የጨዋታ ሪፖርት | ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት መርሃግብር ዛሬ ቀጥሎ ሲውል በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሌላኛው የመውረድ ስጋት የተደቀነበትን ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል፡፡

በዛሬው ጨዋታ ላይ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከወትሮው በተለየ በአማካይ ክፍላቸው ላይ ከአዲስ ፈራሚው ጋናዊው ኢማኑዌል ላሪያ ፊት ሶስት የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን አማካዮች ማለትም ዮሴፍ ዳሙዬን በግራ ሱራፌል ዳንኤልን በቀኝ እንዲሁም አምሃ በለጠን በ10 ቁጥር ሚና ከሁለቱ የፊት አጥቂዎች ሀብታሙ ወልዴና በረከት ይሳቅ ጀርባ ተጠቅመዋል፡፡ በአንጻሩ ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስአበባ ከተማ ከተሸነፈው ቡድን ላይ ከቅጣት የተመለሰውን ሮቤል ግርማን በግራ ተከላካይነት ሲያሰልፉ አማካይ ስፍራ ላይ አንበሉ ታዲዮስ ወልዴ ዳግም ወደ መጀመርያ አሰላለፍ ተመልሶ ቡድኑ በ4-1-4-1 ቅርፅ ወደ ጨዋታው ገብተዋል፡፡

ተመጣጣኝ የሆነ በአመዛኙ በመሀል ሜዳ ላይ ቶሎ ቶሎ የሚቆራረጡ የኳስ ቅብብሎች በታዩበት የመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ይህ ነው የሚባል የግብ እድል ለመፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ደካማና ለተመልካች እጅግ አሰልቺ የሆነ እንቅስቃሴ በታየበት በዚሁ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱ የድሬዳዋ ከተማ አጥቂ የሆኑት ሀብታሙ ወልዴና በረከት ይስሃቅ በጨዋታው ዋንኛ የድሬዳዋ ከተማ የፈጠራ ምንጭ እንዲሆኑ ከጀርባቸው ከተሰለፉት ሶስቱ የአጥቂ አማካዮች የኳስ አቅርቦት ሲያገኙ አልተስተዋለም፡፡ ይልቁንም ግብጠባቂው ሳምሶን አሰፋ በቀጥታ ወደፊት የሚያሻግራቸው ኳሶች በአንጻራዊነት ድሬዳዋ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ለፈጠሯቸው ሁለት ኢላማቸውን ያልጠበቁ የግብ ሙከራዎች መንስኤ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በኩል አልፎ አልፎ በፈጣን የመስመር አጨዋወት አደጋ ለመፍጠር ከሚያደርጉት ጥረት ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ በቀኝ መስመር ተከላካያቸው ሄኖክ አዱኛ በኩል በተደጋጋሚ ጫናዎችን መፍጠር ቢችሉም የተገኙትን አጋጣሚዎች ይሁን እንደሻውና ሀብታሙ ወልዴ ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡
ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታውን ለማሸነፍ በተሻለ ፍላጎት ተንቀሳቅሰዋል በዚህም ቶሎ ቶሎ ወደፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በተለይም የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኙት ኢትዮጲያ ንግድ ባንኮች በ75ኛው ደቂቃ ላይ ፒተር ንዋድኬ በግንባሩ ያቀበለውን ኳስ ቢኒያም አሰፋ በአየር ላይ ኳሷ እንደመጣች ሞክሯት ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ ተጠቃሽ ነበረች፡፡

በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ብልጫ ወስደው የተሻለ ወደፊት መድረስ ቢችሉም የቡድኑ ተጫዋቾች በመልሶ ማጥቃት በእጃቸው የገባችውን አንድ ነጥብ ላለማጣት በሚመስል መልኩ አፈግፍገው በመጫወታቸው ወደፊት ሲሄዱ ቁጥራቸው በእጅጉ ስለሚያንስ በተደጋጋሚ በድሬዳዋ ተጫዋቾች የቁጥር ብልጫ ስለሚወሰድባቸው የሚገኙትን ኳሶች ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡

ደካማ እንቅስቃሴ በታየበት በዚሁ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በ90 ደቂቃ ውስጥ ሁለት ብቻ ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎች ብቻ መታየታቸው ብቻ ጨዋታው ምንም ያህል ደካማ እንቅስቃሴ እንደታየበት በበቂ ሁኔታ የሚገልፅ ነበር፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ16 ነጥብ ከበላያቸው ከሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ጋር በነጥብ እኩል ቢሆኑም በግብ ክፍያ ተበልጠው አሁንም በሊጉ ግርጌ ላይ ሲገኙ ድሬዳዋ ከተማዎች በ22 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

አስተያየቶች

ሲሳይ ከበደ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስለ ጨዋታው

“በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ቡድናችን ባሰብነው መልኩ ባለመንቀሳቀሱ እጅግ በጣም ደካማ የሆነ እንቅስቃሴን ልናሳይ ችለናል፡፡በሁለተኛው አጋማሽ መጠነኛ የታክቲክ ለውጦች አድርገን ተጭነን ለመጫወት ጥረት አድርገናል፡፡ በሜዳችን እንደመጫወታችን ነጥቡ ያስፈልገን ስለነበር የተቻለንን ጥረት አድርገናል ነገርግን ልጆቼ አሁንም የአቅም ማነስ ችግር ሳይኖርባቸው በተከታታይ ነጥብ በመጣላችን የተነሳ ከሚገኙበት የስነልቦና ጫና መውጣት ስላልቻሉ አሁንም እየተቸገርን እንገኛለን፡፡”

ስለ ቀጣይ እቅድ

“በሊጉ ገና ቀሪ 9 ጨዋታዎች አሉ በነዚህም ጨዋታዎች ላይ ያሉብንን ችግሮች ቀርፈን በሊጉ ለመቆየት የተቻለንን ጥረት እናደርጋለን፡፡”

ስለ ግብ የማስቆጠር ችግራቸው

“በውድድሩ አጋማሽ ወደ ቡድናችን በቅርቡ የተቀላቀለው ቢኒያም አሰፋ በፊት በቡድኑ ከነበሩት አጥቂዎች በተሻለ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ከዚህ ቀደም በቡድኑ ውስጥ የነበሩት የአጥቂ ተሰላፊዎች ቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወቅት እገዛቸው እጅግ ያነሰ ነበር ፤ ነገርግን አሁን እነዛን ተጫዋቾች በሜዳ ውስጥ የቆዩበትን ደቂቃ ቀንሰነዋል፡፡በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ላይ የታክቲክ ለውጦች በማድረግ ቡድኑ በቶሎ ወደ ግብ እየደረሰ ግቦችን የሚያስቆጥር ቡድን ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን፡፡”

ዘላለም ሽፈራው – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው ሁለት የተለያዩ መልኮች የነበሩት ነበር፤ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድናችን ፍፁም ቀዝቃዛ ነበር በብዙ መስፈሮቶች ደካማ ነበርን ፤ በሁለተኛው አጋማሽ በነዚህ ችግሮች ላይ ተነጋግረን መጠነኛ ለውጦችን አድርገን በሁለተኛው አጋማሽ በጣም ጫና ፈጥረን ተጫውተናል፡፡ነገርግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻልንም፡፡እንደአጠቃላይ በሁለተኛው አጋማሽ ባሳየነው ነገር ብደስትም ያገኘናቸውን የግብ እድሎች ወደ ግብ በመቀየር ረገድ ቡድናችን በጣም ደካማ ሆኖ አስተውዬዋለሁ፡፡”

በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ አቻን ለማግኘት በማሰብ በጥልቀት ስለመከላከላቸው

“በጨዋታው የመጨረሻ 5 ደቂቃዎች ላይ ብቻ ቡድኔ በፍፁም መከላከልን መሠረት አድርጎ ተጫውቷል፡፡ከሜዳ ውጪ እንደሚጫወት ቡድን እነዚህን አደገኛ የሆኑ የመጨረሻ 5 ደቂቃዎች ግብ እንኳን አስቆጥረህ እየመራህ ቢሆንም እንኳን በእጅህ የያዝከውን ነገር ላለማጣት ስትል በጥብቅ መከላከሉ የግድ ይላል፡፡በተለይ በነዚህ ደቂቃዎች ላይ ለማጥቃት በማሰብ ወደፊት ተጭነህ ስትጫወት ግብ ብታስተናግድ የ90 ደቂቃ ልፋትህ መና ይቀራልና በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በእርግጥም ተከላክለን ተጫውተናል፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *