በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ሶስተኛ የጨዋታ ቀን አዲስ አበባ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ 09:00 ላይ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የተጫወተው ደደቢት 1-1 በሆነ ውጤት ጨዋታውን አጠናቋል። ጨዋታው የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ለመቆናጠጥ በሚደረገው ፉክክር ተሳታፊ በሆነው ደደቢት እና ከመውረድ ስጋት ነፃ መሆን ባልቻለው ኤሌክትሪክ መሀል እንደመደረጉ የማሸነፉን ቅድመ ግምት ደደቢት አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ጨዋታው ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ ተደርጎበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ የሆነ የጨዋታ አቀራረብ የነበራቸው ሲሆን ተመጣጣኝ የሆነ የጨዋታ እንቅስቃሴ ተመልክተናል። ደደቢት ከተከላካዮች ፊት ከድር ኩሊባሊ፣ አስራት መገርሳ እና ሳምሶን ጥላሁንን በመጠቀም ከፊት ኤፍሬም አሻሞና ሽመክት ጉግሳን በመስመር፣ ጌታነህ ከበደን በፊት አጥቂነት ያሰለፈ ሲሆን ኤሌክትሪኮችም በተመሳሳይ የአጥቂ ክፍላቸውን በፍፁም ገብረማርያም፣ ሙሉአለም ጥላሁን እና ኢብራሂም ፎፋና በማዋቀር ወደሜዳ ገብተዋል። ኤሌክትሪኮች ኳስን በአጭር ቅብብል ወደተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ይዘው በመግባት አልፎ አልፎም በቀኝ መስመር በኩል የኢብራሂም ፎፋናን ፍጥነት በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ደደቢቶች በበኩላቸው ለጌታነህ ከበደ በረጅሙ በሚሻገሩ ኳሶች ለመጠቀም ሲሞክሩ ተስተውሏል።
በጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ጨዋታውን የጀመሩት ደደቢቶች የመጀመሪያውን ግብ ለማስቆጠር 3 ደቂቃዎች ብቻ ወስዶባቸዋል። አምበሉ ብርሃኑ ቦጋለ ከማዕዘን ምት በቀጥታ ያሻማው ኳስ የኤሌትሪኩ ግብ ጠባቂ ሱሌይማን አቡ ስህተት ታክሎበት መረብ ላይ አርፎ ደደቢትን መሪ አድርጓል።
በጨዋታው 11ኛ ደቂቃ የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ ይዘው የገቡትን ኳስ ፍፁም ገብረማርያም አግኝቶ መሬት ለመሬት ወደግብ ቢያሻማውም ሙሉዓለም ጥላሁን ከግብ ጠባቂው ሱሌይማን ቀድሞ ሊደርስበት አልቻለም። ኤሌክትሪኮች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብ ማስተናገዳቸው ድንጋጤ ሳይፈጥርባቸው ተረጋግተው መጫወት የቀጠሉ ሲሆን በ16ኛው ደቂቃም አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ አግኝተዋል። ሙሉዓለም ጥላሁን በግሩም ሁኔታ የላከለትን ኳስ አይቮሪያዊው አጥቂ ኢብራሂም ፎፋና ተቆጣጥሮ አይናለም ሀይሉን በማለፍ የደደቢት መረብ ላይ አስቆጥሯል።
ደደቢቶች መሪነታቸውን መልሰው ለማግኘት ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን በ33ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ ከርቀት ሞክሮ ወደውጪ የወጣበት፣ እንዲሁም በ36ኛው ደቂቃ ከድር ኩሊባሊ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ወደግብ መትቶ የኤሌክትሪኩ ተከላካይ በረከት ተሰማ ከመስመር ላይ ያወጣበት ኳስ የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ። በጨዋታው ተደጋጋሚ ስህተቶችን ሲሰራ የነበረው ጋናዊ የኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ ሱሌይማን አቡም በ41ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት የሞከረውን ኳስ በግሩም ሁኔታ በማዳን ቡድኑን በድጋሚ ከመመራት ታድጓል።
በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜም ከመጀመሪያው ብዙም ያልተለየ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በኤሌክትሪክ በኩል የመስመር ተከላካዮቹ በተለይም በቀኝ በኩል ተስፋዬ መላኩበተደጋጋሚ ወደፊት በመሄድ የማጥቃት እንቅስቃሴውን እንዲያግዙ ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል።
በ64ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ሲሴ ሃሰን በግንባሩ ሞክሮ ታሪክ ጌትነት ሲመልስበት በተቃራኒው ጎል በመልሶ ማጥቃት የሄደውን ኳስ ጌታነህ ከበደ ለኤፍሬም አሻሞ አመቻችቶ ሰጥቶት ኤፍሬም ለማመን በሚከብድ ሁኔታ የሳተው ኳስ ለደደቢት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ዳዊት እስጢፋኖስ ከ20ሜትር ርቀት አካባቢ የመታው ቅጣት ምት ለጥቂት ወደውጪ ሲወጣ ጨዋታው መደበኛ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ 1ደቂቃ ሲቀረው ተስፋዬ መላኩ ከሳጥን ውጪ መትቶ ግብ ጠባቂው የያዘበት ኳስ የጨዋታው የመጨረሻ ሙከራ ነበር።
ውጤቱን ተከትሎ ኤሌክትሪክ 24 ነጥቦችን በመያዝ መከላከያን በግብ ክፍያ በልጦ 10ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ እስኪደረግ ድረስ ሊጉን ለጥቂት ሰዓታት መምራት ችሎ የነበረው ደደቢት በ36 ነጥቦች ሁለተኛ ነው።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ብርሃኑ ባዩ – ኤሌክትሪክ
ሙሉ በሙሉ አጥቅተን ተጫውተን ውጤት ይዘን ለመውጣት ነበር እቅዳችን። ጥሩ እንቅስቃሴ ከማሳየት በላይ እኛ ውጤቱን ነበር የፈለግነው። ነገርግን እንዳሰብነው አልሆነልንም፤ በእግርኳስ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ይዘህ የምትገባውን ነገር ሜዳ ላይ ለመተግበር ትንሽ ይከብዳል። ተጫዋቾቹ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፤ ነገርግን አልተሳካልንም። አንድ ነጥብ ይዘን መውጣት ስለቻልን ግን አልተከፋንም። የቡድናችን እንቅስቃሴ ጥሩ በመሆኑ ለሚቀጥሉት ጨዋታዎቻችን ብዙ የሚያሰጋን ነገር የለም።
ኤልያስ ኢብራሂም – ደደቢት (ምክትል አሰልጣኝ)
በእግርኳስ ሁሌ አሸንፋለሁ ብለህ አትገባም። እነርሱ ላለመውረድ ነው የሚጫወቱት፤ እና ደግሞ ለሻምፒዮንነት ነው የምንጫወተው። ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጉልበት አውጥተን ተጭነን ስለተጫወትን ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ላይ የመቀዛቀዝ ነገር ታይቶብናል። ከዚህ በኋላ ለሚኖሩን ጨዋታዎች ድክመታችንን አስተካክለን ባለንበት የሻምፒዮንነት ፉክክር እንቀጥላለን ብዬ ነው የማስበው።