የአዳማ ከተማው አማካይ ፋሲካ አስፋው ክለቡ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለ ግብ በተለያየበት ጨዋታ ባሳየው ያልተገባ ባህርይ የ4 ጨዋታዎች ቅጣት እንደተላለፈበት ይታወሳል፡፡ ፋሲካ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ያሳየው ተግባር ያልተገባ መሆኑን ገልጿል፡፡
” ሜዳ ውስጥ ስትጫወት ብዙ ጊዜ ስሜታዊ የሚያደርጉ ነገሮች ይፈጠራሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ያልተገባ ነገሮች ታደርጋለህ። ባለፈው ከኢትዮዽያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ተመልካቹ እኔ ላይ ተቃውሞውን ሲያሰማ በዕለቱ ስሜታዊ ሆኜ ያልተገባ ነገር አሳይቻለሁ፡፡ ያደረኩት ነገር ተገቢ አለመሆኑን አውቄ በይፋ ደጋፊዎችን ይቅርታ ጠይቄያለሁ።” የሚለው ፋሲካ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ተግባሮች ውስጥ እንደማይገባ አያይዞ ተናግሯል፡፡
” በማደርጋቸው ጥሩ ያልሆኑ ተግባራት ቅጣት እየተጣለብኝ ቡድኔን መጥቀም አልቻልኩም። ከዚህ በኋላ ግን ይህ መደገም የለበትም፡፡ ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ የተፈጥሮ ጠባይ አለው፡፡ እኔ ቶሎ ስሜታዊ በመሆን አላስፈላጊ ነገሮችን በሜዳ ውስጥ አደርጋለሁ፡፡ ከተጫዋቾች እና ከደጋፊዎች ጋርም እጋጫለው፡፡ ከዚህ በኋላ ባለው ቀሪ የእግር ኳስ ሕይወቴ ግን ተረጋግቼ መጫወት ነው የምፈልገው።
“ሰሞኑን እንኳ የተፈጠረው ነገር ያለኝን ስምና ዝና አጥፎቶብኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምንም ማሰብ አያስፈልግም፡፡ ከአንድ ጤናማ ከምትለው ሰው የሚጠበቅ አይደለም። ስለዚህ ስሜን ጠብቄ እኔን ለማየት የሚመጡ ታዳጊዎች እና የስፖርት ቤተሰብ ምሳሌ የሚሆን ተግባር ሜዳ ውስጥ ለማሳየት ከዚህ በኃላ እራሴን በሚገባ አስተካክዬ እመጣለው። ”
የቀድሞው የመከላከያ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ በመጨረሻም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ከሚገኘው አዳማ ከተማ ጋር እስከመጨረሻው የመጓዝ አላማ እንዳለው ገልጿል፡፡
” የዘንድሮ አዳማ ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ልምድ ያላቸው እና ታዳጊዎች ያሉበት ስብስብ ነው። አሁን ጨዋታዎችን እያሸነፍን በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ነን፡፡ ከዚህ በኋላ ባሉት ቀሪ ጨዋታዎች ነጥቦችን እየያዝን የዋንጫው አሸናፊ ለመሆን የተቻለንን እናደርጋለን። ”