ከተጀመረ ስድስተኛ አመቱን ያያዘው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በዘንድሮው የውድድር አመት የቅርፅ ለውጥ አድርጎ 20 ቡድኖች ለሁለት ተክፍለው ሲወዳደሩ ቆይተው ከምድብ ሀ ደደቢት ከምድብ ለ ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምድባቸው የበላይ ሆነው በማጠናቀቅ በነገው እለት በ10:00 በአዲስአበባ ስታዲየም የሊጉ አሸናፊ ለመሆን ይፋለማሉ፡፡
ይህንን ጨዋታ በማስመልከት የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሆኑት አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውና ጌቱ ተሾመ የነገውን ጨዋታ አስመልክተው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ እኛም የነበራቸውን ቆይታ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡
አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ስለ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ
“የዘንድሮው የውድድር ዘመን ያለምንም ጥያቄ ከሌሎቹ የውድድር ዘመናት እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ነው ፤ ምክንያቱም ሊጉ በተመሠረተ በስድስት አመት ውስጥ ምንያህል ክለቦች ከአመት አመት መሻሻልን እንዳሳዩ በግልጽ ያሳየ ፉክክር መመልከት ችለናል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩት አመታት ወደ ጨዋታ በምንገባበት ወቅት የማሸነፋችን ነገር እርግጥ ስለነበር ምንያህል ግብ ተጋጣሚያችን ላይ እናገባለን የሚለው ነገር ነበር የሚያሳስበን፡፡ ዘንድሮ ግን በየጨዋታው ሶስት ነጥብን ስለምናገኝበት መንገድ በብዙ መንገድ ማሰብና መወጠር ጀምረናል፡፡ እንደውም በድፍረት መናገር የሚቻለው እስከዛሬ ድረስ ስራ ላይ እንዳልነበርን መናገር ይቻላል ፤ ነገርግን አሁን ስራ ላይ ነን፡፡ እንደአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በ6 አመት ጉዞ ውስጥ በእጅጉ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡”
ስለ ቡድኑ የዘንድሮው አመት አቋም
“ከዚህ ቀደም ቡድናችን ይታወቅባቸው የነበሩ ጥንካሬዎች አሁን ላይ ከቡድኑ ጋር አሉ ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረን የቡድን ስብስብ በርካታ ተጫዋቾች በጉዳት ከሜዳ ርቀውብን ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለፉት አመታት የቡድናችን ቁልፍ ተጫዋቾች በአሁኑ ሰአት ከክለቡ ለቀዋል፡፡ ስለዚህም ይህንን ቡድን በነበረበት ደረጃ ዳግም ለማደራጀት ጊዜ ይወስዳል፡፡ በውድድር ዘመኑ ላይ ከፍተኛ ፈተና ሆኖብን የነበረው የተጫዋቾች ጉዳት ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ በጠባብ ውጤትም ቢሆን እያሸነፍን እዚህ ደርሰናል፡፡ ነገርግን በማሸነፍ ውስጥም ሆነን በርካታ ጉድለቶች እንደነበሩብን ግልጽ ነበር፡፡”
ስለ እሁዱ ጨዋታ
“የነገው ጨዋታ ለኛ ታሪካዊ ጨዋታ ነው፡፡ በስድስት አመት ቆይታችን ውስጥ ለስድስተኛ ጊዜ ነው ለዋንጫ የምንፋለመው፡፡ ይህ ለኛ ጥሩ ታሪክ ነው፡፡ ለሌሎች ጨዋታዎች ከምናደርገው ዝግጅት በተለየ ያደረግነው የተለየ ዝግጅት የለም፡፡ በዋንጫ ጨዋታ ላይ ከችሎታም በዘለለ አርበኝነት የግድ ይላል፡፡ እርግጥ ነው ደደቢት የወቅቱ ሻምፒዮን ነው ፤ ከዛም በተጨማሪ በቡድኑ ውስጥ በግላቸው ልዩነት መፍጠር የሚችሉ ጥሩ ጥሩ ልጆችን የያዘ ቡድን ነው፡፡ ነገርግን ዋንጫን ለማሸነፍ ከሚያበቁት ነገሮች አንዱ የሆነውን የአርበኝነት መንፈሰሸ ከተላበሱት ተጫዋቾቼ ጋር አብረን በመሆን ከነበሩብን ችግሮች ትምህረት በመውሰድ ለአራተኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት ዝግጅታችንን አጠናቀናል፡፡
ስለ አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ
“አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ ወደ ሴቶች እግርኳስ በመጣበት አመት ይህንን የመሰለ ጠንካራና ተፎካካሪ የሆነ ቡድን ገንብቷል፡፡ እንደእርሱ ያሉ ወጣት አሰልጣኞች በፊት በፊት ወደ ሴቶች እግርኳስ እንዲመጡ ጥሪ ስናደርግላቸው አይመጡም ነበር፡፡ አሁን ላይ ያለውን የሴቶች እግርኳስ ለውጥ ተከትሎ ወደዚህ በመምጣቱ ሊደነቅና ሊመሰገን ይገባዋል፡፡”
ስለ ተመልካች
