በአብርሀም ገብረማርያም እና ቴዎድሮስ ታከለ
ቀን – ሀሙስ ሚያዝያ 5 ቀን 2009
ቦታ – ሀዋሳ ከተማ ስታድየም ፤ ሀዋሳ
ሰአት – 10:00
ዳኛ – ፌዴራል ዳኛ አሰፋ ደቦጭ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚያስተናግዳቸው ትልልቅ የደርቢ ጨዋታዎች መካከል በሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና መካከል የሚደረገው ጨዋታ አንዱ ነው፡፡ ነገ የሀዋሳ ከተማ ስታድየምም በ23ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ይህንን ” የወንድማማቾች ደርቢ ” ያስተናግዳል፡፡ ሲዳማ ቡና በዋንጫ ፉክክር ወስጥ ለመቀጠል የሚያደርገው ጨዋታ ሲሆን ለሀዋሳ ከተማም ሙሉ ለሙሉ ከወራጅነት ስጋት ለመውጣት ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡
ወቅታዊ ሁኔታ
ሀዋሳ ከተማ
ደረጃ – 8ኛ
የ5 ጨዋታ አቋም | አቻ – ተሸ – አሸ – አሸ – አቻ
ሀዋሳ ከተማ ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ በኋላ የተሻሻለ ቡድን መሆን ችሏል፡፡ ቀድሞውንም በርካታ ግብ የሚያስቆጥረው ቡድን በ6 ጨዋታ 13 ጎል በማስቆጠር ሲቀጥል የሚቆጠርበትንም ጎል መቀነስ ችሏል፡፡ በወራጅ ቀጠናው ሲዳክር የነበረው ቡድን አሁን በሰንጠረዡ ወገብ ላይ መቀመጥ የቻለ ሲሆን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አዝናኝ እና በማጥቃት ላይ የተመሰረተ እግርኳስ የሚጫወተውን ቡድን ውጤታማ ለማድረግ መንገዱን ያገኙ ይመስላሉ፡፡ በሁለተኛው ዙር በደደቢት ብቻ ሽንፈት ሲያስተናግድ በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጪ ነጥብ ይዞ መውጣት ጀምሯል፡፡
ሲዳማ ቡና
ደረጃ – 3ኛ
የ5 ጨዋታዎች አቋም | አቻ – አቻ – አሸ – ተሸ – አሸ
እንደ ሀዋሳ ከተማ ሁሉ በሁለተኛው ዙር አንድ ጨዋታ ብቻ የተሸነፈው ሲዳማ ቡና ሲቸገርበት የነበረው ከሜዳ ውጪ ውጤታማ የመሆን ችግር በመጠኑ መቅረፍ ችሏል፡፡ በዚህም ፋሲልን አሸንፎ ከድሬዳዋ እና ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ የተሸነፈውም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሴኮንዶች ሲቀሩት በተቆጠረበት ግብ ነው፡፡ ጠንካራ የተከላካይ መስመር እና በማይቀያየር የተጫዋቾች ምርጫ የተዋሀደው ሲዳማ ቡናን ለማሸነፍ ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡
ከጨዋታው ምን እንጠብቅ?
የሀዋሳ ከተማ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እና ተደጋጋሚ ጥቃት ፤ የሲዳማ ቡና ጥልቅ መከላከል እና የመልሶ ማጥቃት በጨዋታው ላይ ይጠበቃል፡፡
ሀዋሳ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ላይ እንደታየው ኳስን በብዛት ከመቀባበልና በሜዳው ቁመት የማጥቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ ባሻገር በቅርብ ጨዋታዎች የሜዳውን ስፋት በመጠቀም ከተሻጋሪ ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ምናልባትም የመቀባበያ ክፍተቶች የማይሰጠው ሲዳማ ቡናን መግጠማቸው ሜዳውን ወደ ጎን በመለጠጥ ሰፊ የመቀባበያ ክፍተቶችን ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሲዳማ ቡና ከሜዳ ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ ተጠቅጥቆ በመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ሲጫወት ተመልክተናል፡፡ በአጥቂዎቹ (በተይም አዲስ ግደይ) ፍጥነት በመጠቀም ከተጋጣሚ ተከላካይ መስመር ጀርባ ያለውን ቦታ ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ እንዲሁም በመሀል እና የመስመር ተከላካዮች መካከል ያለውን ክፍተት ለመጠቀም ሲጥሩ ይስተዋላል፡፡ ሀዋሳ በሁለተኛው ዙር ሲያደርግ እንደነበረው በ3-5-2 የሚጫወት ከሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴ ወቅት በመስመር ተመላላሾች እና ሶስቱ የመሀል ተከላካዮች መካከል የሚፈጠረውን ክፍተት ሲዳማዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡
