በ23ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናግዳል፡፡ በአራት ነጥቦች የሚለያዩት ሁለቱ ክለቦች (ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አለው) የሚያደርጉት ፍልሚያ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ወሳኝነት አለው፡፡ የኢትዮጵያ ቡና አምበል መስኡድ መሃመድ ስለደርቢ ጨዋታ እና የኢትዮጵያ ቡና ወቅታዊ አቋምን በተመለከ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ስለደርቢው ጨዋታ እና ዝግጁነት
“ትልቅ ጨዋታ ነው ከፊታችን ያለው፡፡ እኛ ደግሞ ተሸንፈን ነው የመጣነው፡፡ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ትልቅ ጨዋታም እንደመሆኑ የተቻለንን በአካል ብቃትም በታክቲካልም ሰርተናል፡፡ የጨዋታውን ቀን እየጠበቅን ነው፡፡ ሁሉንም ጨዋታዎች እኛ ለማሸነፍ ነው የምንጫወተው፡፡ ምንም የተለየ ጫና የሚፈጥርብን ነገር የለም፡፡ ሶስቱን ነጥብ በጣም እንፈልገዋለን፡፡ ለዚህም የሚሆኑ ነገሮችን ሜዳ ላይ መስእዋትነት ከፍለን ነው ማምጣት የምንፈልገው፡፡”
የግብ ማስቆጠር አቋም
“ካለፉት ጨዋታዎች ጀምሮ የሚና ለውጥ አድርጌ ትንሽ ወደ ሳኑሚ ተጠግቼ እንድጫወት ተደርጓል፡፡ ይህም አግዞኛል፡፡ ከማግባት ይበልጥ ደግሞ እድሎችን እየፈጠርኩ ነው፡፡ በቅዳሜ ጨዋታም ግብ የማገባ ይመስለኛል፡፡”
የኢትዮጵያ ቡና በጨዋታዎች ላይ መውጣት እና መውረድ
“ሁልግዜም በአመቱ ወጥ አቋም ማሳየት እንዳለብን እናውቃለን ግን አንዳንድ ግዜ ቡድኖች የጨዋታ አቀረራባቸው ለእኛ ትንሽ ጠንከር የሚሉ ቡድኖች አሉ፡፡ የክልል ጨዋታዎችንም በቀላሉ ማሸነፍ አልቻልንም፡፡ እነዚህ ለወጣ ገባ ውጤቶች ዳርገውናል፡፡”
በብዛት በደርቢ ጨዋታ ላይ መጫወት ስለሚፈጥረው ስሜት
“ጨዋታው ትልቅ ድባብ ያለው ጨዋታ ነው፡፡ የመጀመሪያውንም ስጫወት እኔ የተሰማኝ ስሜት አለ እና እነሱም (በደርቢው ተጫውተው የማያውቁ የቡና ተጫዋቾች) ይህ ስሜት ይኖራቸዋል ብዬ ነው ማስበው፡፡ ለእነሱም ሜዳ ላይ ያለው ነገር ሳይሆን ውጪ ያለው ነገር ከበድ እንደሚል ቀድሜ እነግራቸዋለው፡፡ ከባድ ነው ውጤት ይጠበቅባል ማሸነፍ አለብህ ተቀናቃኝ ቡድን ነው፡፡ ለዛ ብዙ መስዋትነት መክፈል አለብህ፡፡
“በሊጉ ብዙ ግዜ እንሸናነፋለን ወይም አቻ እንወጣለን፡፡ በአሸናፊዎች አሸናፊ ግን በደርሶ መልስ እኛ አሸንፈን ዋንጫ ያነሳንበት ጨዋታ እኔ በጣም ደስ የሚለኝ ነው፡፡ ብልጫም ወስደን ነው ያሸነፍናቸው እሱን አልረሳውም፡፡”