“የስፖርት ቤተሰቡ እሁድ በሚደረገው ጨዋታ ላይ ወደ ስታድየም መጥቶ ቢመለከተን በወንዶች እግርኳስ የማይጠበቀውን ነገር በሴቶች እግርኳስ ሲደረግ ማየት ይችላል፡፡ ልዩ ተሰጥኦ እና ፈጠራን ለመመልከት ወደ ስታድየሙ እንዲመጡ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡ ወደ ስታድየም ሲመጡም ስርአት ባለው መልኩ ቢያበረታቱ እንዲሁም አላስፈላጊ ከሆኑና የሴቶቹን ሞራል ከሚነኩ ድርጊቶችና ንግግሮች ተቆጥበው ውድድሩን ቢከታተሉ የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡”
አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ – ደደቢት
በሴቶች እግርኳስ የመጀመሪያ አመት የአሰልጣኝነት ቆይታው ስላጋጠሙት ነገሮች
“በወንዶች እግርኳስ ውስጥ በተጫዋችነት በርካታ አመታትን እንደማሳለፌ በቅድሚያ ወደ ሴቶች እግርኳስ የመጣሁበት ሁኔታ ለብዙ ሰዎች ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ነገርግን ብዙ ጊዜ ፈተናዎች መጋፈጥ አለብህ እናም የኔም አመጣጤ ይህንን ፈተና ለመጋፈጥ ነበር፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ ቡድኑ የ2008 የሊጉ ቻምፒዮን በመሆኑ በርካታ ፈተናዎች ቀለው ነበር የጠበቁኝ፡፡ ፈተናዎቹን ሊቀሉልኝ የቻሉት አንደኛው እግርኳስን በግሌ ተጫውቼ በማሳለፌ ልጆቹን በብዙ ነገሮችን እረዳቸዋለሁ በዚህም ማድረግ የሚፈልጉትን እንዲያደርጉ ነፃነቱን እስጣቸዋለሁ፡፡ ሁለተኛው ሜዳ ላይ ልጆቹ ያላቸውን ነገር አውጥተው እንዲጠቀሙ ነፃነቱን አሰጣቸዋለሁ፡፡ በተጨማሪም ለሴቶች እግርኳስ አዲስ መሆኔ ስራውን ትንሽ ከባድ ቢያደርገውም አብዛኛውን ጊዜ የምሰጣቸውን ነገር ልጆቹ በአግባቡ በመቀበላቸው እንዲሁም በተጨማሪም ሴቶች በተፈጥሮ ለስራ ያላቸው ተነሳሽነት እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ስራዬን በስኬት እንዳከናውን ረድቶኛል፡፡”
ስለ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ
“የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን በሰፊ ጎል መርታታችን ከተመለከትኩ በኋላ ውድድሩ ቀላል መስሎኝ ነበር፡፡ ነገርግን ውድድሩ በጣም ከባድ ነው፡፡ እያንዳንዱ ቡድን ከባድ የሆነ እንቅስቃሴ ነበር የሚያደርጉት፡፡ በዚህም የተነሳ በጣም ብዙ ፈተናዎች ገጥመውናል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የኛ ቡድን በተከታታይ የነበሩትን ጨዋታዎችን ከአዳማው የአቻ ውጤት ውጪ ሁሉንም ማሸነፍ ችለናል፡፡ ያም ቢሆን ግን ሁሉንም ጨዋታዎች ስናሸንፍ በርካታ ፈተናዎች ገጥመውን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ ለውጥ አምጥቷል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡”
ስለ ውድድር ዘመኑ የቡድኑ እንቅስቃሴ
” ልጆቼ በውድድር ዘመኑ በአጠቃላይ በማይዋዥቅ መልኩ ተከታታይነት ያለው ወጥ አቋምን ማሳየት ችለዋል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ገና የውድድር ዘመኑን ስንጀምር አመቱን ሙሉ በጠንካራነታችን ዘልቀን ሻምፒዮን ሊያደርገን የሚችለውን ጠንካራ ስራ በመስራታችን ነው፡፡”
ስለተጋጣሚያቸው
“በኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ ሁለቱ ቡድኖች ጠንካራ ተቀናቃኝ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሁለት አመት በፊት የሊጉ ቻምፒዮን የነበረ ቡድን ነው፡፡ አሁን ላይ ግን በደደቢት ቡድን ውስጥ ወደ ጠንካራ ብቃታቸው ላይ እየደረሱ የሚገኙ ተጫዋቾች በመገኘታቸው የበላይነቱን መቀልበስ ችለዋል፡፡ ቢሆንም ግን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሻምፒዮን የነበረ ቡድን በመሆኑ የሚናቅ ቡድን አይደለም፡፡ እኛ እንደ ቡድን አመቱን ሙሉ ስንዘጋጅ የነበረው ለንግድ ባንክ ጨዋታ አይደለም፡፡ ገና አመቱን ስንጀምር ቻምፒየን እንሆናለን ብለን ነበር የጀመርነው፡፡ ስለዚህ ለንግድ ባንክ ብለን ያደረግነው የተለየ ዝግጅት ባይኖርም እንደሌላው ጨዋታ ትኩረት ሰጥተን ተዘጋጅተን ለማሸነፍ እንጫወታለን፡፡ በሊጉ ዘንድሮ ካደረጓቸው ጨዋታዎች የተወሰኑትን ጨዋታዎች ለመከታተል ችያለሁ፡፡ በቡድናቸው ውስጥ በርካታ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች አሉ ፤ ፊት ላይም ያገኟቸውን እድሎች በአግባቡ የሚጠቀሙ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን ነው፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ቡድን እንደመሆኑ ጥንቃቄ አድርገን በመጫወት ዋንጫውን ለማግኘት እንጥራለን፡፡”