አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስለ ዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ይናገራሉ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፊቱ ለሚጠብቁት የአፍሪካ ዋንጫ እና ቻን ማጣርያዎች የሚረዳውን ዝግጅት በ23 ተጫዋቾች በትላንትናው እለት ጀምሯል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስለ ዝግጅቱ እና አጠቃላይ የብሔራዊ ቡድን ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

የዝግጅት ጊዜ መጀመርና ቀጣይ ስራቸው

ዛሬ በይፋ ስራችንን ጀምረናል፡፡ በቀጣይ በቀሩት ቀናት ውስጥ ተጫዋቾቹ ከጨዋታ የመጡ በመሆኑ እንዳያችሁት ጠንከር ያሉ ልምምዶች አልሰጠናቸውም፡፡ የማቀናጀት ስራ ነው በዋናነት የሰራነው፡፡ ከዚህ በኋላ ባሉት ቀናት እኔ ወደምፈልገው አጨዋወት ለማምጣት በዚህ መልኩ ዝግጅታችንን የምንቀጥል ይሆናል።

ቡድኑን ስላልተቀላቀሉ ተጫዋቾች

አራቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ክለባቸው ኢንተርናሽናል ጨዋታ ስላለበት አልተቀላቀሉም፡፡ ቢኖሩ መልካም ነበር ፤ ከሌሉ ግን እነሱ የሉም ብለን ቡድን ከመስራት አንቆጠብም፡፡ የሚቻለንን ለመስራት እንሞክራለን። ከደረሱልን እሰየው ነው ፤ ካልመጡ ግን ያው ስራችንን እንቀጥላለን።  ከሽመልስ እና ኡመድ ጋር ተነጋግረናል፡፡ በእርግጠኝነት የፊታችን ሰኞ ወይም ማክሰኞ ይገባሉ። እንደመጡም ቀጥታ ወደ ልምምድ አንከታቸውም የተወሰኑ ቀናት እረፍት እንሰጣችዋለን፡፡

የአቋም መፈተሻ ጨዋታ

እንግዲህ የሚሆነውን አብረን እናየዋለን። እኛ ግን አለ ብለን ነው ፕሮግራም አውተን እየጠበቅን እና እየተዘጋጀን የምንገኘው። የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ቢኖርና ብንጫወት በጣም አስፈላጊ ነው።

ስለ ተጫዋች ምርጫ

ሀገር ውስጥ በጥሩ ብቃት ላይ አሉ የሚባሉና በተለይ እኔ ለምፈልገው አጨዋወት ይሆናሉ ያልኳቸውን ከሀገር ውስጥም ከውጭ መርጫለው። ምርጫ ስትመርጥ ሁሉን ማስደሰት አትችልም ፤ በምትችለው መጠን ሁሉን ለማሳተፍ ትሞክራለህ፡፡ በተረፈ የመጀመርያ ምርጫ ነው በቀጣይ ያልተመረጡ ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ወደ ፊት የሚካተቱ ይሆናል።

የስብስቡ ከዚህ ቀደም ከነበረው እምብዛም አለመለወጥ

ሀገሪቷ ለአመታት ስትጎዳበት የቆየ ችግር ነው። አንድ አሰልጣኝ ሲመጣ ቡድን ይገነባል ሌላው ሲመጣ ቡድን ያፈርሳል። ይሄ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ መቅረት አለበት፡፡ አሰልጣኝ ሊቀያየር ይችላል ፤ ያለው ቡድን ግን መቀጠል አለበት፡፡ እኔም በዚህ ስለማምን የተወሰኑ አዲስ ተጨዋቾችን አመጣው እንጂ ቀድሞ ከነበረው ብሔራዊ ቡድን ብዙ ለውጥ አላደረኩም ።

በመጨረሻ

ከጋና ጋር ላለው ጨዋታ 18 ተጨዋቾች የሚያቀኑ ሲሆን የቀሩት ተጨዋቾች አይበተኑም እዚሁ ጠብቀውን ስንመለስ ዝግጅታችን የምንቀጥል ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *