የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 25ኛ ሳምንት ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 25ኛ ሳምንት ሀሙስ ተደርገዋል፡፡ በምድብ ሀ ሽረ ከመሪዎቹ ያለውን ልዩነት ሲያጠብ በምድብ ለ ጅማ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና አሸንፈዋል፡፡

ምድብ ሀ

ሽረ ላይ ለገጣፎ ለገዳዲን የገጠመው ሽረ እንዳስላሴ 1-0 በማሸነፍ ትላንት ጨዋታ ካላደረጉት መሪዎቹ ወልዋሎ እና መቀለ ያለውን ነጥብ ማጥበብ የቻለበትን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ የሽረ እንዳስላሴን ወሳኝ የድል ጎል ዘላለም በረከት ሲያስቆጥር በዳኛ ወሳኔ ላይ ተቃውማቸውን የገለፁት አስልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬ ከመቀመጫቸው በቀድ ካርድ እንዲወጡ የተደረገበት የጨዋታው ክስተት ነበር፡፡

ሱሉልታ ያያ ቪሌጅ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የአራዳ ክፍለ ከተማ ና የአማራ ውሃ ስራ ጨዋታ ወደ ለገጣፎ ሜዳ የዞረ ሲሆን ከወጣለት መርሀ ግብርም ቀደም ብሎ ተጀምሮ አማራ ውሀ ስራ 2-1 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ዳዊት ሞገስ በ25ኛው ደቂቃ አማራ ውሀ ስራን ቀዳሚ ሲያደርግ በ35ኛው ደቂቃ አብዱ እልቂ ባስቆጠራት ግብ አራዳዎች አቻ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ ከዕረፍት መልስ አማራ ውሃ ስራ በ75ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ታደሰ ባስቆጠረው ግብ ጨዋታው በአማራ ውሀ ስራ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በ8፡00 ኦሜድላ ሜዳ ላይ ሁለቱ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት አአ ፖሊስ እና አክሱም ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በእንግዳው አክሱም አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ውጤቱም አክሱም ከተማን ከወራጅ ቀጠናው ያለውን የነጥብ ልዩነት እንዲያሰፋ ማድረግ ችሏል፡፡

ሰበታ ላይ ሰሜን ሸዋ ደብርብርሃንን ያስተናገደው ሰበታ ከተማ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ኢሳያሰ ታደሰ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ሰሸ ደብረብርሀን ወደ አንደኛ ሊጉ ለመውረድ ተቃርቧል፡፡ በ26ኛው ሳምንት የሚያደርገውን ጨዋታ ከተሸነፈም ወደ አንደኛ ሊጉ መውረዱን ያረጋግጣል፡፡

ቡራዩ ላይ ቡራዩ ከተማን ከ ኢትዮጵያ መድህን ያገናኘው ጨዋታ በቡራዩ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ለቡራዩ ከተማ ነስረዱን ሀይሌ በ38ኛው ደቂቃ እንዲሁም በኃይሉ ሀይሉ በ60ኛው ደቂቃ የድል ጎሎቹን አስቆጥረዋል፡፡

በእለቱ በምድብ ሀ ከተካሄዱት ጨዋታዎች መካከል ያለ ግብ የተጠናቀቀው ጨዋታ በሱሉልታ ከተማ እና ኢትዮጵያ ውሀ ስፖርት መካከል የተካሄደው ነው፡፡

የምድበ መሪ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ ባህርዳር ከተማ እንዲሁም መቀለ ከተማ ከ ወሎ ኮምቦልቻ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በፌዴሬሽኑ ውሳኔ መሰረት ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግረዋል፡፡

ምድብ ለ

የምድቡ መሪ የሆነው ጅማ ከተማ ወደ ቦንጋ ያደረገውን ጉዞ በአሸናፊነት በመወጣት ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚያደርገውን ግስጋሴ ቀጥሏል፡፡ ጅማ ከተማ ካፋ ቡናን 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ንጋቱ ገብረስላሴ በ35ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ ጅማ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሎታል፡፡

ከፍተኛ ግምት የተሰጠው የሻሸመኔ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ በሻሸመኔ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ሻሸመኔ ከተማ ቀዳሚ መሆን የቻለበትን ጎል ኤልያስ እንድርያስ በ3ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር በ35ኛው ደቂቃ ወንድምአገኝ ግርማ ባስቆጠራት ግብ ወልቂጤ አቻ መሆን ችለዋል፡፡ የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ኤፍሬም ቶማስ ግብ በማስቆጠር ባለሜዳው ሻሸመኔ ወሳኝ 3 ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሎታል፡፡

ሆስዕና ላይ ሀድያ ሆሳዕና ዲላ ከተማን አስተናግዶ ከዕረፍት መልስ በተገኘች ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፎ መውጣት ችሏል፡፡ በዚህም ከመሪው ጅማ ያለውን ርቀት አስጠብቆ መከተሉን ቀጥሏል፡፡

ሀላባ ከተማ ከተከታይ ሁለት ጨዋታ ሽንፈት በኃላ ወደ አሸናፊነት መመለስ የቻለበትን ውጤት ነገሌ ቦረና ላይ አስመዝግቧል፡፡ በ5ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ፍቅሬ ቀዳሚዋን ግብ ሲያስቆጥር ስንታየው መንግስቱ በ70ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ጎል አክሏል፡፡

ስልጤ ወራቤ አርሲ ነገሌን አስተናግዶ ከእረፍት በፊት እና በኋላ በተቆጠሩ ጎሎች 2-0 በማሸነፍ በሁለተኛው ዙር ባሳየው መሻሻል ቀጥሏል፡፡ አርሲ ነገሌ ሽንፈቱን ተከትሎ የምድቡን ግርጌ ለመያዝ ተገዷል፡፡

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ፖሊስ ከ ደቡብ ፖሊስ ያደረጉት ጨዋታ በእንግዳው ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የደቡብ ፖሊሱ ተከላካይ ጢምቲዎስ ቢረጋ ኳስ በግብ ክልል ውስጥ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ልይህ ገ/መስቀል አስቆጥሮ ድሬዳዋ ፖሊስን ቀዳሚ አድርጎ ወደ እረፍት አምርተዋል፡፡ ከእረፍት መልስ ደቡብ ፖሊሶች በ63ኛው ደቂቃ ላይ በሙዲን አብደላ ጎል አቻ ሲሆኑ በ69ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ሀብታሙ ገዛህኝ ደቡብ ፖሊስ ከሜዳው ውጭ ወሳኝ 3 ነጥብ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡ በጨወታው በ72ኛ ደቂቃ ላይ እሸቱ እንድርያስ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰን በመሳደቡ በቀይ ካርድ ከተቀያሪ ወንበር ተወግዷል፡፡

ነቀምት ላይ ነቀምት ከተማ ከ ናሽናል ሲሚንት ጋር ያገናኘው መርሀ ግብር በነቀምት 3-2 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ አዲስ አበባ ላይ ፌደራል ፖሊስ ከ ጅንካ ከተማ 1-1 አቻ በሆነ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *