የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20 ሳምንት መርሃ-ግብር ሁሉም ጨዋታዎች በአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች ነገ ይካሄዳሉ፡፡ የቻምፒዮንነቱ ነገር የተረጋገጠ የሚመስለው የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀጣይ ሳምንታት ትኩረት ላለመውረድ በሚደረገው ፍልሚያ ላይ ይሆናል፡፡ በ8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርባምንጭ ከነማ እና በ13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሐረር ሲቲ የነጥብ ልዩነት 8 ብቻ በመሆኑ ከወገቡ ጀምሮ በሚገኙ ክለቦች መካከል የሚደረገው ፉክክር አጓጊ መልክን ይዟል፡፡

የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያን የሚገጥምበት ጨዋታ የሳምንቱ ታላቅ ፍልሚያ ነው፡፡ ከፈረሰኞቹ በእጥፍ ነጥቦች አንሶ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መከላከያ ይህን ጨዋታ አድርጎ ለናይል ተፋሰስ ሃገራት የክለቦች ሻምፒዮና ወደ ሱዳን የሚያቀና በመሆኑ ጨዋታውን እንደመነሳሻ ይጠቀሙበታል፡፡ ፈረሰኞቹ ቀደም ብለው ቻምፒዮንነታቸውን ለማረጋገጥና ታሪክ መስራት ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡

-ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህንን ጨዋ አሸንፎ ኢትዮጵያ ቡና ይርጋለም ላይ ተሸንፎ ከተመለሰ ፈረሰኞቹ 6 ጨዋታ እየቀራቸው የሊጉን ሻምፒዮንነት ያውጃሉ

ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና ወደ ይርጋለም አምርቶ ሲዳማ ቡናን ይገጥማል፡፡ በደርቢው ሽንፈት የቻምፒዮንነት ህልማቸው የጨለመው አደገኞቹ ወደ ይርጋለም የሚያቀኑት ምናልባትም 2ኛ ደረጃቸውን ለማስከበር ይሆናል፡፡

-ሲዳማ ቡና ዘንድሮ በሜዳው የተሸነፈው 1 ጊዜ ብቻ (በሀዋሳ ከነማ) ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ወደ ደቡብ ባደረጋቸው 4 ጉዞዎች ምንም ድል አላስመዘገበም፡፡ (በወላይታ ድቻ ሽንፈት ፣ ከአርባምንጭ ከነማ እና ሐዋሳ ከነማ አቻ)

በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ደደቢት ከኢትዮጵያ መድን በ11፡30 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይገጥማል፡፡ ጨዋታው በሳምንቱ መጀመርያ በኢትዮጵያ ዋንጫ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ከተቀላቀለው ደደቢት ይልቅ በ9 ነጥቦች የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ለሚገኘው ኢትዮጵያ መድን ወሳኝ ነው፡፡ ላለመውረድ በሚደረገው ፍልሚያ ጭላንጭል ተስፋ ያለው መድን ይህንን ጨዋታ ካላሸነፈ ነገሮች አስቸጋሪ ይሆኑበታል፡፡

-መድን ዘንድሮ ያሸነፈው አንድ ጨዋታ ብቻ ነው፡፡ ይህም የነገው ተጋጣሚው ደደቢትን በኢብራሂም ሁሴን እና ወሰኑ አሊ ግቦች 2-1 ያሸነፈበት ነው፡፡ ደደቢት 2ኛው ዙር ከገባ ምንም ጨዋታ አላሸነፈም፡፡

ፋሲለደስ ላይ ዳሽን ቢራ ሀዋሳ ከነማን ያስተናግዳል፡፡ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ዳሽን ቢራ በሜዳው እንደመጫወቱና ሀዋሳ ከነማም የመውረድ ስጋትም ሆነ የሻምፒዮንነትም ተስፋ የሌለው እነደመሆኑ ለጎንደሩ ክለብ መልካም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል፡፡

ሌላው ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ ውስጥ የሚገኘው ሐረር ሲቲ ወላይታ ድቻን ይገጥማል፡፡ ምንም እንኳን ሐረር ሲቲ 13ኛ ደረጃ ላይ ቢገኝም ከወላይታ ድቻ ጋር ያለው ልዩነት የ7 ነጥቦች ብቻ በመሆኑ ከድቻ ከባድ ፉክክር ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ መብራት ኃይልን የሚያስተናግድበት ጨዋታም በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የደረጃ ለውጥ ሊያመጡ ከሚችሉ ፍልሚያዎች አንዱ ነው፡፡

አሰላ ላይ ንግድ ባንክን የሚያስተናግደው ሙገር ሲሚንቶ ወደ ወራጅ ቀጠናው ላለመግባት ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ 22 ነጥቦች የያዘው ሙገር ይህንን ጨዋታ ተሸንፎ ከስሩ የሚገኙት ክለቦች ካሸነፉ 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ክለብ ያለው ርቀት 3 ብቻ ይሆናል፡፡

ከደደቢት እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታዎች ውጪ ሁሉም ጨዋታዎች በተመሳሳይ 9፡00 ላይ ይደረጋሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *