በ26ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አብዛኞቹ ተከታዮቹ ነጥብ የጣሉለት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሀዋሳ ከተማን አስተናግዶ በሳላዲን ሰይድ ብቸኛ ጎል በማሸነፍ ከተከታዩ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ሶስት አድርሶ ሊጉን መምራቱን ቀጥሏል ።
በተለመደው ልዩ የደጋፊዎች ድባብ እና በደመናማ የአየር ሁኔታ ታጅቦ የተካሄደው የዕለቱ ጨዋታ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ የታየበት ነበር ። በተለይም በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች እና ፈጠን ያሉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች መመልከት ችለናል ። በአራተኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር አጥቂነት የተሰለፈው ባለድንቅ ግራ እግር ባለቤቱ ጋዲሳ መብራቴ ወደግራ አጥብቦ በመግባት የመታው እና የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል ። ሆኖም የሀዋሳዎች የወትሮው የመሀል ሜዳ የኳስ ንክኪ የበዛበት አጨዋወት የቅዱስ ጊዮርጊስን የተከላካይ መስመር ሰብሮ ለመግባት ሲሳነው ታይቷል ። ካለመጠን የተጠጋጋው የመስመር አጥቂዎቹ እና የመሀል አማካዮቹ እንቅስቃሴ ኳሶች አብዛኛውን የሜዳ ክፍል አቋርጠው አጥቂው ጃኮ አራፋት ጋር ከመድረሳቸው በፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ አማካዮች በቀላሉ እንዲቋረጡ ምክንያት ሲሆንም ታይቷል ። ጃኮም በጊዮርጊስ የመሀል ተከላካዮች መሀከል እና አልፎ አልፎ ወደ መስመሮች እየወጣ ጥሩ ቢንቀሳቀስም በቂ አቅርቦት ከአማካይ መስመሩ ማግኘት ግን አልቻለም ። ሆኖም ሀዋሳዎች ግብ አያስቆጥሩ እንጂ ሌሎች ሙከራዎችን ግን ማድረጋቸው አልቀረም ። በተለይም 23ተኛው ደቂቃ ላይ ጋዲሳ መብራቴ ከ ፍሬው ሰለሞን የተሰነጠቀለትን ድንቅ ኳስ ይዞ ወደውስጥ በመገባት የሞከረው እና ዘሪሁን ያዳነበት አጋጣሚ በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው ። ከዚህ ውጪም ሀዋሳዎች በዳንኤል ደርቤ እና በጃኮ አራፋት አማካይነት ከሳጥን ውጪ ጠንካራ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ።
የሀዋሳዎች የተከላካይ መስመር በእጅጉ ወደመሀል ሜዳ መጠጋቱ ጊዮርጊሶች መሀል ሜዳ ላይ የሚነጥቋቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደፊት በመጣል እና ለሳላዲን በማድረስ ከሀዋሳ የመጨረሻ ተከላካዮች እስከ ሳሆሆ ሜንሳ ያለውን ክፍተት በተደጋጋሚ ለመጠቀም ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል ። በ5ኛው ደቂቃ ላይም ለሳላዲን የተጣለውን ኳስ ሳሆሆ ቀድሞ ደርሶ ሲያወጣበት ከ10 ደቂቃዎች በኋላ ግን በተመሳሳይ መንገድ ከቀኝ መስመር የተነሳውን እና የሀዋሳ ተከላካዮች አለመናበብ የታየበትን ኳስ ሳላዲን ሳሆሆን በማለፍ የጨዋታው ብቸኛ ግብ አድርጓታል ።
ከግቡ መቆጠር ሁለት ደቂቃ ቀደም ብሎ ሳላዲን ከቀኝ መስመር በኩል ከ ኒኪማ የተሻገረለት እና በቅርብ ርቀት ሞክሮ የግቡ ቋሚ ያወጣበት አጋጣሚም በተመሳሳይ መንገድ የሚጠቀስ ነበር ። ከዚህ ውጪ የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ከፊታቸው የነበረውን ሰፊ የሜዳ ህፍል ከኋላ በሚላኩ ኳሶች ለማቋረጥ ያደርጉ የነበረው ጥረት በሀዋሳዎች የጨዋታ ውጪ ወጥመድ ምክንያት ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም ።
ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ በመጠኑ ከመጀመሪያው ቀዝቀዝ ያለ እና ከጨዋታው ፍሰት ይልቅ አወዛጋቢ የዳኛ ውሳኔዎች የተየበት ነበር ። በዚህም ረገድ የሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች በተደጋጋሚ በአልቢትሩ ላይ የነበራቸውን ተቃውሞ ለመታዘብ ተችሏል ። እንደመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ሰዐት በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ማሳለፍ የተሳናቸው ሀዋሳዎች ሰዐት በገፋ ቁጥር እየተዳከሙ ሄደዋል ። መዳኔ ታደሰን እና ፍርዳወቅ ሲሳይ የመሳሰሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጨዋቾች በማስገባት እንዲሁም የመስመር አጥቂዎቻቸውን ጋዲሳ መብራቴን እና ዮሀንስ ሴጌቦን ቦታ በመቀያየር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም የአቻነቷን ግብ ማግኘት ግን አልቻሉን ። በተወሰኑ አጋጣሚዎች ያገኟቸውን የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችም ከግብ ለማድረስ ተቸግረው ታይተዋል ።
በተነሳሳይ በሳላዲን ጎል መሪ መሆን የቻሉት ጊዮርጊሶች 60ኛው አቂቃ ላይ ሳላዲን ከቀኝ መስመር አሻምቶ አዳነ በግንባሩ ሲገጭ ወደላይ ከተነሳበት ጥሩ ሙከራ ውጪ ግልፅ የማግባት ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ታይተዋል ። ሆኖም የደጉ ደበበ እና የተስፋዬ አለባቸው ወደሜዳ መግባት ቡድኑ ተጋጣሚውን ከመሀል ሜዳ እንዳያልፍ አድርጎ እና ጥቃቱን ተቆጣጥሮ ጨዋታውን እንዲጨርስ ረድቶታል ። በዚህም አኳኋን የተገኙት ሶስት ነጥቦች ክለቡን ለሻምፒዮንነት እንዲቃረብ አድርገውታል ። ሀዋሳዎች በበኩላቸው በሁለተኛው ዙር ላይ እያሳዩ ከነበረው መልካም አቋም በተቃራኒ ወደታችኛው ዞን ለማሽቆልቆል ተገደዋል ።