥቡን ወደ 37 አሳድጎ አሁንም ከምድቡ አናት እንደተሰየመ ይገኛል፡፡
ይርጋለም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ እንግዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፍፁም የጨዋታ የበላይነት ያሳዩ ሲሆን በ33ኛው ደቂቃ ትመር ጠንክር ከማዕዘን ምት ያሻማችውን ኳስ አምበሏ ሜሮን አብዶ አሰቆጥራ ጊዮርጊስን መሪ በማድረግ ለዕረፍት ወጥተዋል፡፡
በሁለተኛውም አጋማሽ አሁንም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ሲሆነን በርካታ ሙከራዎችንም ማድረግ ችለው ነበር፡፡ ሲዳማ ቡናዎች አልፎ አልፎ ከሚፈጥሩት እድል ውጭ ይህ ነው የሚባል እድል ባይፈጥሩም ጨዋታው ሊጠናቀቅ 4 ደቂቃ ሲቀር ገለሜ ወርቁ ከቅጣት ምት ያሻማችውን ኳስ ቱሪስት ለማ አስቆጥራ ሲዳማ ቡናን ከመሸነፍ ታድጋለች፡፡
ጌዲኦ ዲላ በሜዳው አርባምንጭ ከተማን አስተናግዶ 3-1 አሸንፏል፡፡ በጨዋታው ባለሜዳዎቹ መቅደስ ተሾመ ጎል መሪ መሆን ቢችሉም ሣራ ጌዳ አርባምንጭን አቻ አድርጋ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡ በሁለተኛውው አጋማሽ ጌዲኦ ዲላዎች ጥሩ የኳስ እንቅስቃሴን በማድረግ ወይንሸት ሽኩር እና በሻቱ ረጋሣ ባስቆጠሯቸው ግቦች 3-1 ማሸነፍ ችለዋል፡፡
[table id=242 /]
[league_table 18083]