ደደቢት ስፖርት ክለብ በዘንድሮው የውድድር አመት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ለሆኑት የክለቡ ተጫዋቾች እና የቡድን አባላት በትላንትናው እለት ምሽት በጎልፍ ክለብ በተካሄደ የሽልማት ስነስርዓት ከ5ሺህ-50ሺህ ብር የሚደርስ የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡
ክቡር አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የቀድሞው የክለቡ አመራሮችን እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የትላንት ምሽቱ ፕሮግራም የደደቢት ስፖርት ክለብ በ2009 ምንም ጨዋታ ሳይሸነፍ 18 ጨዋታዎችን አሸንፎ በአንዱ ብቻ አቻ በመለያየት የሊጉን ዋንጫ ለተከታታይ ሁለተኛ አመት ላነሱት ተጫዋቾች የማበረታቻ ሽልማት አበርክተዋል፡፡
በደደቢት የስፖርት ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ በሆኑት ኮሎኔል ዳንኤል ቡሳ የመክፈቻ እና የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ጅማሮውን ባደረገው በዚሁ ፕሮግራም በመቀጠልም ከክለቡ ስኬታማ የዘንድሮው አመት ጉዞ ጀርባ ዋንኛ ተዋንያን የነበሩት ተጫዋቾችና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት እንደየደረጃቸው ከ5ሺህ ብር እስከ 50ሺህ ብር ሽልማት ከእለቱ የክብር እንግዶች እጅ ተቀብለዋል፡፡
በማስከተልም የእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ባደረጉት ንግግር በአሸናፊ ሴቶች መሀል መገኘታቸው የፈጠረባቸውን ደስታ ገልፀው ይህም ድላቸው በሌሎች መስኮች ሁሉ ለተሰማሩ ታታሪ ሴቶች አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
በመቀጠል ንግግራቸውን ያደረጉት የክለቡ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ወልዳይ በርሄ እንደተናገሩት አምና በተመሳሳይ ወቅት የ2008 የሊጉን ዋንጫ ካነሱ በኃላ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ተጫዋቾቹ የገቡትን ቃል ጠብቀው ዳግም ለዚህ ድል በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልፀው በቀጣይ ደግሞ የቀረውን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ እንደሚያነሱ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
በፕሮግራሙ መገባደጃ ላይ የክለቡ አሰልጣኝ የሆነው ጌቱ ተሾመና አምበሏ ኤደን ሽፈራው በጋራ በመሆን ቡድኑ በምድብ “ሀ” የምድቡ አሸናፊ በመሆኑና በፍጻሜ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በመርታት ሻምፒዮን የሆኑበትን ሁለት ዋንጫ ለክለቡ ስራስኪያጅ ለሆኑት አቶ ወልዳይ በርሄ አስረክበዋል፡፡
ከርክክቡ በኃላ አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ እንደተናገረው ክለቡ ስላደረገላቸው ነገር በቅድሚያ ምስጋናውን አቅርቦ በመጀመሪያው አመት የአሰልጣኝነት ቆይታው ይህንን ድል እንዲያሳካ ለረዱት የክለቡ ተጫዋቾች ምስጋናውን በተመሳሳይ አቅርቧል፡፡ በመጨረሻም በቀጣይ በሚኖሩ ውድድሮች ላይ በተመሳሳይ ዋንጫ እንደሚያነሱ ቃል ገብቷል፡፡ የቡድኑ አምበል ኤደን ሽፈራው በበኩሏ አምና ገብተውት የነበውን ቃል ጠብቀው እዚህ በመድረሳቸው እንደተደሰተችና በቀጣይም አመትም በእርግጠኝነት ዋንጫውን እንደሚያነሱ በሙሉ ልብ ተናግራለች፡፡
በመጨረሻም በፕሮግራሙ ላይ እንደተገለፀው ከሆነ በቀጣይ ቡድኑ የጥሎ ማለፉን ዋንጫ የሚያነሳ ከሆነ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ለተጫዋቾቹ ለየት ያለ ሽልማት ለመስጠት እንዳሰበም ተሰምቷል፡፡