በ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጥሎ ማለፍ ውድድር ወሳኝ ምእራፍ ላይ ደርሷል፡፡ ነገ ከሰአት በሚደረጉ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎችም የዋንጫ ተፋላሚዎች ይለያሉ፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ የሁለቱን የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ በዚህ መልኩ አሰናድታለች፡፡
ደደቢት ከ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ
ይህ ጨዋታ የሊጉን ሀያል ቡድን ደደቢትን ወደፊት የኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ላይ ያንፀባርቃሉ ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው የአካዳሚ ወጣቶች ጋር የሚያገናኝ ጨዋታ ነው፡፡
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊዎቹ ደደቢቶች በዘንድሮው የውድድር ዘመን እስካሁን ድረስ ምንም ሽንፈት አለማስተናገዳቸው ምን ያህል ጠንካራ መሆናቸውን እና በሊጉ ከሚወዳደሩት ቡድኖች ጋር ያላቸውን ሰፊ ልዩነት በግልፅ የሚያሳይ ሆኗል፡፡
ሰማያዊዎቹ በጥሎ ማለፉ እስካሁን ባደረጓቸው ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቻቸውን በቀላሉ እያሸነፉ እዚህ መድረስ ችለዋል፡፡ በመጀመርያው ዙር አዲስ አበባ ከተማን በብርቱካን ገብረክርስቶስ እና ሰናይት ቦጋለ ጎሎች 2-0 ሲረቱ በ2ኛው ዙር ሲዳማን በፎርፌ አሸንፈው በማለፍ በሩብ ፍፃሜው ጥረት ኮርፓሬትን በሎዛ አበራ ሐት-ትሪክ በመታገዝ 3-0 አሸንፈው ለነገው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ መድረስ ችለዋል፡፡ በተጨማሪም ደደቢቶች ባሳለፍነው ቅዳሜ በጎል ክለብ በተደረገላቸው የማበረታቻ ሽልማት በይበልጥ በሞራል ተነቃቅተው ለዚህ ጨዋታ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተጋጣሚው ደደቢት በነበረበት ምድብ “ሀ” በሊጉ በ13 ነጥብ በ8ኛ ደረጃ ይዞ ቢያጠናቅም በጥሎ ማለፉ የተሻለ ጉዞ ማድረግ ችሏል፡፡ የተጫዋቾቹ ብቃት እንዳለ ሆኖ በተነፃፃሪነት በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር መደልደሉ ወደ ግማሽ ፍፃሜው እንዲደረስ አስተዋጽኦ አበርክቷል ማለት ይቻላል፡፡ በሁለተኛው ዙር ድሬዳዋ ከተማን በፎርፌ አሸንፎ ሲያልፍ በሩብ ፍፃሜው ንፋስ ስልክ ላፍቶን 3-1 አሸንፏል፡፡
ዘንድሮው የውድድር ዘመን ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ምድብ ሀ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ደደቢት እጅግ ፍፁም ከሆነ የበላይነት ጋር 4-1 እና 8-1 በሆነ በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል፡፡
በነገው ጨዋታ ላይ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በኩል የቡድናቸው ደካማ የተከላካይ ክፍል የሊጉን ጠንካራ የማጥቃት ጥምረትን ለመቋቋም ከፍተኛ ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡ በተመሳሳይ በአካዳሚዎች በኩል ፈጣኖቹ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች የሆኑት ቃልኪዳን ተስፋዬ ፣ ይመችሽ ዘውዴ እንዲሁም የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነችው ዳሳሽ ሰዋገኝ ይጠበቃሉ፡፡
ሀዋሳ ከተማ ከ አዳማ ከተማ
በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአዲስ መልኩ ከወትሮው በተሻለ አቅም ተጠናክረው የመጡት ሁለቱ ክለቦች በሊጉ በየምድባቸው እጅግ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው አሳልፈዋል፡፡
በምድብ “ሀ” የነበሩት አዳማ ከተማዎች የሊጉ ቻምፒዮን ደደቢትን ሳይቀር ከሜዳቸው ውጪ በመምጣት ፈትነው አቻ መለያየት ችለዋል፡፡ ይህ ውጤት ደደቢት በውድድር ዘመኑ ነጥብ የጣለበት ብቸኛ ጨዋታ መሆኑ ሲታሰብ የአዳማን ጥንካሬ ያጎላዋል፡፡ በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማዎች በምድብ “ለ” የምድቡ አሸናፊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጭምር መርታት የቻለ ጠንካራ ስብስብ ባለቤት ናቸው፡፡
አዳማ ከተማ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ በተገኙ እና ነባር የቡድኑ ተጫዋቾችን በማዋሃድ እጅግ ጠንካራ ቡድን መገንባት ችሏል፡፡ በቡድኑ ውስጥ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ በክዊንስ ኮሌጅ እንዲሁም በተለያዩ ክለቦች መጫወት የቻለችውና ባገጠማት ጉዳት ምክንያት ለተወሰኑ አመታት ከእግርኳስ ርቃ የነበረችው እንደገና አለምዋሶ ከወጣቶቹ የቡድኑ ተጫዋቾች ጋር በተለይም ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ፍሬ ከሆነችው አጥቂዋ ሴናፍ ዋቁማ ጥሩ የአጥቂ ስፍራ ጥምረት መፍጠር ችላለች፡፡
ቡድኑ ከማጥቃቱም በዘለለ በሊጉ ጥሩ የሆነ እግርኳስ ከሚጫወቱ ቡድኖች ተጠቃሽ ነው፡፡ በተጨማሪም የቡድኑ የአማካይ እና ተከላካይ ስፍራ ጥንካሬም ተጠቃሽ ነው፡፡
የአምናው የደቡብ ምስራቅ ዞን አሸናፊዎቹ ሀዋሳ ከተማዎች የቡድናቸው ወሳኝ ተጫዋቾችን በዝውውር መስኮቱ በሌሎች ቢነጠቁም ዘንድሮም ጠንካራና ተፎካካሪ ቡድን መገንባት ችለዋል፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዘመን እጅግ ድንቅ እንቅስቃሴን እያደረገች የምትገኘው ግብ ጠባቂያቸው ትእግስት አበራም በበርካታ አጋጣሚዎች ቡድኑ በሚቸገርበት ወቅት ቡድኑን መታደግ ችላለች፡፡ በአማካይ ስፍራ ላይ የቡድኑ አምበል እታለም አብዩ የተጋጣሚን ቡድን የማጥቃት እንቅስቃሴን ከማክሸፍ በዘለለ የቡድኑን እንቅስቃሴ በማደራጀትና በመምራት በኩል በዘንድሮው አመት በተለየ ነጥራ መውጣት ችላለች፡፡ ከሷ በተጨማሪም ሌላኛዋ ታታሪ አማካይ ትርሲት መገርሳ በ24 ግቦች የምድቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለሆነችው አይናለም አሳምነው ያለቀላቸው ኳሶችን በማቀበል እንዲሁም በቡድኑ የመከላከል እንቅስቃሴ ላይ በትጋት በመሣተፍ ባሳየችው ድንቅ እንቅስቃሴ የበርካቶች አድናቆት ማትረፍ ችላለች፡፡
ሀዋሳ ከተማ በ2ኛው ዙር መከላከያን 2-1 ሲያሸንፍ በሩብ ፍጻሜው ጠንካራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በመለያ ምት 5-4 አሸንፎ ለግማሽ ፍጻሜው በቅቷል፡፡ አዳማ ከተማ ደግሞ በ2ኛው ዙር ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲን 3-1 ሲያሸንፍ በሩብ ፍጻሜው ጊዲኦ ዲላን 1-0 በማሸነፍ እዚህ ደርሰዋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ጨዋታ ከቀናት በፊት ተገናኝተው አዳማ ከተማ 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ሊጉን በ3ኛ ደረጃ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