በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውና 12 ክለቦችን ያሳተፈው የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ድሬዳዋ ላይ በተዘጋጀ ስነ ስርአት ተጠናቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት የሊጉ ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ሀዋሳ ከተማም ዋንጫውን ተቀብሏል፡፡
ድሬዳዋ ስታድየም ላይ ድሬዳዋ ከተማን የገጠመው ሀዋሳ ከተማ 4-2 በማሸነፍ በድል የውድድር ዘመኑን ማጠናቀቅ ችሏል፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ድሬደዳዋ ከተማዎች የተሻለ ቢንቀሳቀሱም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ሪትም የገቡት ሀዋሳዎች ገብረመስቀል ዱባለ በ23ኛው ደቂቃ ላይ ከአንድነት መዐዛ የተሻገረለትን ኳስ በግምባሩ በመገጨት ወደ ግብነት ቀይሮ ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡
ድሬዳዋ ከተማ አቻ ለመሆን የፈጀባቸው 4 ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ በዕውቀቱ ከፍያለው በመስመር እየገፋ ወደ ውስጥ አጥብቦ በመግባት ድሬዳዋን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ የሀዋሳ ከተማው አጥቂ ገብረመስቀል ዱባለ ልዩነት ፈጣሪ መሆን የቻለበት ነበር፡፡ ገና እንደተጀመረ ፀጋአብ ዩሴፍ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ለራሱም ለክለቡም ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን በድጋሚ መሪ አድርጎል፡፡ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የድሬዳዋ ተከላካዮች በቸርነት አውሽ ላይ የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ ፌድራል ዳኛ ባሪንሶ ባላንጎ የሰጡትን ቅጣት ምት ወደ ግብነት ቀይሮ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል፡፡ ገብረመስቀል በ88ኛው ደቂቃ ላይ ከጸጋአብ ዮሴፍ የተመቻቸለትን ኳስ ለሀዋሳም ለራሱም 4ኛ ጎል በማድረግ የቡድኑንም መሪነት አስተማማኝ ማድረግ ችሏል፡፡
ጨዋታው ሊጠናቀቅ 4 ጭማሪ ደቂቃ ላይ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው በዕውቀቱ ከፍያለው ለራሱና ለክለቡ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በጨዋታው ከድሬዳዋ ከተማ አጥቂው በዕውቀቱ ከፍያለው ፣ ከሀዋሳ ከተማ 4 ግቦች በእለቱ ያስቆጠረው ገብረመስቀል ዱባለ እና ተከላካዩ ሰለሞን ወዴሳ እጅግ አመርቂ እንቅስቃሴን ማድረግ ችለዋል፡፡
ከጨዋታው ፍጻሜ በኃላ ሀዋሳ ከተማዎች ከአቶ ዘሪሁን ቀቀቦ (የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባል እና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ) እንዲሁም ከአቶ አስራት ጫላ (የድሬዳዋ ከተማ ስፖርት ምክር ቤት ም/ሰብሳቢ) እጅ የተዘጋጀላቸውን ዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተረክበዋል፡፡ ትላንት ደደቢትን 2-1 ያሸነፈው አዳማ ከተማ 2ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ የብር ሜዳልያ ተሸላሚ ሲሆን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-1 የተለያየው ኢትዮጵያ ቡና 3ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የነሀስ ሜዳልያ ተሸልሟል፡፡ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ለስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ የተዘጋጀውን ዋንጫ ተሸልሟል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ ቀደም በየውድድሮቹ መጨረሻ የሚያበረክተውን የኮከቦች ሽልማት ዘንድሮ በመቀየር የሁሉንም ውድድሮች በአንድ ላይ የሽልማት ደረጃን በጠበቀ መልኩ እንደሚያካሂድ በማስታወቁ የ20 አመት በታች ውድድር ኮከቦችም ከሌሎች ውድድሮች ጋር በጋራ የሚካሄድ ይሆናል፡፡