የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ለሴኔጋሉ የ2015 የአፍሪካ ከ20 አመት በታች ሻምፒዮና ለማለፍ የ1ኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታውን በመጪው እሁድ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያደርጋል፡፡
በቅድመ ማጣርያው የሲሸልስ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድንን በድምር ውጤት 5-0 አሸንፎ ወደ አንደኛው ዙር ለማለፍ የበቃው ወጣት ቡድኑ ጨዋታውን በአሸናፊነት ለመወጣት እንደተዘጋጁ አሰልጣኝ ወንድማገኝ ከበደ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ስለ ደቡብ አፍሪካ ከ20 አመት በታች ቡድን የቻልነውን ያህል መረጃ ሰብስበናል፡፡ በጉልበት እና ፍጥነት ላይ ያመዘነ ጨዋታ እንደሚጫወቱ ተረድተናል፡፡ ከሲሸልሱ ጨዋታ ያገኘነውን ልምድ በማጎልበት ተጫዋቾቹን በታክቲኩ እና ስነልቡናው በኩል በሚገባ አዘጋጅተናቸዋል፡፡ ለጨዋታው ልዩ ትኩረት በማድረጋችን ተጫዋቾቹ በመገናኛ ዘዴዎች ላይ ያለቸውን አጠቃቀም ገድበናል፡፡ ›› ብለዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ከኢትዮጵያ በኩል ከሲሸልስ ጋር በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ 2 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው አጥቂው ሃያቱ አብዱራህማን በጉዳት ምክንያት በእሁዱ ጨዋታ አይሰለፍም፡፡
ኢትዮጵያ በደርሶ መልሱ ደቡብ አፍሪካን ጥላ ካለፈች በ2ኛው ዙር ከካሜሩን ከ21 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጋር ትጫወታለች፡፡
{jcomments on}