በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ እጅግ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሁለቱ ሀያላን ፍልሚያ በደደቢት የበላይነት ተጠናቆ ለተከታታይ አመታት የሊጉ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ሰማያዊዎቹ 3ኛ ዋንጫቸውን በማንሳትም የዋንጫ ብዛታቸውን ከንግድ ባንክ ጋር አስተካከለዋል፡፡
ሁለቱም አሰልጣኞች ባልተጠበቀ መልኩ ለወትሮው ይጠቀሙባቸው ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል መጠነኛ ለውጦችን አድርገው ነበር ጨዋታቸውን የጀመሩት፡፡ ደደቢቶች ታታሪዋን አጥቂ ሰናይት ባሩዳን ወደ ተቀያሪ ወንበር አውርደው በምትኳ ነህሚያ አበራ በመተካት ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙበት በነበረው ተመሳሳይ የ3-5-2 ቅርፅ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው በደደቢቶች በመሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድባቸው በማሰብ አጥቂዋ ብዙነሽ ሲሳይ ምትክ ተከላካይ በማስገባት ለወትሮው በቀኝ መስመር ተከላይነት የምትጫወተውን ሀብታምነሽ ሲሳይን ወደ አማካይነት በማምጣት በ4-5-1 ቅርጽ መጫወት ሲችሉ ከጉዳት የተመለሰችው ግብ ጠባቂዋ ዳግማዊት መኮንን ወደ ቡድን ስብስባቸው መመለስ ችለዋል፡፡
ጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ እንደተጠበቀው ሳቢ የሆነ እንቅስቃሴ አልታየበትም፡፡ ንግድ ባንኮች ፊት ላይ ረሂማ ዘርጋው ብቻ ተነጥላ ቀርታ ሌሎቹ የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በማፈግፈግ በጥልቀት ሲከላከሉ ተስተውሏል፡፡ ኳስ በቁጥጥራቸው በምትውልበት ጊዜም በተናጥል የመስመር ተከላካይዋ እፀገነት ብዙነህ በግሏ የማጥቃት እንቅስቃሴን ለማስጀመርና ረሂማን ለማገዝ ከምታሳየው ተነሳሽነት በስተቀር አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከመከላከሉ በዘለለ በማጥቃቱ ላይ የመሳተፍ ተነሳሽነት አይታይባቸውም ነበር፡፡ በደደቢቶች በኩል ብሩክታዊትና ሰናይት ቦጋለ በባህሪያቸው የሚፈልጉትን በተከላካይ እና አማካይ ተጫዋቾች መካከል ያለውን ስፍራ በንግድ ባንኮች ጥልቅ የመከላከል የተነሳ ማግኘት ባለመቻላቸው ተቸግረው ተስተውሏል፡፡
በ24ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ያሻማችውን የማዕዘን ምት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክዋ ግብ ጠባቂ ዳግማዊት መኮንን በቀላሉ መያዝ ስትችል የተፋችውን ኳስ በቅርብ ርቀት የነበረችው ነሀሚያ አበራ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይራ ደደቢትን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች፡፡
ከግቧ መቆጠር በኃላ ደደቢቶች ይበልጥ ተሽለው በመንቀሳቀስ ቢችሉም የጠሩ የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ንግድ ባንኮችም ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር እጅግ የዘገየ በመሆኑ የተነሳ በተቃራኒ የሜዳ ክፍል የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ውጤታማ አልነበሩም፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ንግድ ባንኮች በመጀመሪያው አጋማሽ ለረሂማ ዘርጋው ቀርባ ስትጫወት የነበረችውና እጅግ ደካማ እንቅስቃሴን ያሳየችው ብዙሃን እንዳለን በብዙነሽ ሲሳይ በመተካት ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡ ከቅያሬው በኃላ ንግድ ባንኮች ከተከላካዮች እንዲሁም ከህይወት ዳንጌሶ እግር በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች ወደ ግብ በፍጥነት ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡
ደደቢቶች ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ የመሀል ሜዳውን ብልጫ ቢወስደም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ተዳክመው ታይተዋል፡፡ በተደጋጋሚ ኳስ ወደ እሷ በአግባቡ መድረስ ባለመቻሉ ከወትሮው በተለየ መልኩ ሎዛ አበራ በጥልቀት ወደ ኃላ እየተመለሰች ኳሶችን ይዛ ለመግባት ጥረት አድርጋለች፡፡
በ77ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ በግሩም ሁኔታ የተላከላትን ኳስ ሎዛ አበራ አስደናቂ ፍጥነቷን በመጠቀም የውድድር ዘመኑን 33ኛ እንዲሁም የደደቢትን አሸናፊነት ያረጋገጠችውን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡ ጨዋታውም ተጨማሪ የግብ ሙከራዎች ሳይስተናገድበት በደደቢት 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
5፡00 ላይ ከሁለቱም ምድብ ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት አዳማ ከተማንና ሀዋሳ ከተማን ባገናኘው የደረጃ ጨዋታ በአዳማ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
የአዳማ ከተማ ፍፁም የበላይነት በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነችው 16 ቁጥሯ ከሳጥን ውጭ እጅግ ማራኪ ግብ አክርራ በመምታት አስቆጥራ ቡድኗን ቀዳሚ ማረግ ቻለች፡፡
ከወትሮው በተለየ በመጀመሪያው አጋማሽ ተዳክመው የተስተዋሉት ሀዋሳ ከተማዎች በደቂቃዎች ልዮነት ወደ ጨዋታው መመለስ የሚችሉበትን አጋጣሚ በፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም የምድብ “ለ” ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዋ አይናለም አሳምነው ሳትጠቀምበት ቀርታለች፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው የተሻለ የመሸናነፍ ፉክክር ቢያሳዩም እደገና አለምዋሶን ተክታ ወደ ሜዳ የገባችው አይዳ ኡስማን ሁለተኛ ግብ አክላ አዳማ ከተማ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሆነው ማጠናቀቅ እንዲችሉ አድርጋለች፡፡
በመዝጊያ ስነስርአቱ ውድድሩን ከአንድ እስከ ሶስት ያጠናቀቁት ቡድኖች የሜዳሊያ ሽልማት ሲበረከትላቸው የየምድባቸው አሸናፊ የሆኑት ደደቢት እና ንግድ ባንክ እንዲሁም የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ የሆኑት ቦሌ ክ/ከተማዎች የተዘጋጀላቸውን ሽለልማት ተቀብለዋል፡፡ በመጨረሻም ደደቢት የ2009 የውድድር ዘመን አሸናፊ መሆኑን የሚያበስረውን ዋንጫ አምበሏ ኤደን ሽፈራው ከፍ አድርጋ አንስታለች፡፡