በ20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ድል ማድረግ የቻሉት አዲስ አበባ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ በዚህ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ተገናኝተው በሁለተኛ አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።
በተመሳሳይ የ 4-1-3-2 የተጨዋቾች አደራደር ጨዋታቸውን የጀመሩት ሁለቱ ቡድኖችበመጀመሪያው አጋማሽ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እጅጉን ተቸግረው ታይተዋል። የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴን እና ብዛት ያለው የኳስ ቅብብልን መሰረት በማድረግ ወደተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት የሚታወቁት አዲስ አበባ እና አርባምንጭ የሚጠቀሙት ስትራቴጂ ተመሳሳይነት ጨዋታውን በበላይነት ለማጠናቀቅ ይህን ዕቅድ በተሻለ መተግበር የሚችለው ቡድን ዕድል ሊኖረው እንደሚችል የሚያስገምት ቢሆንም በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ተቀዛቅዘው ታይተዋል።
ወንድሜነህ ዘሪሁንን እና ምንተስኖት አበራን በተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጠው ጨዋታዉን የጀመሩት አርባምንጮች በመጀመሪያው አጋማሽ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ኳስን መቆጣጠር ችለው ነበር። የኳስ ቁጥጥራቸውም በብዛት እስከ አዲስ አበባዎች የሜዳ ክልል ድረስ የዘለቀ ነበር ። ሆኖም ወደ ማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር ፍጥነት ዘገምተኛ መሆኑ የባለሜዳዎቹ አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች በቶሎ ከኳስ ጀርባ እንዲገኙ የሚፈቅድ ነበር ። በዚህም የተነሳ አርባምንጮች በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ኳስ መቀባበያ ክፍተትን ማግኘት ሲቸገሩ ተስተውሏል። የመስመር አማካዮቹ እንዳለ ከበደ እና ታደለ መንገሻም ወደ መሀል በመግባት ይህን ችግር ለማቃለል ቢሞክሩም ስኬታማ መሆን ግን አልቻሉም። ቡድኑ እንዳማራጭ ለመጠቀም የሞከራቸው ረጃጅም ኳሶችም በዐመለ ሚልኪያስ እና በገ/ሚካኤል ያዕቆብ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ምክንያት በተደጋጋሚ ሲባክኑም ታይቷል ። በዚህ የመጀመሪያ አጋማሽም አዞዎቹ በ36ተኛው ደቂቃ ዐመለ ሚልኪያስ ከሞከረው እና ወደውጪ ከወጣበት ኳስ በቀር ሌላ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
ንግድ ባንክን የረቱበትን የተጨዋቾች ስብስብ የተጠቀሙት እና የወትሮው የመሀል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ማግኘት የተሳናቸው አዲስ አበባዎች ባልተለመደ ሁኔታ ረጃጅም ኳሶችን እንደ ዋና አማራጭ ሲጠቀሙ ተስተውሏል። ሆኖም የአጥቂ አማካዮቹ ሳይቀሩ በብዛት ከኳስ ጀርባ መገኘታቸው የሚጣሉትን ረጅም ኳሶች በአርባምንጭ ሜዳ ላይ ለመጠቀም በቂ ተጨዋቾችን በማጥቃት ሂደት ላይ ለማሳተፍ አለመቻላቸው ኳሶቹ በብዛት ውጤት አልባ እንዲሆኑ ያስገደደ ነበር። በሁለቱ አጥቂዎች እና በአማካይ መስመሩ መሀከልም የሚፈጠረው ሰፊ ክፍተት ምክንያት ለተወሰደባቸው ብልጫ ያፈገፈገው የአማካይ መስመራቸው አንዱ መንስኤ ነበር ። የፊት አጥቂው አጥቂ ኃይሌ እሸቱ አልፎ አልፎ ይህን ክፍተት ለመሙላት ወደኃላ በመሳብ ያደርግ የነበረው ጥረትም ለብቻው የመሀል ሜዳ የበላይነቱን መመለስ አላስቻለውም ። የቡድኑ ዋነኛ የመሀል መስመር ተሰላፊዎችም ከወትሮው በተለየ ተደጋጋሚ የኳስ ቅብብል ስህተት ሲሰሩ ታይቷል።
የሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ፍፁም የተለየ ገፅታ ነበረው። ቡድኖቹም በመጀመሪያው አጋማሽ የነበሩባቸውን ችግሮች በመጠኑ ቀርፈው ታይተዋል። ይህን ተከትሎም ጎሎች እና በርካታ ሙከራዎች በጫወታው ሁለተኛ 45 ለመመልከት በቅተናል። አርባምጮች ከመጀመሪያው በተሻለ በማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ ፍጥነትን በመጨመራቸው የተሻለ ክፍተትን እያገኙ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በቅተዋል። አዲስ አበባዎችም በበኩላቸው ወደኋላ ተስቦ የነበረውን የአማካይ መስመራቸውን ወደአጥቂዎቹ ቀርቦ እንዲጫወት ማድረጋቸው ለጥቃት ሲያጋልጣቸው የነበረ ቢሆንም በአንፃሩ የአርባምንጮችን ግብ ለመፈተሽ አግዟቸዋል።
በዚህም መሰረት ከእረፍት መልስ አርባምንጮች በ 47ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ ሳጥን ውስጥ ገብቶ የሞከረውን እና ተክለማርያም ያወጣበትን እንዲሁም 59ኛው ደቂቃ ላይ አሁንም ታደለ ከግራ መስመር የላከለትን ኳስ ዐመለ በግንባሩ ሞክሮ ወደውጪ የወጣበትን ጥሩ ዕድሎች መፍጠር ችለው ነበር። ሆኖም የአዲስ አበባው የመስመር አማካይ ዳዊት ማሞ ፤ በ 63ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ አለሙ በግራ መስመር ከግብ ክልሉ ከወጣው ጃክሰን ፊጣ ጋር ተገናኝቶ ኳስን በመንጠቅ መሀል ላይ ይገኝ ለነበረው ኃይሌ እሸቱ የላከውን እና ተከላካዮች በአግባቡ ሳያወጡት በመቅረታቸው ያገኘውን ኳስ በቀጥታ በመምታት የመጀመሪያውን ጎል አስቆጠረ ። ይህች ጎል ለዳዊት በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ያስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ነበረች ።
የአዲስ አበባዎች መሪነት ግን ከሁለት ደቂቃ በላይ መዝለቅ አልቻለም። በ65ኛው ደቂቃ ላይ የአዞዎቹ የፊት አጥቂ ገ/ሚካኤል ያዕቆብ በግንባሩ በመግጨት ጨዋታውን ወደ አቻነት መልሶታል።
ከዚህ በኋላ በነበረው እንቅስቃሴ ደከም ብለው የታዩት አርባምንጮች 80ኛው ደቂቃ ላይ በብርሀኑ አዳሙ እና በገ/ሚካኤል አማካይነት ከግቡ አፋፍ ላይ ጥሩ እድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም አልተሳካላቸውም። አዲስ አበባዎችም ተቀይሮ በገባው የመስመር አማካይ ጀምስ ኩዋሜ የግንባር ኳስ 86ኛ ደቂቃ ላይ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር አልሆነላቸውም። 88ተኛው ደቂቃ ላይ ይሄው ተጨዋች በአስገራሚ ብቃት በግራ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ዳዊት ማሞ አግኝቶ ከሳጥን ውስጥ ሲሞክር ጃክሰን ፊጣ አውጥቶበታል። ይህም የጨዋታው የመጨረሻ የግብ ሙከራ ትእይምት ሆኖ አልፏል። ከጨዋታው ባሳኩት አንድ ነጥብ አማካይነትም አርባምንጮች ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችሉ አዲስ አበባዎች በነበሩበት የ 15ተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል።