የጨዋታ ሪፖርት፡ መከላከያ ከወራጅ ቀጠናው የራቀበትን ድል ንግድ ባንክ ላይ አስመዝግቧል

 

በ24ኛ ሳምንት የፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ መከላከያ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3-1 በመርታት ከወራጅ ቀጠናው የራቀበትን ድል አስመዝግቧል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አበባ ከተማን 1-0 ያሸነፈው መከላከያ የጨዋታው ብቸኛ ግብ ከመረብ ያዋሃደው ምንይሉ ወንድሙን ከባዬ ገዛኸኝ ጋር በፊት መስመር ሲያጣምር ንግድ ባንክ በደደቢቱ ጨዋታ ቋሚ የነበረውን ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃንን በቢኒያም አሰፋ ተክቶ በሁለት የፊት አጥቂዎች ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ታዬ በግብ ክልሉ ውስጥ አግኝቶ የሞከረውን ኤማኑኤል ፌቨር ሲመልስበት ፒተር ንዋድኬ በሰባተኛው ደቂቃ ያገኘውን እድል ሳይጠቀምበት ኳስን በግቡ አናት ላይ ሰዷታል፡፡

በመጀመሪያው 45 እምብዛም የግብ እድሎች ቡድኖቹ ሲፈጥሩ አልተስተዋለም፡፡ የመስመር ተከላካዮቻቸውም ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ገብቶ ማጥቃቱን የማገዝ ነገርም ፈፅሞ በሁለቱ ክለቦች ላይ አልታየም፡፡ ንግድ ባንኮች ከመስመር ለፒተር እና ቢኒያም በሚሻገሩ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ጦሩ አልፎ አልፎ ወደ ፈጣኖቹ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ኳስን በመጣል የንግድ ባንክን የኃላ መስመር ለመረበሽ ሞክረዋል፡፡

በ16ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ግርማ በቀለ ከፌቨር ጋር ባለመግባባቱ የተፈጠረውን እድል የመከላከያ ተጫዋቾች ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ ጨዋታው ኢላማቸውን ባልጠበቁ ሙከራዎች ታጅቦ ሲካሄድ ቆይቶ በ43ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ደነቀ ጥፋት በመስራቱ ምክንያት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ አስቆጥሮ ጦሩን መሪ አድርጓል፡፡ ቡድኖቹ ለእረፍት ከማምራታቸው አስቀድሞም አዲስ ተስፋዬ በጥሩ ሁኔታ የሞከረው የቅጣት ምት ኳስ ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡

ከእረፍት መልስ ንግድ ባንኮች በማጥቃቱ በኩል ተሸለው መጥተዋል፡፡ በ47ኛው ደቂቃ አቤል ማሞ የቢኒያም በላይን ሙከራ ሲያመክን በ56ኛው ደቂቃ ፒተር የመታውን ኳስ አሁንም አቤል ወደ ውጪ አውጥቶታል፡፡ በተለይ ይህ አጋጣሚ አቤልን ለጉዳት ዳርጎታል፡፡ ከሙከራው በኃላም የመከላከያ ተጫዋቾች የፎር ፕለይን ህግ ጥሶ ግብ ለማግባት በጣረው ፒተር ላይ ቅሬታቸው አስመተዋል፡፡ ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ የነበሩት ንግድ ባንኮች አቻ ለመሆን አራት ደቂቃዎች ብቻ ነው የፈጀባቸው ፤ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ጥላሁን ወልዴ አስቆጥሯል፡፡ ከግብ መቆጠር በኃላ ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ማጥቃታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በ64ኛው ደቂቃ የፒተር ቅጣት ምትም የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡

ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ መከላካያዎች ከሳጥኑ ውጪ ያገኙት ቅጣት ምት ቴዎድሮስ በቀለ አስቆጥሮ የጦሩን መሪነት መልሷል፡፡ በ76ኛው ደቂቃ በንግድ ባንክ ቀኝ መስመር በጥሩ መልኩ ኳስን ይዞ ወደ ሳጥን ይዞ የገባው ፈጣኑ ሳሙኤል ሳሊሶ ያቀበለው ኳስ ተጠቅሞ ምንይሉ ሶስተኛዋን ግብ ከመረብ በማዋሀድ የጦሩን መሪነት ማስፋት ችሏል፡፡ ለግቧ መቆጠር የሳሙኤል ሚና ላቅ ያለ ነበር፡፡

ንግድ ባንኮች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸው ግብ ለማግኘት በተለይም ወደ አደጋ ክልሉ ከመስመር ያደርሷቸው የነበሩ ኳሶች ይህ ነው የሚባል የግብ እድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል፡፡

ድሉን ተከትሎ መከላከያ ደረጃውን አሻሽሎ በ30 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በወራጅ ቀጣናው ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ20 ነጥብ በነበረበት 15ኛ ደረጃ ላይ ቀርቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *