የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የደደቢት ተጫዋቾች ስለነገው ወሳኝ ፍልሚያ ይናገራሉ 

የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ነገ በ10፡00 አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ፍፃሜውን ያገኛል፡፡ በዚህም በ52 ነጥብ የምድብ “ሀ” የበላይ ሆኖ ያጠናቀቀው ደደቢት በምድብ “ለ” በተመሳሳይ በ46 ነጥብ የበላይ ሆኖ ካጠናቀቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጋር የሚፋለም ይሆናል፡፡

ይህንን ጨዋታ በማስመልከት የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡትን አስተያየት በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡

ሎዛ አበራ – ደደቢት

ስለ ዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ

“የዘንድሮው የውድድር አመት እንደሌሎቹ አመታት ሁሉ በርካታ መሰናክሎችን አልፈን ከዚህ ወሳኝ ምእራፍ ላይ መድረስ ችለናል፡፡ ከሞላ ጎደል የዘንድሮው አመት እንቅስቃሴያችን ጥሩ የሚባል ነው፡፡”

ስለ ደደቢት ጉዞና በግሏ ስላሳለፈችው የውድድር ዘመን

“እንደ ቡድን ቡድናችን ዘንድሮ ጥሩ እንቅስቃሴን እያደረገ ይገኛል ፤ ለጥሩነታችንም አንደ ማሳያ የሚሆነው በምድባችን ካደረግናቸው 18 ጨዋታዎች 17ቱን አሸንፈን በአንዱ ብቻ ነው አቻ የተለያየነው፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም እንደነበሩት አመታት የቡድናችንን ጥንካሬ ያሳያል ብዬ አስባለሁ፡፡ በግሌ ጎሎችን እያስቆጠርኩ ነው የመጣሁት ፤  በእርግጥ ያመከንኳቸው በርካታ አጋጣሚዎች አንዳሉ ሆነው ማለት ነው፡፡ ይህም በእግርኳስ አለም ላይ የሚያጋጥም ሁኔታ ነው ፤ በግሌም ቢሆን ከሞላ ጎደል ጥሩ ጊዜን እያሳለፍኩ እገኛለሁ፡፡”

ቡድናቸው ውስጥ ስላለው ስሜት

“ቡድኑ ውስጥ አሁን ላይ ያለው ስሜት በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ሁላችንም አምሯችንን አዘጋጅተን በጥሩ የማሸነፍ ስሜት ላይ እንገኛለን፡፡ በእርግጠኝነት የእሁዱን ጨዋታ እናሸንፋለን ብዬ አስባለሁ፡፡ በእሁዱ ጨዋታ ላይ በግሌ ከፈጣሪ ጋር ሶስት ግቦችን አስቆጥራለው ብዬ አስባለሁ፡፡”

ስለተጋጣሚያቸው

“በዘንድሮው የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በተለያየ ምድብ በመደልደላችን የተነሳ  የመግጠም እድሉን አላገኘንም፡፡ ነገርግን ከዚህ ቀደም ለበርካታ ጊዜያት በመገናኘታችን በደንብ እንተዋወቃለን፡፡ የኛ ቡድን በጠንካራ ስሜትና አቋም ላይ እንደመገኘቱ የእሁዱን ጨዋታ ምንም እንኳን ሜዳ ላይ የሚደረገው እንቅስቃሴ የሚወስን ቢሆንም በእኛ በኩል ጨዋታውን አሸንፈን ዋንጫውን ለማንሳት ተዘጋጅተናል፡፡”

ህይወት ዳንጌሶ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስለዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ

“የዘንድሮው አመት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከዚህ ቀደም ከነበሩት ውድድሮች በጣም ጠንካራው ነው፡፡ በዘንድሮው ውድድር ከወትሮው በተለየ በርካታ ተፎካካሪ የሆኑ ቡድኖች በመኖራቸው የተነሳ ጠንካራ ፉክክርን ለማየት ችለናል ብዬ አስባለሁ፡፡”

ስለ ክለባቸው የውድድር ዘመኑ ጉዞ

“በውድድር ዘመኑ የቡድናችን ስብስብ በተጫዋቾች ጉዳት ከመሳሳቱ የተነሳ ወጣ ገባ የሚልን አቋም ልናሳይ ተገደናል፡፡ የቡድናችን ወሳኝ የሚባሉ ተጫዋቾች በመጎዳታቸው ትንሽ ተቸገርን እንጂ ቡድናችን እጅግ ጥሩ ነው፡፡ የምድቡ አሸናፊ እንደመሆናችን ለእሁዱ ጨዋታ በስነልቦናም ሆነ በጨዋታ ዝግጅት ረገድ ሁላችንም የቡድኑ አባላት በአንድነት እየተዘጋጀን እንገኛለን፡፡”

በግሏ በውድድር ዘመኑ ስላሳየችው ድንቅ ብቃት

“በግሌ በዘንድሮው አመት አቅሜ በፈቀደ መልኩ ጥሩ ነገርን ለክለቤ ማበርከትን ችያለሁ፡፡ በግሌ ለቡድኔ ከዚህም በተሻለ ጥሩ ነገር ለማድረግ ነው ፍላጎቴ፡፡ ምክንያቱም በእኔ ጥሩ መንቀሳቀስ ውስጥ ክለቤ ተጠቃሚ ስለሚሆን ነው፡፡ ይህንንም የማደርገው ብቻዬን አይደለም ፤  ከሌሎቹ የቡድን አጋሮቼ ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡ በእሁዱ ጨዋታ ከቡድን አጋሮቼ ጋር በጋራ በመሆን የተሻለ ነገርን ለመፍጠር እንጥራለን፡፡”

ስለ ተጋጣሚያቸው

“ደደቢት ጥሩ ቡድን ነው ፤ እኛ የምድባችን አሸናፊ እንደመሆናችን ሁሉ እነሱም የምድባቸው አሸናፊ ናቸው፡፡ ስለዚህ የእሁዱ ጨዋታ በሁለት ጠንካራ ቡድኖች መካከል የሚካሄድ ጠንካራ ጨዋታ ነው ፤ እኛም የአምናውን ሽንፈት ለመበቀል ተዘጋጅተናል፡፡”

ሰናይት ቦጋለ – ደደቢት

ስለዘንድሮው አመት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ

“የዘንድሮው አመት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከወትሮው በተለየ ሁሉም ቡድኖች ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው መቅረብ ችለዋል ፤ ከዚህም በተነሳ ጠንካራ ፉክክር የታየበት ጠንካራ የውድድር ዘመን ሆኖ አልፏል፡፡እኛም የመጨረሻ ምእራፍ ላይ እንደመገኘታችን የአምናውን ክብር ለመድገም ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን፡፡”

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በግሏ ስላሳለፈችው ድንቅ ጊዜ

“ከአምናው በጣም በብዙ ነገሮች ተሻሻያለሁ ብዬ አስባለሁ ፤ አምና በአመዛኙ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበሉ በኩል ጥሩ ነበርኩኝ፡፡ በዘንድሮው አመት ከዛ በተጨማሪ ግቦችን እያስቆጠርኩኝ እገኛለሁ ከዚህም የተነሳ የኮከብ ተጫዋቹነቱን ክብር ከፈጣሪ ጋር አገኛለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ረሂማ ዘርጋው – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስለዘንድሮ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ

“የዘንድሮው የውድድር ዘመን ለእኔ በጣም የተለየ ነበር ፤ እንደከዚህ ቀደሙ በቀላል የምታሸንፋቸው ቡድኖች የሉም፡፡ ሁሉም ቡድኖች ተፎካካሪ ሆነዋል ፤ በዚህም እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ ምከንያቱም ውድድሩ ከወትሮው በተሻለ ብቃትህን የምትለካበት በመሆኑ በጣም ደስተኛ ሆኜ እየተጫወትኩ እገኛለሁ፡፡”

ስለ ክለባቸው የውድድር ዘመኑ ጉዞ

“የቡድናችን ተጫዋቾች በእኔና ሽታዬ ሲሳይ ከቡድኑ ጋር በጉዳት አለመኖራችንን ተከትሎ በስነ ልቦናቸው ረገድ ጫና ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በኛ አለመኖር ቡድኑን አጉድሎት እንደነበር ይሰማኛል ፤ አሁን ላይ ሁሉም ነገሮች ተስተካክለዋል ከፈጣሪ ጋር የተሻለን ነገር እናሳከለን ብዬ አስባለሁ፡፡”

ስለ ደደቢት

“ደደቢቶች በጣም ጥሩ አቋም ላይ ነው የሚገኙት ፤ እኛም ከዚህ ቀደም ከነሱ ጋር ባደረግናቸው ጨዋታዎች ባገኘናቸው ልምዶች ላይ በመመርኮዝ የእነሱን ጠንካራና ደካማ ጎኖቻቸውን ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ በደካማ ጎናቸው በመጠቀም ጠንካራ ፉክክርን አሳይተን ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል፡፡”

በውድድር ዘመኑ ስላሳፈቻቸው አስቸጋሪ ጊዜያት

“በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ አጋማሽ ጉልበቴ ላይ ባጋጠመኝ ጉዳት የተነሳ ምንም አይነት ጨዋታዎችን ማድረግ አልቻልኩም፡፡ በሁለተኛው ዙር ከጉዳቴ አገግሜ ወደ አቋሜ ለመመለስ ባደረኩት ጥረት ላይ ሰውነቴ በመጨመሩ የተነሳ ወደ ጨዋታ ዝግጁነት ለመምጣት ትንሽ ተቸግሬ ነበር ፤ አሁን ፈጣሪ ይመስገን ጥሩ ጤንነት ላይ እገኛለሁ፡፡”

ስለ እሁዱ ጨዋታ

“እስከዛሬ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ብዙ ስኬቶችን ማጣጣም ችለናል፡፡ ነገርግን አሁን ላይ ሆኜ የሚሰማኝ ነገር ቢኖር እስካሁን ድረስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ምንም ዋንጫ እንዳላገኘሁ ነው፡፡ ይህንን ዋንጫ በግሌ በጣም እፈልገዋለሁ፡፡ ከፈጣሪ ጋር በጨዋታው የአቅሜን ሁሉ ጥረት በማድረግ ጓደኞቼን አስደስታቸዋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ወይንሸት ፀጋዬ – ደደቢት

ስለዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ

“በግሌ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከሌሎች የውድድር አመታት አንጻር የወረደ እንቅስቃሴ ነው የታየበት፡፡ አምና በጣም ጠንካራ ፉክክር ይታይበት ነበር ፤ የእኛም ቡድን ምንም እንኳን አምናም ጠንካራ የነበረ ቢሆንም በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ቡድኖችን ለማሸነፍ እንቸገር ነበር፡፡”

ስለ ቡድናቸው አቋም

“በዘንድሮው የውድድር ዘመን እስካሁን ምንም አይነት ሽንፈትን አላስተናገድንም ፤ ከአንድ አቻ በስተቀር፡፡ በዘንድሮው የውድድር ዘመን አምና የነበረን ጥንካሬ ላይ ዘንድሮ ቡድናችንን ከተረከበው ጠንካራው አሰልጣኛችን ጋር ጠንካራ ስራዎችን እየሰራ የነበረንን ጥንካሬ ማስቀጠል ችለናል፡፡”

ለረጅም አመታት ብቃቷን ጠብቃ ስለመጫወቷ ሚስጥር

“ጠንካራ ስራዬ አሁን ለምገኝበት ደረጃ አድርሶኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገርግን አሁንም ቢሆን ጠንክሬ በመስራት ይህንን ነገር ማስቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ እስከዛሬ ድረስ ያካበትኩትን ልምድ ለቡድን አጋሮቹ በማካፈል ከቡድኔ ጋር በቀጣይ ጠንካራ ስራዎችን ለመስራት እፈልጋለሁ፡፡”

ስለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

“እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከሚወዳደሩ ጠንካራ ክለቦች አንዱ ነው ፤ የሚናቅ ቡድን አይደለም ፡፡ ዘንድሮ እስካሁን እርስበእርስ አልተገናኘንም ፤ ነገርግን በውድድር ዘመኑ ያደረጓቸውን በርካታ ጨዋታዎች የመከታተል እድል ነበረኝ፡፡ በዚህም እንዳየሁት ከሆነ በጣም ጠንካራ ቡድን ናቸው ቢሆንም  ጨዋታውን ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል፡፡”

ፅዮን እስጢፋኖስ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስለዘንድሮው አመት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ

“የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከዚህ ቀደም ከነበሩት ብዙ የተለየ ነገር አለው ብዬ አላስብም፡፡ ነገርግን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቁልፍ የሆነ ተጫዋቾቹን በጉዳት በማጣቱ የተነሳ ወጣ ገባ በሚል አቋምን ከሌላው ጊዜ በተለየ ማሳየቱ ምናልባት የተለየ ሊያደርገው ይችላል፡፡”

ስለ እሁዱ ጨዋታ

“የእሁዱ የፍፃሜ ጨዋታ እንደከዚህ ቀደም ለሶስት ነጥብ ከሚደረገው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በተወሰኑ መልኩ ለየት ያለ ዝግጅትን አድርገናል፡፡ በግሌ በዚህ የዋንጫ ጨዋታ ላይ  ስጫወት ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ አምና ስላጣሁት ዘንድሮ በቁጭትና በሙሉ ዝግጅት ይህንን ጨዋታ እየጠበኩት እገኛለሁ፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *