ቀን – ሀሙስ ሚያዝያ 5 ቀን 2009
ቦታ – አዲስ አበባ ስታድየም
ሰአት – 10:30
ዳኛ – ፌዴራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በሚደረጉ 6 ጨዋታዎች ሲጀመር ኢትዮጵያ ንግደድ ባንክ ከ ደደቢት የሚያደርጉት ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ካለው አስፈላጊነት አንጻር ተጠባቂ ጨዋታ ሆኗል፡፡
የቅርብ ጊዜ አቋም
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ደረጃ – 15ኛ
ያለፉት 5 ጨዋታዎች – አቻ – ተሸ – ተሸ – አቻ – አሸ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከረጅም ሳምንታት ድል አልባ ጉዞ በኋላ በ22ኛው ሳምንት ከአርባምንጭ በ2-0 ድል መመለሱ ለጨዋታው ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥርለታል፡፡ ቡድኑ አስከፊ የውድድር ዘመን እያሳለፈም ቢሆን ላለመውረድ በሚደረገው ፉኮክር ውስጥ የሚሳተፉ ክለቦች እምብዛም በነጥብ አለመራቃቸው ለንግድ ባንክ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ በተለይ ከባንክ በላይ የሚገኙት ክለቦች ከሜዳቸው ውጪ እንደመጫወታቸው የዛሬው ጨዋታ ለሀምራዊ ለባሾቹ የፕሪምየር ሊግ ቆይታ ወሳኝ ነው፡፡
ደደቢት
ደረጃ – 2ኛ
ያለፉት 5 ጨዋታዎች – አሸ – አሸ – አቻ – አቻ – አሸ
ደደቢት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኝ እንደመሆኑ ወጥ አቋም የሚጠበቅበት ቡድን ነው፡፡ ከጅማ አባ ቡና እና ኤሌክትሪክ በተከታታይ ነጥቦች በመጣል መሪነቱን ለማደላደል የነበረውን እድል ቢያመክንም አአ ከተማን አሸንፎ ወደ ድል ተመልሷል፡፡ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍም ሰማያዊዎቹ የሊጉን መሪነት ቢያንስ እስከ ቅዳሜ ድረስ እንዲጨብጡ ያደርጋቸዋል፡፡
ከጨዋታው ምን ይጠበቃል?
በሁለቱም በኩል የተዋሀደ ቡድን አለመያዝ በውድድር ዘመኑ ተስተውሏል፡፡ ደደቢት በተከላካይ ፣ አማካይ እና አጥቂ መስመር ላይ በሚገኙት የተጫዋቾች የተናጠል ብቃት ነጥቦች መሰብሰብ ቻለ እንጂ እንደ ቡድን የተደራጀ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በተመሳሳይ ጥሩ የተጫዋቾች ስብስብ ቢይዝም ከተናጠል እንቅስቃሴ ውጪ እንደ ቡድን ደካማ የውድድር ዘመን እየያሳለፈ ይገኛል፡፡
ከዚህ መነሻነት የተጫዋቾች የተናጠል ብቃት የጨዋታውን ውጤት የመወሰን ብቃት ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በ18 ጎሎች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በመምራት ላይ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ እንደነገሩ የተዋቀረውና በቀላሉ ግቦች የሚያስተናግደው የንግድ ባንክ የተከላካይ መስመርን እንደሚፈትን ሲጠበቅ ካድር ኩሊባሊ የቦታ አጠባበቅ ከፍተኛ ችግር ያለበት የንግድ ባንክ የአማካይ መስመርን በቀላሉ ሊቆጣጠረው ይችላል፡፡ በአንጻሩ በኤሌክትሪክ እና ጅማ አባ ቡና ጨዋታዎች ላይ እንደታየው የደደቢት አራት ተከላካዮች በመካከላቸው ያልተመጣጠነ ስፋት የሚኖር ከሆነ በሚገኘው ክፍተት ፒተር ኑዋዲኬ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡
የእርስ በእርስ ግንኙነት እውነታዎች
ሁለቱ ቡድኖች 15 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ደደቢት 5 ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ድል አስመዝግበዋል፡፡ 8 ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ ደደቢት 16 ፣ ባንክ 11 ጎሎችን አስቆጥረዋል፡፡
– በሁሉም የውድድር ዘመናት ግንኙነት ታሪካቸው በአመቱ ከሚያደርጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አንዱን በአቻ ውጤት እያጠናቀቁ እዚህ ደርሰዋል፡፡ በመጀመርያው ዙር ደደቢት 2-1 ያሸነፈ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ አቻ ከተለያዩ ታሪኩ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
– አቻ ከተለያዩባቸው 8 ጨዋታዎች አራቱ ያለ ግብ የተጠናቀቁ ናቸው፡፡
የቡድን ዜናዎች
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን በቅጣት ይህ ጨዋታ ሲያመልጠው የተጫዋች ጉዳት የለም፡፡ በደደቢት በኩል ሽመክት ጉግሳ ልምምድ ላይ ካጋጠመው ቀላል ጉዳት አገግሞ በዛሬው ጨዋታ ላይ ይሰለፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ኤልያስ ኢብራሂም – ደደቢት
የደደቢት ዋና አሰልጣኝ ስለመሆቸው
ከደደቢት ጋር ከቅድመ ውድድር ዝግጅት ጀምሮ አብሬ ስለቆየሁ የነበረውን ነገር አስቀጥዬ ለመጓዝ እየተንቀሳቀስኩ እገኛለሁ፡፡ አስራት ኃይሌ አሁንም ከክለባችን ጋር የሚቀጥል በመሆኑ ከእሱ እና የክለቡ ሀላፊዎች ጋር በመመካከር እየሰራን እንገኛለን፡፡ እኔም ቡድኑ ባለው ነገር ላይ ተመስርቼ ውጤታማነቱን ለማስቀጠል እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ መሻሻል
የማጥቃት አጨዋወትን ለማሻሻል ስልጠናው እና ሲስተሙ ቢኖርም ዋናው ቁልፍ ያለው ተጫዋቾቹ ጋር ነው፡፡ በተጫዋቾቹ ላይ በመስራት ለማሻሻል ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡ የአማካይ ተጫዋቾችን ቁጥር ቀንሰን የአጥቂዎቹን ቁጥር በማበራከት በተሻለ ውጤታማ ለመሆን እንጥራለን፡፡
ስለ ጨዋታው
በወራጅ ቀጠና ውስጥ ከሚገኙ ክለቦች ጋር መጫወት ፈታኝ ነው፡፡ ሆኖም የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገን ለማሸነፍ ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፡፡
ክለቡ በርካታ ጨዋታ አአ ላይ ማድረጉ በሊጉ ጉዞ የሚኖረው አስዋጽኦ
በእኛ በኩል ለሁሉም ጨዋታ (በሜዳም ከሜዳም ውጪ) ተመሳሳይ ግምት ነው የምንሰጠው፡፡ ሆኖም የሜዳ አድቫንቴጅ በመጠቀም የተሻለ ደረጃ ለመድረስ እንጥራለን፡፡
አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የአርባምንጩ ድል የሚፈጥረው መነሳሳት
አሁን በወራጅ ቀጠና ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ በተደጋጋሚ ውጤት ማጣታችንም በስነልቦናው ረገድ ጫና ፈጥሮብን ኀበር፡፡ የአርባምንጩ ድል ከሜዳ ውጪ የተገኘ እንደመሆኑ በተጫዋቾቻችን ላይ ጥሩ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡
ስለ ጨዋታው
ለእኛ በሊጉ ለመቆየት ቀሪዎቹ ጨዋታዎች ላይ ነጥቦች መሰብሰብ ያስፈልገናል፡፡ ከደደቢት በላይ ጨዋታው ለኛ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ተጫዋቾቹም ለማሸነፍ ዝግጁ ሆነዋል፡፡
የአቀራረብ እና የተጫዋቾች ተደጋጋሚ ለውጦች
ቡድናችን ከፍተኛ ችግር የነበረበት ቡድን ነው፡፡ በቀላሉ ግቦች ይቆጠሩብን ነበር፡፡ በአማካይ ክፍሉ በቁጥር በርካታ ተጫዋች ብንይዝም በጉዳት እንደምንፈልጋቸው አላገኘናቸውም፡፡ የአጥቂ መስመራችንም ደካማ ነበር፡፡ በዝውውር መስኮቱ አዳዲስ ተጫዋቾች ቡድኑን እንደመቀላቀላቸው ወደ አንድ የተስተካከለ ቡድን ለመምጣት ተደጋጋሚ ለውጦችን ስናደርግ ቆይተናል፡፡ አሁን ወደ ፎርሙ እየመጣን ስለሆነ እንደከዚህ ቀደሙ ለውጦች ይኖራሉ ብዬ አላስብም፡፡
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ኢማኑኤል ፌቮ
ፍቃዱ ደነቀ – ቢንያም ሲራጅ – ግርማ በቀለ – ሮቤል ግርማ
ጥላሁን ወልዴ – ጋብሬል አህመድ – ደረጄ መንግስቱ – ቢንያም በላይ
ቢንያም አሰፋ – ፒተር ኑዋዲኬ
ደደቢት
ክሌመንት አዞንቶ
ስዩም ተስፋዬ – አይናለም ኃይለ – አክሊሉ አየነው – ብርሀኑ ቦጋለ
ካድር ኩሊባሊ – ሳምሶን ጥላሁን
ሽመክት ጉግሳ – ሮበን ኦባማ – ኤፍሬም አሻሞ
ጌታነህ ከበደ