ውድድር – የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ፍጻሜ
ቀን – እሁድ ግንቦት 6 ቀን 2009
ሰአት – 10:00
ቦታ – አዲስ አበባ ስታድየም
ዳኛ – ኢንተ. ዳኛ – ፅጌ ሲሳይ
በከፍተኛ ፋይናንስ ጠንካራ ቡድንን መገንባት የቻሉት ሁለቱ ቡድኖች የኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ልዕለ ኃያልነታቸው ዘንድሮም ቀጥሏል፡፡ የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በየምድባቸው የበላይ ሆነው ወደ ፍጻሜው በማለፍ ወደ ለነገው ፍጥጫ ቀርበዋል፡፡ በዚህ ዳሰሳ ከነገው ጨዋታ በፊት ስለ ሁለቱ ቡድኖች ሊያውቋቸው የሚገቡ ነገሮችን ሁሉ አሰናድተናል፡፡
የሁለቱ ክለቦች ኃያልነት
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር በሚል ስያሜ በ2004 ከዚህ ቀደም በነበረው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ ባወጣው አስገዳጅ ደንብ ምክንያት ሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የሴቶች ቡድን እንዲይዙ በተደነገገው መሠረት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀድሙት አመታት በአዲስአበባ ከፍተኛ ዲቪዝዬን ሲወዳደር የነበረውን ሴንትራል ዮኒቨርስቲ ኮሌጅ ቡድን ወደ ራሱ በመጠቅለል ቡድኑን ሲያዋቅር ፤ ደደቢት ደግሞ በአሰልጣኝ አስራት አባተ እየተመራ አዲስ ቡድን በማቋቋም በሊጉ መወዳደር ከጀመሩበት 2004 ጀምሮ ሁለቱ ቡድኖች እየተፈራረቁ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ችለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ2005-2007 በተከታታይ ባሳካቸው ክብሮች ታግዞ 3 ጊዜ በማንሳት ቀዳሚ ሲሆን ደደቢት የመጀመርያውን እና የመጨረሻውን አመት ዋነጫዎች በማንሳት ይከተላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሁለቱን ቡድኖች ጥንካሬ በሚያሳይ መልኩ በ2004 ወንጂ ላይ ከተደረገውና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ዳሽን ቢራ ከተገናኙበት የማጠቃለያ ውድድር ፍጻሜ በስተቀር በቀሩት አራቱ የማጠቃለያ ውድድሮች ላይ ለፍፃሜ መገናኘት የቻሉት እነዚሁ ሁለቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሀያላን ክለቦች ናቸው፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከዚህ ቀደም ማእከላዊ ሰሜን ዞን እንዲሁም ደቡብ ምስራቅ ዞን እየተባለ በሁለት ዞኖች ተከፍሎ ሲካሄድ የነበረውን የውድድር ቅርፅ ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ዘንድሮ ለውጥ በማድረግ ምድብ “ሀ” እና ምድብ “ለ” በሚል ውድድሩ በሁለት ምድቦች ተከፍሎ መካሄድ ችሏል፡፡ በዚህም ሁለቱ ቡድኖች የሁለቱ ምድቦች አባት ቡድን በመሆን በተለያዩ ምድቦች ከሌሎች 9 የፕሪሚየር ሊጉ ቡድኖች ጋር ውድድራቸውን ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡
በምድብ “ሀ” የተደለደለው የአምናው ባለ ድል ደደቢት የምድቡ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው 3 ሳምንታት ሲቀሩት ነበር፡፡ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች 17 አሸንፎ በአንዱ ብቻ አቻ በመለያየት በ52 ነጥብ ከተከታዩ አዳማ ከተማ በ13 ነጥብ ርቆ ምድቡን በበላይነት ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በምድብ ለ የለደለደለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም አንድ ጨዋታ እየቀረው ነበር የምድቡ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው፡፡ ሀምራዊ ለባሾቹ ካደረጓቸው 18 ጨዋታዎች በ14ቱ ሲያሸንፉ በሁለቱ ተሸንፈው በቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው በ46 ነጥብ ከተከታያቸው ሀዋሳ ከተማ በ4 ነጥብ ከፍ ብለው የምድብ “ለ” አሸናፊ በመሆን ለነገ 10:00 የአዲስ አበባ ስታድየም የፍፃሜ ጨዋታ መድረስ ችለዋል፡፡
የውድድር ዘመን ጉዞ
ደደቢት
የአምናው ቻምፒዮን ደደቢት አመቱን የጀመረው ቡድኑን ከ3 አመታት በኋላ ወደ ሊግ ክብር ከመለሰው አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ጋር ተለያይቶ በአሰልጣኝነት ሙያ ልመምድ የሌለው የቀድሞ የንግድ ባንክ ድንቅ አማካይ ጌቱ ተሾመን ወደ አሰልጣኝነት መንበሩ በማምጣት ነበር፡፡
ቡድኑ አምና ከነበረው የቡድን ስብስብ ውስጥ ከግብ ጠባቂዋ ሊያ ሽብሩ ጋር ከመለያየታቸው በስተቀር ተጠቃሽ የሆነ የተጫዋች ለውጥ አላደርጉም፡፡ በሌላ በኩል የቀድሞ ተጫዋች የሆነችው ብሩክታዊት ግርማ እና አምና በቅዱስ ጊዮርጊስ ልዩ ብቃቷን ማሳየት የቻለችው ትእግስት ዘውዴን ወደ ቡድናቸው የቀላቀሉበት ዝውውር ቡድኑን ይበልጥ ያጠናከረ ነበር፡፡
በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሀ ግብር ኢትዮጵያ ቡናን 7-0 በመርታት የውድድር ዘመኑን ሀ ብለው የጀመሩት ሰማያዊዎቹ አመቱን ሙሉ ወጥ አቋምን ማሳየት ችለዋል፡፡ ለዚህም ተወዳዳሪ የሌለው የተጫዋቾች ስብስብ ጥራት በሁሉም የሜዳ ክፍል መያዙ እንደምክንያት ይጠቀሳል፡፡
አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ አመዛኙን የውድድር ዘመን በ3-5-2 ሙሉ ለሙሉ ማጥቃት ላይ መሠረት ያደረገ እግርኳስን መጫወት ችሏል፡፡ በወይንሸት ፀጋዬ ፣ ዘቢብ ሀ/ስላሴ እና መሠረት ካንኮ የሚመራው ጠንካራው የመከላከል ክፍልም የሊጉ እጅግ አነስተኛ ግቦች ያስተናገደው የመከላከል ጥምረት ነው፡፡
በ5 ተጫዋቾች የተዋቀረው የመሀል ክፍላቸው ተጠጋግቶ በመጫወት ፣ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተጠጋ አቋቋም ፣ ለቡድን አጋሮቻቸው ክፍተትን በመፍጠር ፣ መሀል ለመሀል እንዲሁም በመስመሮች በኩል በሚደረግ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴን እንደ አስፈላጊነቱ በተለዋዋጭነት በመጠቀም ለተጋጣሚዎቹ ፈተና መሆን ችሏል፡፡ በደደቢት የመሀል ሜዳ ላይ ከሚገኙት 5 ተጫዋቾች መካከል ኤደን ሽፈራው በተከላካይ አማካይነት ስፍራ ላይ ከተጋጣሚዎች ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት ከማቋረጥ በዘለለ ቡድኑ ኳስን ከራሱ የሜዳ ክልል መስርቶ ለመውጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ በጉልህ የሚታይ ሚና ነበራት፡፡ ከእሱዋ አጠገብ በግራና ቀኝ የሚጫወቱት በሊጉ በፈጠራ ብቃታቸው በላቀ ደረጃ ከሚገኙት ጥቂት ምርጥ አማካዮች ውስጥ የሚመደቡት ብርክታዊት ግርማና ሰናይት ቦጋለ ቡድኑ ላስቆጠራቸው በርካታ ግቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ ሰናይት ቦጋለም በግሏ በዘንድሮው የውድድር አመት አምና ትታወቅበት ከነበረው ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ከማቀበል በዘለለ መልኩ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በርከት ያሉ ግቦችን ማስቆጠር ችላለች፡፡ ብርቱካን ገብረክርስቶስም እጅግ ከፍተኛ የሆነ የአካል ብቃትንና ብርታትን የሚጠይቀውን የመስመር ተመላላሽነት (wing-back) ሚና በቶሎ በመላመድ ድንቅ የውድድር ጊዜን አሳልፋለች፡፡
አጥቂ ስፍራ ላይ አምና በዞኑ ውድድር 47 ፣ በማጠቃለያው ውድድር ላይ ተጨማሪ 10 ግቦችን አክላ በአጠቃላይ 57 ግቦችን ማስቆጠር የቻለችው የአምናው የውድድር ዘመን ኮከብ አግቢዋ ሎዛ አበራ ዘንድሮም በ32 ግቦች የምድቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ ከሷ በተጨማሪ ታታሪዋ ሰናይት ባሩዳ በሚዋልል እንቅስቃሴ ወደ መሀል እና ወደ መስመሮች እየወጣች በመጫወት የማጥቃት እና የመቀባበል አማራጮችን በመፍጠር እዲሁም የተጋጣሚን ትኩረት በመበታተን ጥሩ የሚባል የውድድር ዘመን ማሳለፍ ችላለች፡፡
እንደ አጠቃላይ ቡድኑ በውድድር ዘመኑ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ መልካም ጊዜ ማሳለፍ ችሏል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ ወሳኝ አጥቂ የሆነችው ሎዛ አበራ በባህሪዋ የምትፈልገውን ከተከላካዮች ጀርባ የሚኖረውን ክፍተቶችን አፈግፍገው በሚጫወቱ ቡድኖች ስተትፈተን ተስተውላለች፡፡ በተጨማሪም በ3-5-2 ቅርፅ እንደመጫወታቸው ቡድኑ በሜዳው ስፋት ከሶስቱ የመሀል ተከላካዮች ጎን የሚኖረውን ክፍተት የመስመር ተመላላሾቹ በፍጥነት መሸፈን ባለመቻላቸው ቡድኑ በመስመር አጨዋወት በሚጫወቱ ቡድኖች በተደጋጋሚ ሊፈተን ችሏል፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሳለፍነው ክረምቱ የዝውውር መስኮት የክለቡ ቁልፍ ተጫዋቾች የነበሩት ብሩክታዊት ግርማን ወደ ተቀናቃኛቸው ደደቢት እንዲሁም ቅድስት ቦጋለን ወደ አዲስአበባ ከተማ ሲሸኝ በምትካቸውም ወደ ቡድኑ አምና በሀዋሳ ከተማ አስደናቂ ጊዜያትን ያሳለፈችው አዲስ ንጉሴ እና በሲዳማ ቡና ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለችው የካቲት መንግስቱን የመሳሰሉ ተስፈኛ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው ማካተት ችለዋል፡፡
ቡድኑ ገና ከውድድር ዘመኑ ጅማሮ አንስቶ እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ በተጫዋቾች ጉዳት ሲታመስ ቆይቷል፡፡ ለማሳያነትም የቡድኑ ዋነኛ ፊትአውራሪ የሆኑት አጥቂዎች ሽታዬ ሲሳይ እና ረሂማ ዘርጋው ባጋጠማቸው የጉልበት ጉዳት ከቡድኑ ሲርቁ በተመሳሳይ ግብ ጠባቂዋ ዳግማዊት መኮንንና አዲስ ፈራሚዋ አዲስ ንጉሴም ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ምክንያት ቡድኑን ማገልገል አልቻሉም፡፡ በተለይም የአምናዋ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች የነበረችው ሽታዬ ሲሳይ ጉዳት ቡድኑን በእጅጉ እንደጎዳው ተስተውሏል፡፡
ቡድኑ በዘንድሮው የውድድር አመት ካሳየው ነገር በመነሳት እንደ ጠንካራ ጎኑ ከሚነገሩለት ነገሮች አንዱ የሆነው በአትበገሬዋ የመሀል ተከላካይ ጥሩ አንቺ መንገሻ የሚመራው የተከላካይ ስፍራ ጥንካሬ ነው፡፡ ከተከላካይ ስፍራቸው ጥንካሬ በተጨማሪም ግብጠባቂያቸው ንግስቲ መአዛም በግሏ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ልዩነት ፈጣሪ ነበረች፡፡ ሌላኛው የቡድኑ ጥንካሬ ሁለቱ የመስመር ተከላካይ የሆኑት እፀገነት ብዙነህና ሀብታምነሽ ሲሳይ ከመከላከሉ በዘለለ በማጥቃቱ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸው ንቁ ተሳትፎ እንደ ጠንካራ ጎን የሚጠቀስ ነው፡፡