የእርስ በእርስ ግንኙነት እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 15 ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች 4 ጊዜ አሸንፈዋል፡፡ 7 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡ ሀዋሳ 16 ጎል ሲያስቆጥር ሲዳማ ቡና 18 አስቆጥሯል፡፡
– ሀዋሳ ላይ 7 ጨዋታዎች ተደርገው አምስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሁለቱ አንድ አንድ ድል አስመዝግበዋል፡፡
የቡድን ዜናዎች
በሲዳማ ቡና በኩል የተጫዋች ጉዳት እና ቅጣት የሌለ ሲሆን ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል፡፡ በሀዋሳ ከተማ በኩል ግን በርካታ ተጫዋቾች ከጨዋታው ውጪ ይሆናሉ፡፡ ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህ በቅጣት ፣ ደስታ ዮሀንስ ፣ መላኩ ወልዴ እና መሳይ ጳውሎስ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው በተከላካይ መስመሩ ላይ መሳሳትን ይፈጥራል፡፡
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ
አላዛር መርኔ
ዳንኤል ደርቤ – መሀመድ ሲይላ – አዲስ አለም ተስፋዬ – ዮሀንስ ሰጌቦ
ኃይማኖት ወርቁ – ታፈሰ ሰለሞን – ፍሬው ሰለሞን –
ጋዲሳ መብራቴ – ጃኮ አረፋት – መድሀኔ ታደሰ
ሲዳማ ቡና
ለአለም ብርሀኑ
አንተነህ ተስፋዬ – ሰንደይ ሙቱክ – አበበ ጥላሁን – ወሰኑ ማዜ
ኦልሪሽ ሳውሪል – ሙሉአለም መስፍን
ትርታዬ ደመቀ – ፍፁም ተፈሪ -አዲስ ግደይ
ላኪ ሳኒ
አስተያየቶች
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ሲዳማ ቡና
በሁለተኛው ዙር ቡድኑ ያሳየው መሻሻል
ከመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ጀምሮ ጥሩ መሻሻል እያሳየን እንገኛለን፡፡ ተደጋጋሚ ነጥብ ማስመዝገብም ችለናል፡፡ ከማራኪ እና ደጋፊውን ከሚያስደስት እንቅሰቃሴ ጋር ውጤት ማስመዝገብ ችለናል፡፡ በዚህም ወደ ጥሩ ሪትም መጥተናል፡፡ የነገው ተጋጣሚያችን ሲዳማ ሊጉን ከሚመሩት እንደኛው ነው፡፡ እኛ ደግም ሙሉ በሙሉ ከስጋት ለመላቀቅ የምናደርገው ጨዋታ በመሆኑ ጠንካራ እና ለሁለታችንም አስፈላጊ ነው፡፡
የማጥቃት (ሀዋሳ) እና የመከላከል (ሲዳማ) ፍልሚያ
በደደቢት እና አዳማ ከተቆጠሩብን ውጭ በመከላከሉ ጥሩ ሆነናል፡፡ በየጨዋታው ማጥቃትም መከላከልም አለብን፡፡ የሲዳማ አጨዋወት መከላከል ቢሆንም ጥሩ ጥሩ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች አላቸው፡፡ በሊጉ መቆየት ካለብን በቀላሉ ግብ ማስተናገድ የለብንም፡፡ ዋናው ግብ አናስተናግድም ሳይሆን ግብ ብናስተናግድ እንኳ ከተቆጠረብን በላይ ማስቆጠር አለብን፡፡
አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና
የመሪነት ፉክክር
እኛ ከመሪወቹ ተርታ የተገኘነው የተለየ ሚስጥር የለውም ተጫዋቾቼ በሚገባ ስራ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው እና የሚሰጣቸውን በአግባቡ መወጣታቸው ነው፡፡ ለውጤታችን ማማር በነገውም ጨዋታ ይሄን ከተጫዋቾቼ እጠብቃለሁ፡፡
ከመሪወቹ ቡድኖች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በተለየ መልኩ ብዙ ጨዋታ ከሜዳቸው ውጭ ማድረጋቸው የሚያሳድረው ተጽዕኖ
ብዙም ተፅዕኖ ይኖረዋል ብዬ አላስብም፡፡ በተለይ ሜዳው አመቺ ከሆነ ጥሩ እግርኳስን ስለምንጫወት ምንም ነገር ይፈጠራል ብዬ አላስብም፡፡ ጊዮርጊስም ሆነ ደደቢት ከአዲስ አበባ ክለቦች ጋር ስለሚገናኙ እንጂ የተለየ ነገር አለው ማለት ይከብዳል፡፡ እኛ በቀጣይ በሜዳችን አራት ጨዋታ አለን፡፡ ከሜዳችን ውጭ ደግሞ ከነገው ውጭ 3 ጨዋታ ነው የሚቀረን፡፡ በጥንቃቄ እየተጫወትን ውጤት ለማስመዝገብ እና በዋንጫው ውስጥ ለመቆየት ጥረት እናደርጋለን፡፡
ስለ ጨዋታው
በርግጠኝነት እናሸንፋለን፡፡ የደርቢ ጨዋታ ውበት ነው ፤ ህዝቡም በጉጉት ይጠብቀዋል፡፡ እኛ አሁን በማጥቃትም ሆነ በመከላከሉ የተሻለ የሚያደርጉ ተጫዋቾች አሉን፡፡ ስለሆነም በነገው ጨዋታ ሜዳቸውም አመቺ ስለሆነ ጥሩ ተጫውተን ውጤት እናስመዘግባለን፡፡ ስለዚህ ውጤቱ ስለሚያስፈልገን እናሸንፋለን የሚል እምነት አለኝ፡፡