የ2017 ቶታል አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ውድድር ዛሬ በሚደረጉ 5 ጨዋታዎች ሲጀመር ቅዳሜ ምድብ ውስጥ በመግባት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ክለብ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንቶ ከአምናው የአፍሪካ ሻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር የሚጫወት ይሆናል።
የማሜሎዲ ሰንዳውንስ አሠልጣኝ ፒትሶ ሞሲማኔ ለደቡብ አፍሪካ እና ዓለምአቀፍ ሚድያዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም በጨዋታው ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አሠልጣኙ በመግለጫው በደቡብ አፍሪካ ሊግ እና የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እየተሳተፈ ያለው ክለባቸው ላይ ጨዋታዎች መደራረባቸው በቡድኑ ውጤት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል ነው የተናገሩት።
“ካለፈው ዓመት ሰኔ ጀምሮ 60 ጨዋታዎችን አድርገናል። እኛ ስንጫወት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች እረፍት ላይ ሆነው እያዩን ነበር። በደቡብ አፍሪካ ሊግ እና በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ሻምፒዮን ለመሆን መጫወት የጨዋታ መደራረብ ስለሚያመጣ ቀላል አይደለም። አሁን በየ3 ቀን ልዩነት እየተጫወትን ነው፤ የተጫዋቾች ጉዳት እና ቅጣት ዕቅዳችንን ሊያበላሽብን ይችላል። በክለባችን ውስጥ በቋሚነት እየተሰለፉ ያሉ ተጫዋቾችን በከፊል በማሳረፍ ጉልበታቸው ያልተዳከመ ልጆችን መጠቀም ይኖርብናል።”
አሠልጣኙ ምንም እንኳን ወሳኝ የሆኑ ተጫዋቾችን በጨዋታው ላይጠቀሙ እንደሚችሉ ቢናገሩም ጠንካራ እና ጨዋታውን ማሸነፍ የሚችል ቡድን በሜዳ ላይ እንደምንመለከት ገልፀዋል።
“የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግን በመጥፎ ውጤት ላለመጀመር እና በሜዳችን የምናደርጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ማሸነፍ ስለምንፈልግ ጠንካራ ቡድን እናሰልፋለን። ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ እና በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ምድብ ውስጥም ለመጫወት የሚመጥን ቡድን ነው። በሚኖረን ጨዋታ ላይም ክለቡ ምንያህል ጠንካራ እንደሆነ ሁሉም የሚያይ ይመስለኛል። ብዙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታዎችን በቪድዮ ማግኘት ባልችልም በተወሰነ መልኩ ቡድኑን አይቼዋለሁ። ኳስ የሚይዝ እና በህብረት የሚጫወት ቡድን ነው። የሚመጡት ከከፍታ ስፍራ ስለሆነ እና እንደሀገርም በሩጫ ስለሚታወቁ ጨዋታው ፈታኝ ይሆናል።”
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እስካለፈው ዓመት ድረስ በአፍሪካ ውድድር ብዙም ታሪክ ያልነበረው ቢሆንም አምና በማጣሪያው ላይ የኮንጎው ኤኤስ ቪታ ያልተገባ ተጫዋች በማሰለፉ ምክንያት መቀጣቱን ተከትሎ ወደ ምድቡ መግባት ችሏል። ሰንዳውንስ በቀሪ ጨዋታዎችም ድንቅ አቋም በማሳየት ባልተጠበቀ ሁኔታ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳት ችሏል። ከአምናው ታሪካዊ ጉዞ በኋላ ቡድኑ በአፍሪካ ዙሪያ ታዋቂ መሆኑ ሌሎች ክለቦች አጨዋወታቸውን እንዲያጠኑ እንዳደረገም አሠልጣኙ ጨምረው ተናግረዋል።
“ቡድናችን አምና ብዙም ስለማይታወቅ አጨዋወታችንም ተገማች ስላልነበረ ጠቅሞናል። ይህ ግን ዘንድሮ የለም፤ ሁሉም ተጋጣሚዎቻችን በደንብ ስለሚያውቁን ጨዋታዎቻችንን በቴሌቪዥን ይከታተላሉ። ይህ ቢሆንም እኛ ከአምናው ይልቅ በአፍሪካ ውድድር ልምድ አካብተናል፤ ከአምናው በተሻለም ሰፊ እና በርካታ አማራጮች ያለው ቡድን አለን።”
የ52 ዓመቱ ፒትሶ ሞሲማኔ እ.ኤ.አ. በ2012 የፕሪቶሪያውን ክለብ በዋና አሠልጣኝነት ከያዙ በኋላ 2 የደቡብ አፍሪካ ፕሪምየር ሶከር ሊግ፣ 1 ኔድባንክ ዋንጫ፣ 1 የቴልኮም ጥሎማለፍ ዋንጫ እንዲሁም በአፍሪካ መድረክ የቻምፒዮንስ ሊግ እና ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን በማንሳት ውጤታማ ጊዜ ያሳለፉ ሲሆን የ2016 የአፍሪካ ምርጥ አሠልጣኝ በሚልም የካፍ ሽልማት አሸናፊ ነበሩ። ከሰንዳውንስ በፊት የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድንን ሲያሰለጥኑ የነበሩት ፒትሶ ሞሲማኔ በ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ረስተንበርግ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር 1-1 ከተለያዩ በኋላ ከስራቸው መሰናበታቸው ይታወሳል።