አማካይ ስፍራ ላይ ሉሲዎቹን ለረጅም አመታት በአምበልነት የመራችው ብዙሃን እንዳለ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ ዳግም ወደ ቡድኑ ተመልሳ ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት ችላለች፡፡ ከጎኗ የምትሰለፈውና የቡድኑ የውድድር ዘመኑ ኮከቧ ህይወት ዳንጌሶ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ቡድኑ በሚቸገርበት ወቅት የቡድኗ የቁርጥ ቀን ልጅ በመሆን ወሳኝ ግቦችን በማስቆጠር ለቡድኑ እዚህ ደረጃ መድረስ ከፍተኛ ሚናን ተጫውታለች፡፡ በብሩክታዊት እና ቅድስት መልቀቅ ምክንያት የፈጠራ እጥረት የሚስተዋለበት የንግድ ባንክ የአማካይ ክፍል ላይ ከፍ ያለ የቴክኒክ ብቋት ያላት ዙለይካ ጁሀድ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ስትመራ ብተትስተዋልም አመርቂ የሚባል አልነበረም ፡፡
በአጥቂ ስፍራ ላይ የመጀመሪያው የውድድር ዘመን አጋማሽ በጉዳት ያመለጣት ረሂማ ዘርጋው በሁለተኛው ዙር ወደ የጨዋታ ዝግጁነቷን እስክታገኝ ብትቸገርም በሂደት ወደ ጥሩ አቋሟ መመለስ ችላለች፡፡
በ4-4-2 ቅርፅ ከተከላካዮችና ከህይወት ዳንጌሶ በረጃጅሙ በሚላኩ ተሻጋሪ ኳሶች የብዙነሽ ሲሳይንና ረሂማ ዘርጋውን ፍጥነት መጠቀም ላይ የተንጠለጠለ የሚመስለው የንግድ ባንኮች አጨዋወት በአብዛኛው የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ብልጫ መውሰድ ሳይችሉ በጠባብ ውጤት እያሸነፉ ተጉዘዋል፡፡ ይህም አጨዋወት በነገው እለት ጠንካራ የቡድን ውህደት በሚታይበት ደደቢት ከፍተኛ ፈተና እንደሚገጥመው ይጠበቃል፡፡
ንግድ ባንኮች በዘንድሮው የውድድር ዘመን ፍጥነትንና ጉልበትን መሠረት አድርገው በወጣቶች ከተገነቡት ሲዳማ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ቡድኖች ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች ላይ ጨዋታዎች ላይ ቡድኑ ይህንን አጨዋወት ለመቋቋም ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ ይህም በነገው እለት ፈጣን እና ጉልበተኛ የሆኑት ሎዛ አበራና ሰናይት ባሩዳ የሚመራውን የደደቢትን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመመከት ሊቸገሩ እንደሚችል ማሳያ ይሆናል፡፡
ግምታዊ አሰላለፍ
ደደቢት (3-5-2)
ፍሬወይኒ ገብሩ
መስከረም ካንኮ – ወይንሸት ፀጋዬ – ዘቢብ ሀይለስላሴ
ትእግስት ዘውዴ – ብሩክታዊት ግርማ – ኤደን ሽፈራው – ሰናይት ቦጋለ – ብርቱካን ገብረክርስቶስ
ሰናይት ባሩዳ – ሎዛ አበራ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (4-3-3)
ዳግማዊት መኮንን
ሀብታምነሽ ሲሳይ – ጥሩአንቺ መንገሻ – ፅዮን እስጢፋኖስ – እፀገነት ብዙነህ
ህይወት ዳንጌሶ – ብዙሀን እንዳለ – አዲስ ንጉሴ
ዙለይካ ጁሃድ – ረሂማ ዘርጋው – ብዙነሽ ሲሳይ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድሩን ዋንጫ ለአራተኛ ጊዜ በማሸነፍ አምና የተነጠቀውን ክብር ያስመልስ ይሆን? ደደቢት በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የሊጉን ዋንጫ ብዛታቸውን ወደ 3 በማድረስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር መስተካከል ይችሉ ይሆን?
ለነዚህ ጥያቄዎች የነገው የ10:00 ጨዋታ ምላሽ ይኖረዋል፡፡