ኡመድ ኡኩሪ አል አህሊ ላይ ግብ አስቆጥሯል

በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ መሪው አል አህሊን የገጠመው ኤል ኤንታግ ኤር ሃርቢ በኡመድ ኡኩሪ ግብ ታግዞ 1-1 አቻ ተለያይቷል፡፡ ኡመድ በውድድር ዘመኑ 8ኛ የሊግ ግቡን ነው በምሽቱ ጨዋታ ማስቆጠር የቻለው፡፡

አል አህሊ የተሻለ የመሃል ሜዳ ብልጫ በወሰደበት ጨዋታ በተደጋጋሚ በሚሰሩ ጥፋቶች ምክንያት የዳኛ ፊሽካ የበዛበት ነበር፡፡ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በመጀመሪያው አጋማሽ በሳላ አሚን አማካኝነት ወደ ግብ ከሞከረው ኳስ ውጪ አህሊዎች በሙከራም የተሻሉ ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በ47ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ በአል አህሊ ተከላካዮች በአግባቡ ያልተያዘው ኡመድ ኡኩሪ በግንባሩ በመግጨት ሻሪፍ ኤክራሚ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡

የካይሮው ሃያል አቻ ለመሆን ብዙ ደቂቃዎችን መጠበቅ አላስፈለገውም፡፡ ናይጄሪያዊው አጥቂ ጁኒየር አጄዬ አስቆጥሮ ውጤቱን 1-1 አድርጎታል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላም ኤል ሃርቢዎች በመከላከል እንዲሁም አህሊዎች የማሸነፊያ ግብ ለማግኘት ተጠምደው አምሽተዋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም የአህሊው ሆሳም አሹር የጨዋታውን ዳኛ እጅ በመጎተቱ የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል፡፡

ኡመድ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ያሰቆጠራቸውን የግቦች መጠን ወደ 8 ከፍ በማድረግ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ የሊግ ግቦች በግብፅ ያስቆጠረ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ሆኗል፡፡ የቀድሞ የመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ተሰላፊ በውድድር ዓመቱ ላይ ሁለቱ የካይሮ ባላንጣዎች አል አሃሊ እና ዛማሌክ ላይ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ኡመድ አሃሊ ላይ የሊግ ግብ ሲያስቆጥር ይህ ሁለተኛው ግዜ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትሃድ አሌክሳንደሪያ ቆይታው ክለቡ አል አሃሊን 4-1 በረታበት ጨዋታም ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡


የኡመድን ጎል ይመልከቱLINK


በሌላ በኩል ባሳለፍነው ሐሙስ የሽመልስ በቀለው ፔትሮጀት ከኤል ናስር ለል ታደን ጋር ተጫውቶ በሜዳው 1-0 ተሸንፏል፡፡ የእንግዶቹን ግብ አብዱላዚዝ ኢማም በሁለተኛው አጋማሽ አስቆጥሯል፡፡ ሽመልስ በጨዋታው ላይ ለ50 ደቂቃዎች ያህል ተጫውቶ በናስር መሃል ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

ሊጉን አሁንም አል አህሊ በ68 ነጥቦች ሲመራ ምስር አል ማቃሳ በ11 ነጥቦች አንሶ ሁለተኛ ነው፡፡ ፔትሮጀት በ37 ነጥብ 7ኛ ላይ ሲቀመጥ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ከወራጅ ቀጠናው በአምስት ነጥቦች ከፍ ብሎ በ25 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *