ሉሲዎቹ ከናሚቢያ አፍሪካ ዋንጫ የ180 ደቂቃዎች መንገድ ቀርቷቸዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በናሚቢያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 9ኛው የአፍሪካ ሴቶች ሻምፒዮን ሺፕ የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታውን አሁድ ያደርጋል፡፡

በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚሰለጥነው የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከናሚቢያ እና ከካሜሩን ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ጨምሮ ከበርካታ የሀገር ውስጥ የታዳጊ እና የወጣት ቡድኖች ጋር የአቋም መለኪያ ያደረጉ ሲሆን እንደ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ገለፃ ስለ ጋና ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የቻሉትን ያህል መረጃዎችን ሰብስበዋል፡፡ ‹‹ ቡድኑ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በምስል የተደገፈ ማስረጃ ለማግኘት ያደረግኩት ጥረት ባይሳካም ለመጨረሻ ጊዜ ከደቡብ አፍሪካ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ሪፖርት በማንበብ መጠነኛ መረጃ ለማግኘት ሞክሬያለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ያደረጓቸውን ልምምዶችም ተመልክቻለሁ ›› ሲሉ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኙ ጨምረው እንደገለፁት በጨዋታው የሚሰለፉ ተጫዋቾችን መርጠው ጨርሰዋል፡፡

‹‹ከናሚቢያ እና ካሜሮን ጋር ባደረግናቸው ጨዋታዎች የተሰለፉት ተከላካዮችን በዚህም ጨዋታ እጠቀምባቸዋለሁ፡፡ በአጥቂ ስፍራ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኙት ሽታዬ ሲሳይ ፣ ሎዛ አበራ እና ረሂማ ዘርጋ በቋሚ አሰላለፉ ይካተታሉ፡፡ ››

የሉሲዎቹ ምክትል አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በበኩላቸው ትኩረታቸው በሙሉ በጋናው ጨዋታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ የመጨረሻ ግባችን ናሚቢያ ቢሆንም ሙሉ የቡድኑ አባላት ሙሉ ትኩረት ከፊታችን ያለው የጋና ብሄራዊ ቡድን ላይ ነው፡፡ በሁለቱ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ያየናቸውን ድክመቶች አስተካክለን እንገባለን፡፡ እኔ በሴቶች እግርኳስ ጋር ባለኝ ልምድ ላይ የስዩም ብቃት ታክሎበት ጥሩ ቡድን እየሰራን ነው፡፡ ›› ብለዋል፡፡

ሉሲዎቹ በመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ ከደቡብ ሱዳን ጋር ተደልድላ የነበረች ሲሆን ደቡብ ሱዳን ከውድድሩ ራሷን በማግለሏ ኢትዮጵያ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች፡፡

ጨዋታው በ10 ሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲደረግ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በኢቴቪ – 3 በቀጥታ ያስተላልፋል፡፡ {jcomments on}

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *