ኢትዮጵያ ቡና ለ2010 የውድድር አመት ክለቡን የሚመሩትን አሰልጣኝ በትላንትናው እለት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ክለቡ የአሰልጣኙን ድራጋን ፖፓዲችን ሹመት ዝርዝር ጉዳዮች አስመልክቶ በነገው እለት 10:00 ላይ በኢትዮጵያ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡
በክለቡ የ41 ዓመት ታሪክ የመጀመሪያው የውጪ ሃገር አሰልጣኝ ሆነው በ2008 ክለቡን የተቀላቀሉት ሰርቢያዊው ድራጋን ፖፓዲች ከአንድ አመት በኋላ በድጋሚ ወደ ክለቡ እንደተመለሱ ኢትዮጵያ ቡና በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ አሳውቋል፡፡ ትላንት ለሊት አዲስ አበባ መግባታቸውም ታውቋል፡፡
በ2008 የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ ቡናን በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ ያስቻሉት ፖፓዲች ውላቸው ባለመታደሱ ከክለቡ ተለያይተው የታንዛኒያው ክለብ የሆነው አፍሪካን ሊዮንስን ለአጭር ግዜ ካሰለጠኑ በኃላ ከስራ ርቀው ቆይተዋል፡፡ የ71 ዓመቱ አሰልጣኝ ከታንዚኒያ በሚወጡ መረጃዎች ከሆነ ዳግም ወደ ዳሬሰላሙ ክለብ ይመለሳሉ ቢባል አፍሪካን ሊዮን ዛሬ ከታንዛኒያ አዛም ፕሪምየር ሊግ መውረዱ እንዲሁም ኢትዮጵያ የእሳቸው ፈላጊ ሆኖ መቅረቡ ሃሳባቸውን ሳያስቀይራቸው አይቀርም ተብሏል፡፡
የቀድሞ ቡና አማካይ እና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከክለቡ ጋር ስሙ በስፋት ባሳለፍነው ሳምንታት ሲነሳ ነበር፡፡ በ28ኛው ሳምንት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታም የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ካሳዬ ወደ ቡድኑ እንዲመለስ መፈለጋቸው አሳይተዋል፡፡ አመቱን በሌላኛው ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ኒቦሳ ቩሴቪች የጀመረው ቡና ሁለት ጊዜ የአሰልጣኝ ለውጥ በውድድር ዓመቱ አድርጓል፡፡
በዩጋንዳው ኤክስፕረስ፣ በጋናው ሃርትስ ኦፍ ኦክ እና በታንዛኒያው ሲምባ ከዚህ ቀደም የሰሩት ፖፓዲች በምስራቅ አፍሪካ እግርኳስ የገነነ ስም የገነባው ሰርዮቪች ሚሉቲን ‘ሚቾ’ን ወደ አፍሪካ እንዲመጣ በር እደከፈቱለት ይነገራል፡፡