በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሲዳማ ቡና ባልተጠበቀ መልኩ በሊ ጉ ዋንጫ ፉክክር ውስጥ ይገኛል፡፡ የይርጋለሙ ክለብ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ተከታዩ ደደቢት ቀጥሎ በእኩል 39 ነጥብ በሊጉ የሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ለሲዳማ በተለይ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ጥንካሬን ይበልጥ ያላበሰው የኃላ መስመሩ ነው፡፡ በሜዳው አንድም ጨዋታ ላልተሸነፈው ሲዳማ በተከላካይነት ወጥ የሆነ ብቃት ከሚያሳዩ ተጫዋቾች መካከል በዓመቱ መጀመሪያ ክለቡን የተቀላቀለው ኬንያዊው ሰንደይ ሙቱኩ እና ሃይቲያዊው ሳውሬል ኦልሪሺ ይጠቀሳሉ፡፡ ተጫዋቾቹ ስለሲዳማ የዋንጫ ተስፋ እንዲሁም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እያሳለፉት ስለሚገኘው የእግርኳስ ህይወታቸው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
“ሲዳማ ቡና አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ብሎ የጠበቀ የለም” ሳውሬል ኦልሪሽ
ስለሲዳማ በሁለተኛ ዙር መሻሻል
“በህይወት ውስጥ ሁሉም ነገር የሚሳካው ቀስበቀስ ነው፡፡ በመጀመሪያው የሊጉ ዙር የተደራጀ ቡድን ይዘን ለመቅረብ ነበር ሙከራችን፡፡ በሁለተኛው ዙር አሰልጣኛችን ጥሩ ስራ ሰርቷል፡፡ የቋሚ አሰላለፍ ውስጥ መግባት ያለባቸውን ተጫዋቾች መለየት መቻሉ ለመሻሻላችን አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ሌላው የመሻሻላችን ምክንያት ሁሉም ተጫዋቾች እንደአንድ ጠንካራ ቤተሰብ ነው፡፡ ሁሉም እርስበርስ ይግባባል፡፡ የቤተሰብነት ያህል ቀረቤታ በተጫዋቾች መካከል መፈጠሩ ለውጤታችን መሻሻል አይነተኛ ምክንያት ነው፡፡”
ስለ ተከላካይነት እና አማካይነት ሚናው
“ሁሌም በየትኛውም የሜዳ ክልል መጫወት ለእኔ ቀላል ነው፡፡ እኔ በበኩሌ የተሻለ ምቾት የሚሰጠኝ በአማካይነት ስጫወት ነው፡፡ በመጀመሪያው ዙር በተለይ በሁለቱም መስመሮች በተከላካይነት ተሰልፊያለው፡፡ አሰልጣኜ በሚሰጠኝ ቦታ ላይ ተሰልፌ እጫወታለው፡፡ በሁለተኛው ዙር መጀመር በኃላ ግን በተለይ በአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ያሳየሁትን እንቅስቃሴ ተከትሎ አሰልጣኛችን በአማካይ ስፍራ እንድጫወት አድርጎኛል፡፡ ምቾት በሚሰማኝ ቦታ በመጫወቴ ደስተኛ ነኝ፡፡”
ስለሊግ ዋንጫ ግስጋሴ
“አሁን ላይ እየተጫወትን ያለነው ለዋንጫ ነው፡፡ አሁን ላይ ያለን ነገር ጥሩ መሆኑ ሁላችንም የተለየ ነገር ሰርተን ሰዎችን ማስደነቅ እንዳለብን እንድናስብ አድርጎናል፡፡ እውነት ለመናገር ማንም ሲዳማ ቡና አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ብሎ የጠበቀ የለም፡፡ ልምዳ ያለቸው ተጫዋቾችን ልክ እንደሙሉአለም መስፍን፣ ፍፁም ተፈሪ እና ሰንደይ ሙቱኩ የያዘ ስብስብ ስላለን በጠንካራ ስራ ስኬትን ማምጣት እንደሚቻል እናምናለን፡፡ አሰልጣኛችንም (አለማየሁ አባይነህ) እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ዓለማችን እስከመጨረሻው የዋንጫ ተስፋችን ድረስ መታገል ነው፡፡እኔ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁበት ግዜ አንስቶ ሁሌም በሊጉ አናት ላይ ተቀምጦ ዋንጫ የሚወስደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ይህንን የሊግ ዋንጫ ከቅዱስ ጊዮርጊስ መንጠቅ የምንችልበት እድል ለመጠቀም ነው ሃሳባችን፡፡”
ከሀዋሳ ከተማ ጋር ስላለባቸው ወሳኝ የደርቢ ጨዋታ
“ጥሩ ጨዋታ እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡ ሃዋሳ እና ሲዳማ ተቀራራቢ በመሆናቸው የደርቢነት ስሜቱ አለ፡፡ ለእኛም ሆነ ለሀዋሳ ቀላል ጨዋታ አይሆንም፡፡ ለጨዋታ በቂ ትኩረት እና ዝግጅት አድርገናል፡፡ በጨዋታው የሚፈጠረውን መገመት ባልችልም ለእኛ አሁን ላይ ሶስት ነጥብ ማሳካት ግዴታችን ነው፡፡ ስለዚህም ማሸነፍን እና ማሸነፍን ብቻ መሰረት አድርገን ወደ ሜዳ እንገባለን፡፡”
“ታሪክ ለመቀየር ነው የተዘጋጀነው” ሰንደይ ሙቱኩ
በመጀመሪያ የሊግ ቆይታው እያሳየ ስለሚገኘው ብቃት
“ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ማንም አያውቀኝም፡፡ ስለዚህም ያለኝን አቅም እና ብቃት ማሳየት እንዳለብኝ ከመጀመሪያው አስቤ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቴ ጠንከራ ልምምድን እንድሰራ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ አሁን ላይ ላለሁበት ጥሩ አቋም የረዳኝ ጠንካራ ስራ ነው፡፡ ከመደበኛ ልምምድ መልስ በጂም ውስጥ በግሌ እሰራለው፡፡ ከጂም እንቅስቃሴ ጋር ደግሞ የራሴን የግል ከኳስ ጋር የተገናኘ ልምምድ እሰራለው፡፡ ስኬታማ ለመሆን ሁሌም መስራት ያስፈልጋል፡፡”
ከአማካይነት ወደ ተከላካይነት ስላደረገው ሽግግር
“ኬንያ በነበርኩበት ግዜ በአብዛኛው በአማካይነት ነበር የምጫወተው፡፡ አሁን ግን አሰልጣኛችን እኔን ወደ ተከላካይ ስፍራ ወስዶኛል፡፡ በእግርኳስ ሁሌም ተጫዋቾች የሚሰጣቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት አለባቸው፡፡ የሚና ለውጥ የተለመደ ስለሆን ሁሌም ለሚሰጠኝ የቤት ስራ እራሴን አዘጋጃለው፡፡ ተለዋዋጭ መሆን አሁን ላይ በእግርኳስ ስለሚጠይቅ ይህንን ሽግግር በበጎ ጎኑ ነው የተመለከትኩት፡፡ አሰልጣኜ ያዘዘኝ ቦታ ላይ እጫወታለው፡፡”
ስለዋንጫ ፉክክሩ
“ታሪክ ለመቀየር ነው የተዘጋጀነው፡፡ ዋንጫውን ለማንሳት ጥረት እናደርጋለን፡፡ ለዋንጫ የምናደርገው ጉዞ የቀልድ አለመሆኑን በሁለተኛው ዙር ጀምሮ አስመስክረናል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ከፍተኛ ትግል አድርገን በጭማሪ ደቂቃ በተቆጠረብን ግብ ነው የተሸነፍነው፡፡ ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ጥሩ መጓዝ የቻለውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዚህ ሁሉ ደቂቃ መቋቋማችን በጥሩ መልኩ እየተጓዝን እንደሆነ ያሳያል፡፡ በተጫዋቾች መካከል ያለው ህብረት ጥሩ ነው ስለዚህም የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ጥረት ማድረጋችን ይቀጥላል፡፡ ዋንጫ ባናገኝ እንኳን አሁን ላይ ያለንበት ደረጃ እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡”
ስለጠንካራው የሲዳማ የተከላካይ ክፍል
“ሁሉም ተከላካይ ስራው አክብሮ ስለሚሰራ ቡድናችን ጠንካራ የተከላካይ ስፍራ እንዲኖረው አስችሏል፡፡ ጥንካሬ እንዳለን ሆኖ አልፎ አልፎ የምንሰራቸውን ስህተቶች ዋጋ እያስከፈሉን ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ አሁን ላይ ለማሳካት ለምናስበው ውጤት ጥሩ አይደለም፡፡ በተቻለ መልኩ ይበልጥ ለመሻሻል ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በመጀመሪያው ዙር ከሜዳችን ውጪ ብዙ ግቦችን እናስተናግድ ነበር፡፡ ይህም የሆነው የቅንጅት ችግር ስለነበረ ነው፡፡ አሁን ላይ እየዳበረ የሚገኝ ቅንጅት ስላለን ጠንካራ የኋላ መስመር መመስረት ችለናል፡፡”
ስለኬንያ ብሄራዊ ቡድን
“አላማዬ ወደ ሃራምቤ ከዋክብቶቹ ቡድን መጠራት ነው፡፡ አሁን ላይ አሰልጣኛችን (ስታንሊ ኦኮምቢ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የሚከታተልበት አማራጭ ባለመኖሩ ስላለሁበት ሁኔታ መረጃ የላቸውም፡፡ የሊጉ ጨዋታዎች የቴሌቭዢን ስርጭት ስለማያገኙ ይህ እኔን እንዳልታይ አድርጎኛል፡፡ እድሉ ከመጣልኝ ግን አሰልጣኝ ኦኩምቢን እንደማላስከፋ መናገር እችላለው፡፡”