አስልጣኝ ተመስገን ዳና ስለ ሀዋሳ ከተማ U-20 ድል ይናገራል

የ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት እድሜ ብቻ ቀርቶታል፡፡ ትላንት በተደረገ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታም ሀዋሳ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን 7-0 በማሸነፍ ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል፡፡

በወጣቶች እግርኳስ ላይ ውጤታማ ከሆኑ አሰልጣኞች አንዱ የሆነው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ዘንድሮ አምና ከ17 አመት በታች ቡድኑን ይዞ ያሳካውን ድል ዘንድሮም በ20 አመል በታች ድል ደግሞታል፡፡ አሰልጣኝ ተመስገን ከትላንቱ ጨዋታ ፍጻሜ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ስለ ጨዋታው እና ቻምፒዮን ስለመሆናቸው

ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ጎሎቹ ፣ የጨዋታው እንቅስቃሴ እና ደጋፊዎች ያደረጉልን ማበረታቻ ሁሉ በጣም አስደሳችና እና ልዩ ስሜት ነበረው፡፡ በአጠቃላይ በድሉ ኮርቻለው፡፡

በተከታታይ አመታት አሸናፊ መሆን

ከ17 አመቱም ሆነ ከ20 አመት በታች ውድድር ግብ በቅድሚያ ለዋናው ቡድን ተተኪ ማፍራት ነው፡፡ በመቀጠል ደግሞ ውድድር ላይ የማሸነፍ አላማን ሰንቀን መጓዝ እና ውድድር ካለ ማሸነፍ አለ ብዬ በግሌ አምናለው፡፡ ተጫዋቾቹም ያንን ይዘው ነው ለዚህ የበቁት፡፡ ባሳለፍነው አመት የአሸናፊነት ተሞክሮ ይዘን ዘንድሮም ማሸነፍ እንደምንችል ተረድተን ነው ወደ ውድድር የገባነው፡፡ ስለዚህ ድሉ ይገባናል፡፡

ቀጣይ ግብ

እኔ እንደ አስልጣኝ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው ደረጃ በደረጃ ማደግ ነው የምፈልገው፡፡ እንደ አሰልጣኝ አምና ከ17 አመት በታች ቡድኑ ጋር ዘንድሮም ከ20 አመት በታች ቡድን ጋር ባለድል ሆኛለው፡፡ በርካታ ተጫዋቾችንም ለዋናው ቡድን አብቅቻለው፡፡ በቀጣይ አመት ደግም አንድ የተለየ ነገር እፈጥራለው ፤ ከተሳካል የማቅደው ቦታ መድረስ እችላለው፡፡ ባይሳካልኝም አሁን እዚህ ጋር የተሻለ ነገር ሰርቼ የተሻለ ቦታ መድረስ እቅድና አላማዬ ነው፡፡

በትልቅ ደረጃ ስለማሰልጠን

እንደ አሰልጣኝ በየአመቱ የተሻለ ነገር ፍለጋ እጥራለሁ፡፡ ራሴን የማሳደግ ውጥን አለኝ፡፡ ለዚህም በእየለቱ ትግል አደርጋለሁ፡፡ ሜዳ ላይ የምሰራው ቡድንም ያንን ጠቋሚ ነው፡፡ ከእኔ የሚጠበቀው ጠንክሮ መስራት እና በየጊዜው ራሴን ማሻሻል ነው፡፡

በመጨረሻ..

በመጀመሪያ እስካሁን ያልተለዩን ደጋፊዎች እነሱ ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ ሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብም ድጋፍ ጥሩ ነው ያደረገልን፡፡ ለዚህ ውጤት ሁሉም ባለ ድርሻ ነውና ምስጋና እና ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *