በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ደደቢት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረበት ግብ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ በካታንጋ በተቀመጡ የአዞዎቹ ደጋፊዎች ደምቆ በነበረው ጨዋታ አርባምንጭ ከ2-0 መመራት ተነስቶ ነው ከሜዳው ውጪ አንድ ነጥብ ሊያሳካ የቻለው፡፡
አርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ ጳውሎስ ፀጋዬን አሰናብቶ በምትኩ በረከት ደሙን ጊዜያዊ አሰልጣኝ አድርጎ ለጨዋታው ሲቀርብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጋር ባሳለፍነው ሳምንት ያለግብ አቻ የተለያየው ደደቢት እምብዛም ያልተለወጠ አሰላለፍን ተጠቅሟል፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሰማያዊዎቹ በአዛዎቹ ላይ ጫና ለመፍጠር ቢችሉም የጠሩ የግብ እድሎ ግን በመፍጠሩ በኩል ደካማ ነበሩ፡፡ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ኃላ ያፈገፈጉት አርባምንጮች በታደለ መንገሻ እና እንዳለ ከበደ አማካኝነት ወደ ፊት በሚሄድ ተከላካይ ሰንጣቂ ቅብብሎች ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ለዚህም ማሳያው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ተመስገን ካስትሮ ከእንዳለ እንዲሁም አጥቂው አመለ ሚልኪያስ ከታደለ በ21ኛው እና በ28ኛው ደቂቃ ላይ ያገኟቸው እድሎች ናቸው፡፡
ደደቢት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ብልጫ ቢወስድም በ6ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ በቅጣት ምት የሞከረው ሙከራ ጃክሰን ፊጣ በቀላሉ ይዞበታል፡፡ ስዩም ተስፋዬ ከመስመር በጥሩ መልኩ ያቀበለውን ኳስ ኢኳቶሪያል ጊኒያዊው ሮበን ኦባማ በ16ኛው ደቂቃ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በ30ኛው ደቂቃ ታደለ በደደቢት ቀኝ መስመር አከባቢ የተገኘውን ቅጣት ምት ወደ ግብ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ሲወጣበት የቀድሞው የደደቢት ተጫዋች በ36ኛው ደቂቃ ዳግም ከቅጣት ምት የሞከረው ሙከራ የግብ አግዳሚ ገጭቶበታል፡፡ ለእረፈት ሁለቱም ክለቦች እስኪያመሩ በነበረበት የጨዋታ ክፍለ ግዜ የግብ ሙከራዎች አልተስተናገዱም፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ 4 ግቦች እና በደጋፊዎች በተወረወሩ ቁሶች ምክንያት የተቋረጠ ጨዋታን አስመልክቶናል፡፡ ከእረፍት መልስ ደደቢቶች ሽመክት ጉግሳ እና ዳዊት ፍቃዱን በሰለሞን ሃብቴ እና ኤፍሬም አሻሞ ቀይረው አስገብተዋል፡፡ ይህንን ለውጥ ተከትሎ ዳዊት በፊት መስመሩ ላይ ከጌታነህ ጋር ሲጣመር ኦባማ ወደ ግራ መስመር መጥቷል፡፡ በቀኝ መስመር ላይ ሽመክት ተተክቷል፡፡ ሰማያዊዎቹ ግብ ፍለጋ አሁንም አርባምንጭ ላይ ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ዳዊት በ57ኛው ደቂቃ ከአደጋ ክልሉ ውጪ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ሲወጣበት በ65ኛው ደቂቃ አምበሉ ብርሃኑ ቦጋላ በድንቅ ሁኔታ ከመረብ ያሰረፋት የቅጣት ምት ግብ ደደቢትን መሪ አድርጋለች፡፡
ከግብ መቆጠር በኃላ መረጋጋት ያልቻለው የአዞዎቹ የተከላካይ መስመር ሁለተኛውን ግብ ለማስተናገድ የፈጀበት ደቂቃ ሁለት ብቻ ነው፡፡ የኮከብ ግብ አግቢነቱን የሚመራው ጌታነህ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ደደቢት 2-0 መምራት የቻለበትን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ከግብ መቆጠር በኃላ ሽመክት ላይ ጥፋት ተሰርቶበት የህክምና ባለሙያዎች እርዳታ በሚያደርጉለት ወቅት በካታንጋ ከነበሩ አንዳንድ የአርባምንጭ ደጋፊዎች በተወረወሩ ቁሶች ምክንያት ጨዋታው ለሰባት ያህል ደቂቃች ተቋርጧል፡፡
ጨዋታው ዳግም ሲጀመር ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ወንድሜነህ ዘሪሁን በዘንድሮው የአዞዎቹ የሊግ ጉዞ ላይ ያለውን ተፅዕኖ አሳይቷል፡፡ ወንድሜነህ በ78ኛው ደቂቃ ገብረሚካኤል ያዕቆብ ሞክሮ የደደቢት ተካላካዮች የመለሱትን ኳስ በሳጥኑ ውስጥ አግኝቶ አርባምንጭ ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ አስቆጥሯል፡፡ ነገር ግን በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው እንዳለ በታሪኩ ጎጀሌ መቀየሩን ተከትሎ በተለይ በቀኝ መስመሩ ላይ ክፍተት ታይቷል፡፡ ደደቢቶች የግብ ልዩነቱን ለማስፋት የሚችሉበትን እድል ሳምሶን ጥላሁን በ90ኛው ደቂቃ ላይ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
የተጨመረው ሰባት ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት ታሪኩ ጎጀሌ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ወንድሜነህ አሻምቶ ተመስገን ካስትሮ በክሌመንት አዞንቶ መረብ ላይ በማሳረፍ በስታዲየሙ የተገኘውን የአርባምንጭ ደጋፊ አስፈንጥዟል፡፡
ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ የደደቢቱ አጥቂ ጌታነህ ከበደ በውጤቱ በመበሳጨት ያሳየው ያልተገባ ባህርይ በስፍራው የተገኘውን ደጋፊ ያሳዘነ ሆኖ አልፏል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ደደቢት በነበረበት የሁለተኛ ደረጃ በ41 ነጥብ ይዞ ሊጉን መምራት የሚችልበትን እድል ሲያመክን የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረገው አርባምንጭ በ30 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት በሚከተለው መልኩ ቀርቧል፡፡
ኢልያስ ኢብራሂም – ደደቢት
በተጨማሪ ሰአት በተቆጠረ ግብ አቻ መለያየታቸውን ስለ ፈጠረበት ስሜት
“መሰል ክስተቶች በእግርኳስ ላይ የሚከሰቱ ናቸው ፤ ነገርግን ይህ ውጤት ለኛ የሚገባን አይደለም፡፡በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ልጆቻችን ያላቸውን ሁሉ አውጥተው ሰጥተው ግቦችን ማስቆጠር ችለናል ፤ ነገርግን ግቦችን ባስተናገድን ቁጥር የራስ መተማመናችን እየወረደ መቶ በስተመጨረሻም የሰራናቸውን የተወሰኑ መዘናጋቶች ዋጋ አስከፍለውናል፡፡”
የሊጉን መሪነት ሊጨብጥባቸው የሚችልባቸውን በርካታ እድሎችን ስለማባከን
” በእግርኳስ መሸነፍ ማሸነፍ እንዲሁም አቻ መውጣት ያለ ነገር ነው፡፡ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ላይ ቀድመን ግቦችን እናስቆጥራለን ነገርግን ግቦች ይቆጠሩብናል ፤ በቀጣይ እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ ቡድኑን ወደ ውጤታማነቱ ለመለለስ እንሰራለን፡፡”
ስለ ጌታነህ ከበደ ከጨዋታው በኃላ ሲወጣ ማሊያውን ቀዶ ስለመወርወሩ
“እግርኳስ የስሜት ጨዋታ ነው፡፡ ተጫዋች ሜዳ ውስጥ ደሙ በሚሞቅ ጊዜ በስሜታዊነት የሚከሰት ነገር ነው፡፡”
በረከት ደሙ – አርባምንጭ ከተማ
ስለ ጨዋታው
“ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በሜዳችን ነጥብ በመጣላችን የተነሳ ተጫዋቾቻችን ስነ ልቦና በእጅጉ ተጎድቶ ነበር ፤ በተለያዩ ባለሙያዎች እርዳታና ከተጫዋቾቹ ጋር ባደረግነው ውይይት ከዛ ስሜት ወጥተን በጥንቃቄ ተጫውተን አንድ ነጥብ ይዘን መውጣት ችለናል፡፡”
ቀጣይ እቅድ
” ፈፅሞ የመውረድ ስጋት የለብንም፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩት ጨዋታዎች በራሳችን ስህተቶች ነጥቦችን ለመጣል ተገደድን እንጂ ቡድናችን ለዋንጫ የመፎካከር አቅም የነበረው ቡድን ነው፡፡ አሁንም ጊዜው አረፈደም በቀጣይ አስከ አምስተኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ሆነን ለማጠናቀቅ እንሰራለን፡፡”