የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊጠናቀቅ 3 ሳምንታተት ብቻ ቀርተውታል፡፡ ከቡድኖቹ ፉክክር በተጨማሪም በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ለማጠናቀቅ የተቃረበው ጌታነህ ከበደ ለ16 አመታት የቆየውን በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል የማስቆጠር ሪኮርድን ይሰብራል/አይሰብርም የሚለው ጉዳይ መነጋገርያ ሆኗል፡፡ አጥቂው በዚህ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ስለ ውድድር ዘመኑ
የሊጉ ፉክክር ጥሩ ሆኗል፡፡ ላለመውረድም ሆነ ለቻምፒየንነት ያለው ፉክክር የስፖርት ቤተሰቡ እስከ መጨረሻው እንዲከታተለው አድርጎታል። የዘንድሮ ሊግ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጓጊ ሆኖ እየተካሄደ ይገኛል።
በአንድ የውድድር አመት በርካታ ግብ የማስቆጠር ሪኮርድ ስለመስበር
ቅድሚያ የምሰጠው ክለቤ ውጤታማ እንዲሆን ነው ። እስካሁንም ያስቆጠርኳቸው ጎሎች ለክለቤ ወሳኝ ጎሎች ነበሩ። በመቀጠል በግሌ ታሪክ ለመስራት እፈልጋለው፡፡ በቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ላይ ከፈጣሪ ጋር በእርግጠኝነት ጎል በማስቆጠር ሪከርዱን እሰብረዋለው ብዬ አስባለው
አብረውት ቢጫወቱ የጎል ማስቀጠር ሪከርዱን ሊያሻሽሉለት ይችላሉ የሚላቸው አማካዮች
ሁለት ተጨዋቾች አሉ ፤ የሀዋሳዎቹ ጋዲሳ መብራቴ እና ፍሬው ሰለሞን ናቸው። ከእነሱ ጋር ተጣምሬ አብሬ ብጫወት ብዙ ጎል አስቆጥራለው፡፡ ምክንያቱም በጣም አቅም ያላቸው አማካይ ስፍራ ጨዋቾች ናቸው ።
ስለ ብሔራዊ ቡድን
ያለፉት አመታት ለብሔራዊ ቡድን በመጫወት እና ጎሎች በማስቆጠር በምችለው መጠን ሁሉ ሀገሬን አገልግያለው። ወደ ፊትም ቢሆን በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እና በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ላይ በሚኖሩት ጨዋታዎች ከዚህ ቀደም የሰጠሁትን አገልግሎት ለሀገሬ ለመስጠት ተዘጋጅቻለው።
ማልያውን ቀዶ በመውጣቱ የተፈጠረበት ተፅዕኖ
የፈጠረብኝ ተፅእኖ አለ፡፡ እንደሚታወቀው በተለያዩ ሚዲያዎች ቀርቤ የስፖርት ቤተሰቡን ይቅርታ ጠይቄያለው። ነገር ግን ሁሌም ሳስበው ወቅቱ ባደረኩት ድርጊት አፍራለው። በድርጊቱ ማንንም አልጎዳሁም የጎዳሁት ራሴን ብቻ ነው፡፡ ወደ ሜዳ ስመጣ እፍረት ይሰማኛል። አንዴ ሆኖ አልፏል ትምህርትም ሰጥቶኝ አልፏል። ሌሎች እንዲህ ያለ ነገር እንዳያደርጉም መልክቴን አስተላልፋለው።