” ቡድኑ እንደማይወርድ አምነን ነው የምንጫወተው ” ኄኖክ ካሳሁን

ኄኖክ ካሳሁን በውድድር ዘመኑ አጋማሽ አዳማ ከተማን ለቆ በውሰት ወደ ጅማ አባ ቡና ካመራ ወዲህ መልካም ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል፡፡ ጠንካራው የተከላካይ አማካይ በደደቢት እና አዳማ ስላሳለፈው ጊዜ እንዲሁም ስለ ጅማ አባ ቡና ቆይታው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

በደደቢት እና በአዳማ ከተማ ብዙም የመሰለፍ እድል አላገኘህም..

ደደቢት እያለሁ እጫወት ነበር። 2006 ከተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን እንዳደኩኝ አልተጫወትኩም ነበር። ሆኖም በቀሩት ሁለት አመታት ብዙ ባይባልም በቂ የመጫወት እድል አግኝቼ ተጫውቻለው። በአዳማ ከተማ ግን የመጫወት አቅም እያለኝ በአሰልጣኙ ውሳኔ ነው ያልተጫወትኩት ይህን ደግሞ አሰልጣኙ ቢመልሰው ጥሩ ነው። እኔም የመጫወቱ አቅሙ እንዳለኝ ስለማውቅ ነው ከአዳማ ለቅቄ ጅማ አባ ቡና ላመራ የቻልኩት። ያልተጫወትኩትም በአቋም ችግር እንዳልሆነ በሁለተኛው ዙር በሚገባ ማሳየት ችያለው ብዬ አስባለው።

ወደ ጅማ አባቡና ካመራህ ጀምሮ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍክ ነው። ይህን እንዴት ትገልፀዋለህ?

አሁን በጅማ አባቡና እያሳለፍኩት ባለው ጊዜ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከክሪዚስቶም ንታንቢ ፣ ሀይደር ሸረፋ እና ዳዊት ጋር ባለኝ ጥምረትም ደስተኛ ነኝ። በአጠቃላይ ስብስባችን በጣም ጠንካራ ነው። እናንተም እንዳያችሁት ቡድኑ አቅም አለው ፤ በአንዳንድ ጥቃቅን ችግሮች ምክንያት ነው እዚህ ደረጃ እንዲገኝ ያደረገው እንጂ ቡድናችን አቅም ባላቸው ተጨዋቾች የተሞላ ነው። አሰልጣኛችንም በሚሰጠን ስልጠና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ያለን ነገር አሪፍ ነው ።

ሁሉም ጨዋታዎች ላይ ያሳየኸው እንቅስቃሴ መልካም ነው። ሆኖም ከደደቢት እና ከአዳማ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ የተለየ ስሜት ፣ ፍላጎት እልህ ይታይብህ ነበር። ምናልባት በውስጥህ የፈጠረብህ ስሜት አለ ከሁለቱ ቡድኖች ጋር ስትጫወት?

ደደቢት ያደኩበት እና የቆየሁበት ቡድን ነው ። ከዚህ ውጭ ሌላ ቡድን አልተጫወትኩም ነበር። አዳማም ቢሆን የመሰለፍ እድል አላገኘሁም እንጂ የነበርኩበት ቡድን ነው። ያው የነበርክበትን ቡድን ስትገጥም እና የወጣህበት ሁኔታ ብዙ የማያሳምንህ ሲሆን በውስጥህ የሚፈጥርብህ ነገር ይኖራል። እሱ ሊሆን ይችላል የተለየ ነገር የፈጠረብኝ። ያም ቢሆን ግን የተለየ ነገር አላደረኩም ፤ ከሁሉም ቡድን ጋር ስጫወት እንደዛው በእልህ በአልሸነፍ ባይነት ነው የተጫወትኩት።

ጅማ አባ ቡና ላለመውረድ እየተጫወተ ይገኛል። በቀሩት 3 ጨዋታዎች ከቡድን አጋሮችህ ጋር በመሆን ቡድኑ እንዳይወርድ ምን እየሰራችሁ ትገኛላችሁ?

እስካሁን ድረስ እኛ ቡድኑ እንደማይወርድ እና እንደሚተርፍ አምነን ነው የምንጫወተው። እየተጫወትን ያለንውም ይህን አምነን ነው። ጥሩ ነገርም እያሳየን እንገኛለን። በዚህ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ጫና ላይ ሆነን እንዲህ መጫወት ከቻልን ከዚህ የተሻለ ነገር ካገኘን ደግሞ ትልቅ ነገር መስራት እንችላለን። ቡድኑንም በፕሪሚየር ሊጉ ለማቆየት ጠንክረን እንሰራለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *