ሀዋሳ ከተማ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን አረጋገጠ

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ 7-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ የ2009 የውድድር ዘመን አሸናፊ መሆኑን አንድ ጨዋታ እየቀረው አረጋግጧል፡፡

በጨዋታው ሀዋሳ ከተማዎች በተጋጣሚያቸው ላይ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ የወሰዱ ሲሆን ጎል ለማስቆጠርም 2 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ በጨዋታው ድንቅ የነበረው ቸርነት አውሽ ከገብረመስቀል ዱባለ የተሻገረለትን ኳስ አስቆጥሮ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ከ6 ደቂቃዎች በኋላም በድጋሚ ቸርነት አውሽ ወደ ሳጥን እየገፋ በመግባት በግሩም ሁኔታ ለራሱ እና ለክለቡ 2ኛ ግብ አሰቆጥሯል፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 4 ደቂቃዎች ሲቀሩ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች በገብረመስቀል ዱባለ ላይ በሰሩት ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ፀጋአብ ዮሀንስ አስቆጥሮ በሀዋሳ ከተማ 3-0 መሪነት ለእረፍት ወጥተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽም ሀዋሳ ከተማ የበላይ የነበረ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ አብዱልጀባል ሀጂ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጪ አንድም ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ወጥተዋል፡፡

በ52ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ታደሰ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲተፋው ፀጋአብ ዮሀንስ አራተኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡

በጨዋታው ከተከሰቱ ክስተቶች መካከል በ61ኛው ደቂቃ በእለቱ ረዳት ዳኛ የነበረው መሳይ ካኤ ተጎድቶ 4ኛ ዳኛዋ ምስጋና ጥላሁን ተክታ የገባችበት ክስተት ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ሶስቱም ተጫዋቾች ጎል ማስቆጠራቸው አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡ ቴዎድሮስ መሀመድ 5ኛውን ሲያስቆጥር ሳሙኤል ቦጋለ 6ኛውን እንዲሁም ናትናኤል ሞላልኝ በግምት ከ35 ሜትር ርቀት አክርር በመምታት አስደናቂ ጎል አስቆጥረዋል፡፡

ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 7-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ 44 ነጥቦች የሰበሰበው ሀዋሳ ከተማ በኢትዮጵያ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ ከ20 አመት ፕሪምየር ሊግ አንድ ጨዋታ እየቀረው ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ሀዋሳ ከተማ የመጨረሻ ጨዋታውን በቀጣይ ሳምንት ድሬዳዋ ተጉዞ ከድሬዳዋ ከተማ በማድረግ ዋንጫውን የሚቀበል ይሆናል፡፡ የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ታምሩ ታፌ ለቡድኑ ከፍተኛ ማበረታቻ ሽልማት እንደሚኖርም ገልጸዋል፡፡

የቡድኑ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በ2008 የሀዋሳ ከተማ ከ17 አመት በታች ቡድንን የሊጉ ቻምፒዮን ማድረግ የቻሉ ሲሆን አመዛኞቹ ተጫዋቾችን ወደ 20 አመት በታች ቡድን በመጡበት አመትም ቡድኑን የሊጉ አሸናፊ ማድረግ ችለዋል፡፡

ሀዋሳ ከተማ ከአምና ጀምሮ የተደረጉትን ሁለት ከ17 አመት በታች ዋንጫዎች ፣ ከ20 አመት በታች ዋንጫ እና ከ17 አመት በታች ጥለሎ ማለፍ ውድድሮች ጠራርጎ በመውሰድ በኢትዮጵያ የወጣቶች እግርኳስ ላይ የበላይ መሆን የቻለ ሲሆን ዘንድሮ ወደ ዋናው ቡድን ተጫዋቾችን በማሳደግ እና የመሰለፍ እድል በመስጠትም ለሌሎች ክለቦች በአርአያነት የሚጠቀስ ክለብ ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ አዲስ አበባ ላይ ከኢትዮጵያ መድን ያደረገውን ጨዋታ 2-1 ቢያሸንፍም ከሀዋሳ በ4 ነጥቦች በመራቁ የሊጉ አሸናፊነት ተስፋው ጨልሟል፡፡

በዛሬው እለት መካሄድ ከነበረባቸው 6 ጨዋታዎች ሁለቱ በዝናብ ምክንያት ያልተካሄዱ ሲሆን ውጤቶች እና የደረጃ ሰንጠረዡ ይህንን ይመስላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *